በወልቂጤ በሰልፈኞች ላይ ፖሊስ በከፈተው ተኩስ ሦስት ሰዎች መገደላቸውን ኢሰመኮ አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, Wekite FM
በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ የውሃ ችግራቸውን ለማሰማት ሰልፍ በወጡ ነዋሪዎች ላይ የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ ሦስት ሰዎች መገደላቸውን እና ቢያንስ 30 ሰዎች የአካል ጉዳት እንደረሰባቸው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ።
ኮሚሽኑ የፀጥታ ኃይሎች በሰልፈኞቹ ላይ በወሰዱት ተመጣጣኝ ያልሆነ የኃይል እርምጃ ለደረሰው የሕይወት መጥፋት እና የአካል ጉዳትም ተጠያቂነት ሊረጋገጥ እንደሚገባም ኢሰመኮ አርብ የካቲት 10/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አሳስቧል።
ኮሚሽኑ የቧንቧ ውሃ አቅርቦት ከወር በላይ ለሆነ ጊዜ በከተማዋ በመቋረጡ መንግሥት መፍትሄ እንዲሰጣቸው ሰልፍ በወጡ ነዋሪዎች ላይ ፖሊስ በከፈተው ተኩስ የተገደሉት ሦስት ሰዎች ጭንቅላታቸው እና ደረታቸውን በጥይት ተመትተው መሆኑን አስታውቋል።
በተጨማሪም ቢያንስ በ30 ሰዎች ላይ የተለያየ መጠን ያላቸው የአካል ጉዳት መድረሱንም ኢሰመኮ የዐይን ምስክሮችን፣ ተጎጂዎችን፣ የተጎጂ ቤተሰቦችን እና የጤና ባለሙያዎችን በማነጋገር መረጃ ሰብስቤያለሁ ብሏል።
በከተማዋ ያጋጠመው የውሃ ችግር ለረጅም ጊዜም በመቆየቱ ነዋሪዎች ብሶታቸውን ለማሰማት ረቡዕ የካቲት 08/2015 ዓ.ም. ወደ ከተማዋ የውሃ ልማት አስተዳደር ቢሮ ባቀኑበትም ወቅት የፀጥታ ኃይሎች ተኩስ መክፈታቸውን በዕለቱ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
በወልቂጤ ሆስፒታል የቀዶ ሕክምና ሐኪም የሆኑት ዶክተር በኃይሉ ደጉ፣ ደረታቸውን እና ጭንቅላታቸውን በጥይት ተመተው የሞቱ የሁለት ሰዎች አስከሬን ወደ ሆስፒታሉ መምጣታቸውን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
እንዲሁም አምስት ሰዎች ክፉኛ ቆስለው በአስጊ ሁኔታ ወደ ሆስፒታሉ እንደመጡ እና ሌሎች ሦስት ሰዎች ደግሞ ከባድ ነገር ግን ለሕይወታቸው አስጊ ባልሆነ ሁኔታ ተጎድተው ወደ ሆስፒታሉ መግባታቸውን ዶክተር በኃይሉ ለቢቢሲ ገልጸው ነበር።
ለጉዳቱ ምክንያት የሆነው ከሰልፈኞች ውስጥ የተወሰኑት ሰዎች የከተማው የውሃ አገልግሎት ጽህፈት ቤት ላይ ድንጋይ በመወርወራቸው እና የመኪና መንገድ በመዝጋታቸው እንደሆነ የአካባቢው ባለሥልጣናት መናገራቸውን ኢሰመኮ በመግለጫው ላይ አስፍሯል።
“አንገብጋቢ በሆነ የውሃ አቅርቦት ጥያቄ ሰልፍ ወጥተው ድንጋይ በወረወሩ እና መንገድ በዘጉ ሰዎች ላይ ሕይወት የሚያጠፋ መሣሪያ ተጠቅሞ እና ጥይት ተተኩሶ ነዋሪዎች መገደላቸው ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው እርምጃ ነው” የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ተናግረዋል።
ጨምረውም የክልሉ መንግሥት አስቸኳይ ማጣራት አድርጎ በአጥፊዎች ላይ ተጠያቂነት ሊረጋገጥ እና የተጎዱ ሰዎችም ተገቢውን ካሳ ሊያገኙ ይገባል በማለት አሳስበዋል።
ኮሚሽነር ዳንኤል ለወደፊቱም ተመሳሳይ ዓይነት የመብት ጥሰቶች እንዳይፈጸሙ ለፀጥታ ኃይሎች ግልጽ አመራር መሰጠት አለበት ሲሉ መምከራቸውን መግለጫው አስፍሯል።












