ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዩኬ፣ ጣሊያን እና ጃፓን ‘አእምሮ የሚያነብ’ የጦር ጄት ለመገንባት ተጣመሩ
የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚንስትር ሪሺ ሱናክ አገራቸው ዩኬ ሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) የሚጠቀም እጅግ ዘመናዊ ተዋጊ ጄት ለመሥራት ከጣሊያን እና ጃፓን ጋር ጥምረት እንደፈጠረች ይፋ ሊያደርጉ ነው።
ዩኬ በዚህ ጥምረት መካተቷ በሺዎች ለሚቆጠሩ የአገሪቱ ዜጎች የሥራ ዕድል ከመፍጠሩም በተጨማሪ በአገራቱ መካከል ያለውን የደኅንነት ትብብር ያጠናክራል ተብሏል።
ሦስቱ አገራት የሚያመርቱት የሰዎችን አእምሮ ያነባል የተባለው የጦር ጄት እአአ በ2030 አጋማሽ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ተብሏል።
ይህ ቴምፐስት የተባለው የጦር ጄት አሁን ላይ አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ታይፉን ጀቶችን በመተካት ዘመን አፈራሽ የሆኑ እንደ ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤሎችን ይታጠቃል ተብሏል።
ይህ ዘመናዊ ጄት ይዞት ከሚመጣው አማራጮች (ፊቸርስ) መካከል አንዱ አብራሪዎች ሥራ ሲበዛባቸው ወይም አስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ ሲገቡ አማራጭ መስጠት የሚያስችል ሰው ሠራሽ አስተውሎት ተገጥሞለታል።
ወደፊትም በዚህ የጦር ጀት ሥርዓት ላይ ማሻሻያ ማድረግ (አፕግሬድ) ቢያስፈልግ አንድን መተግበሪያ ከኢንተርኔት ላይ አውርዶ ስልክ ላይ እንደመጫን ቀላል ይሆናል ተብሏል።
ይህን ውስብስብ የቴክኖሎጂ ውጤት እውን ማድረግ ከፍተኛ ገንዘብ የሚጠይቅ በመሆኑ አገራቱ መጣመርን መርጠዋል።
በዚህ የጦር ጄት ግንባታ ላይ የጃፓኑ ሚስቲቡሺ ተሳታፊ ሲሆን እንደ ቦይንግ ላሉ ግዙፍ ኩባንያዎች የአውሮፕላን ሞተር የሚያቀርበው ሮልስ-ሮይስ ደግሞ ለቴምፐስት ጄት ሞተር የመሥራት ኃላፊነት ተሰጥቶታል።
ኤምቢዲኤ የተሰኘው የፈረንሳይ፣ ዩኬ እና ጣሊያን ጦር መሣሪያ አምራች በበኩሉ ጄቱ ላይ የሚገጠሙ ሚሳኤሎችን ያቀርባል።
ሌሎች አገራትም ይህን ፕሮጀክት ሊቀላቀሉ ይችላሉ። ፈረንሳይ፣ ጀርመን እና ስፔን የራሳቸውን ዲዛይን እየሠሩ ሲሆን አሜሪካም ለብቻዋ የራሷን ዘመናዊ ጀት እያበለጸገች ትገኛለች።
ዩናይትድ ኪንግደም በዚህ ዘመናዊ የጦር ጀት ግንባታ ተሳታፊ መሆኗ ደኅንነቷን ከማረጋገጡም በላይ በርካታ የሥራ ዕድልን በመፍጠር እና የጦር መሣሪያን በሽያጭ ወደ ውጪ አገራት በመላክ በምጣኔ ሃብቷ ላይ ጉልህ አዎንታዊ ሚና ሊጫወት ይችላል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ የአገራቱን ጥምረት ዛሬ አርብ ይፋ ያደርጋሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፤ ለአስተዳደራቸው የዩናይትድ ኪንግደም ደኅንነት ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው መሆኑን ተናግረዋል።
ዩናይትድ ኪንግደም እና አጋሮቿ፤ ውስብስብ በሆነ የቴክኖሎጂ ውጤት የታገዘ የደኅንነት ስጋት ሊገጥመን ስለሚችል ስጋቱን ለመቀልበስ እንደ ቴምፐስት ያሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ያስፈልጋሉ ይለሉ።