ሴሊን ዲዮን የማይድን ሕመም እንደያዛት ይፋ አደረገች

ታትሟል

ዝነኛዋ ድምጻዊት ሴሊን ዲዮን በብዛት በማይታይና በማይድን ሕመም መያዟን ተናገረች።

ሙዚቀኛዋ ‘ስቲፍ ፐርሰን ሲንድረም’ ወይም ኤስፒኤስ በተባለው አንጎልና ነርቮችን በሚያጠቃ ሕመም ነው የተያዘችው።

ፈረንሳዊት ካናዳዊት ድምጻዊቷ ሕመሙ እንደያዛት ለ5.2 ሚሊዮን የኢንስታግራም ተከታዮቿ ገልጻለች።

ሕመሙ ሰውነቷ ከቁጥጥሯ ውጭ እንዲንቀሳቀስ ከማድረጉ ባሻገር፣ መራመድ እና መዝፈን እንዲሳናት ማድረጉን ተናግራለች።

በቀጣይ ዓመት ዩናይትድ ኪንግደም እና አውሮፓ ውስጥ ልታቀርብ የነበረውን ኮንሰርት ለመሰረዝም ተገዳለች።

 “ዘለግ ላለ ጊዜ ነው በሕመም የተሰቃየሁት። ችግሬን ለመናገር ግን አልደፈርኩም። ከሚሊዮን ሰዎች አንዱ የሚይዘው በሽታ ነው የያዘኝ” ብላለች የ54 ዓመቷ ሴሊን ዲዮን።

ሰውነቷ ከቁጥጥሯ ውጭ የሚቀሳቀሰው በዚህ ሕመም ምክንያት እንደሆነ ገልጻ “የዕለት ተዕለት ሕይወቴን አስተጓጉሎታል። እንደ ድሮው መዝፈንም አልቻልኩም። ቀጣይ ኮንሰርቶቼን መሰረዜን ስነግራችሁ እያዘንኩ ነው” ብላለች።

ለተወዳጁ ‘ታይታኒክ’ ፊልም ማጀቢያ የዘፈነችው ‘ማይ ኸርት ዊል ጎ ኦን’ ኦስካር ተሸልሟል።

ባለቤቷ ረኔ አንገሊል ካንሳር ሲይዘው እአአ በ2014 ሙዚቃ ማቋረጧን ገልጻ ነበር። ከዓመት በኋላ መልሳ ሙዚቃ ብትጀምርም በ2016 ባለቤቷ እና ወንድሟ ሲሞቱ በድጋሚ ሙዚቃ አቋርጣለች።

በኮሮናቫይረስ ምክንያት የተቋረጡ ኮንሰርቶችን በድጋሚ ለመጀመር አቅዳ የነበረ ቢሆንም፣ በጤና እክሏ ምክንያት ማሳካት አልቻለችም።

“ጎበዝ ሐኪሞች አሉኝ። ውድ ልጆቼም እየተንከባከቡኝ ነው። የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ ወደ መድረክ ለመመለስ እየሞከርኩ ነው” ብላ ነበር።

ድምጻዊቷ ለአድናቂዎቿ እያነባች ባስተላለፈችው መልዕክት “የምችለው መዝፈን ብቻ ነው። የምወደውም መዝፈን ነው። አድናቂዎቼ ናፍቃችሁኛል። ለእናንተ ማቀንቀን ናፍቆኛል። መድረክ ላይ ስወጣ በሙሉ አቅሜ መዝፈን ነው የምፈልገው። ሕመሙ ግን ያንን እንዳደርግ አልፈቀደልኝም” ብላለች።

ሴሊን ዲዮን የገጠማት ሕመም ለመረዳት የሚያስቸግርና ሕክምናውም የከበደ ነው።

ጡንቻ እንዲወጠር የሚያደርገው ይህ ሕመም የስሜት ሕዋሳት እጅግ ስሱ እንዲሆኑ በማድረግ ሰውነት ከቁጥጥር ውጭ ማንቀሳቀስን ያስከትላል።

ሕመሙ ያለባቸው ሰዎች መራመድ ወይም መንቀሳቀስ አይችሉም። ከቤታቸው ሲወጡ የሚሰማው እያንዳንዱ ድምጽ በጣም ስለሚረብሻቸውና ሊወድቁ ስለሚችሉ አዘውትረው ለመውጣት አይፈልጉም።

ከቁጥጥራቸው ውጭ በተደጋጋሚ ስለሚወድቁ የአካል ጉዳት ይደርስባቸዋል።