ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአንድ የቤልጂዬም መንደር ነዋሪዎች በሎተሪ 143 ሚሊዮን ዩሮ አሸነፉ
በቤልጂዬም አንድ መንደር ውስጥ የሚኖሩ 165 ሰዎች በጋራ የ143 ሚሊዮን ዩሮ ሎቶሪ አሸናፊ ሆኑ።
ኦልምን በተባለ መንደር የሚኖሩት ሰዎች ሎቶሪውን የገዙት እኩል ገንዘብ አዋጥተው ነበር። ከሎቶሪው እያንዳንዳቸው 868 ሺህ ዩሮ ይካፈላሉ።
የቤልጂዬም ብሔራዊ ሎቶሪ እንዳለው፣ በሎቶሪው ከ27 ሚሊዮን በላይ እጣዎች ነበሩ።
ሰባት ትክክለኛ ቁጥሮችን በማስገመት ለአሸናፊዎች ከፍተኛ ገንዘብ የሚሰጠው ዩሮሚሊዮንስ፣ በዘጠኝ የአውሮፓ አገራት መካከል የሚካሄድ የሎቶሪ እጣ ሲሆን አሸናፊዎች እስከ 142 ሚሊዮን 897 ሺህ 164 ዩሮ ድረስ ይሸለማሉ።
የብሔራዊ ሎቶሪ ቃል አቀባይ ጆክ ቨርሞር እንዳለችው፣ ቤልጂዬም ውስጥ በቡድን ተወዳድረው አሸናፊ የሆኑ ሰዎች ማግኘት የተለመደ አይደለም።
ከዚህ ቀደም እንዲህ ብዙ ሰዎች በጋራ ተወዳድረው አሸንፈውም አያውቁም።
165ቱ የአንድ መንደር ነዋሪዎች ሎቶሪው እንደደረሳቸው ሲሰሙ እጅግ እንደተደሰቱ የገለጸችው ቃል አቀባዩዋ “ምርጥ የገና ስጦታ ነው ያገኙት” ብላለች።
እጣውም ቤልጂዬም ውስጥ የሚያዘጋቸው ወኪል ተቋም ኃላፊ፣ ለዓመታት ሰዎች በጋራ እጣ እንዲያወጡ ሲያበረታታ ቆይቷል።
የአንድ መንደር ሰዎች በጋራ ማሸነፋቸውን ለማመን ስለከበዳቸው ዜናውን ስድስት ጊዜ ደጋግመው እንደሰሙትም ተናግሯል።
ያሸነፉት ሰዎች ማንነት እስካሁን ይፋ አልተደረገም።
ከዚህ ቀደም አንድ የዩናይትድ ኪንግደም ዜጋ 195 ሚሊዮን ፓውንድ አሸንፎ ነበር። ይህም አንድ ሰው የደረሰው ትልቁ ገንዘብ ነው። ከወራት በፊት ደግሞ 184 ሚሊዮን ፓውንድ አሸንፈዋል።
ዩሮሚሊዮንስ የሚዘጋጀው በቤልጂዬም፣ ፈረንሳይ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ስፔን፣ ፖርቹጋል፣ አየርላንድ፣ ኦስትሪያ፣ ስዊዘርላንድ እና ሉግዘምበርግ ነው።