በደቡብ አፍሪካ በርካታ ታዳጊ ወንዶችን የደፈረው ግለሰብ 12 የዕድሜ ልክ እስራት ተፈረደበት

ገርሃርድ አከርማን

የፎቶው ባለመብት, News 24

ታትሟል

በደቡብ አፍሪካ በርካታ ታዳጊ ወንዶችን የደፈረውና ለወሲብ ንግድ የሸጣቸው ግለሰብ 12 የዕድሜ ልክ እስራት ተፈረደበት።

የጆሃንስበርግ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ገርሃርድ አከርማን በታዳጊዎቹ ላይ አሰቃቂ ጥቃቶችን በመፈጸም ጥፋተኛ ሆኖ አግኝቸዋለሁ ሲልም ነው ይህንን ብያኔ ያስተላለፈው።

ፍርድ ቤቱ ግለሰቡን ጥፋተኛ ሆኖ አግኝቸዋለሁ ካላቸው ወንጀሎች መካከል መድፈር፣ ህገወጥ የህጻናት ዝውውር፣ የወሲብ ብዝበዛ፣ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ታዳጊዎችን ለወሲብ ድርጊቶች መመልመል፣ ህጻናቱን የወሲብ ፊልሞች ማሰራት እና ማሰራጨት ይገኙበታል።

የጆሃንስበርጉ ዳኛ መሃመድ ኢስማኤል 12ቱ የዕድሜ ልክ እስራት በአንድ ላይ እንደሚፈጸምበትም ወስነዋል።

ብያኔውን ያስተላለፉት ዳኛ ለራሱ ጥቅም ሲል ራሱን ጨምሮ በሌሎች ታዳጊ ወንዶች ጥቃት እንዲፈጸምባቸው ያደረገ “ፍጹም በክፋት የተሞላ” ሰው ነው ብለዋል።

አከርማን በግድያ ሙከራ እና በዋነኝነት በወንዶች ህጻናት ላይ በርካታ የወሲብ ጥቃቶችን በመፈጸም ፍርድ ቤቱ ጥፋተኛ ሆኖ ያገኘው ሚያዝያ ወር ላይ ነበር።

አከርማን በጎሮጎሳውያኑ 2018 በጆሃንስበርግ ክለብ ውስጥ በልጅ ላይ በፈጸመው ወሲባዊ ጥቃትም ሌላኛው የተከፈተበት ክስም አሁንም በፍርድ ሂደት ላይ ነው።

የአከርማን ተባባሪ እንደሆነ የተጠረጠረው ሰብዓዊ ተሟጋች እና ዳኛ ፖል ኬኔዲ ባለፈው ዓመት የካቲት ወር የፍርድ ሂደቱ ከመጀመሩ በፊት የራሱን ህይወት አጥፍቷል።

ፖል በህጻናቱ ላይ ወሲባዊ ጥቃት እንዲፈጸምባቸው በማገዝ እና አከርማን የሰጠውንም የኤችአይቪ ቫይረስ የተወሰኑ ህጻናትን በመበከል ክስ ቀርቦበት ነበር።

አከርማን አቅማቸው ደካማ ከሆኑ ቤተሰቦች የተወለዱ ታዳጊ ወንዶችን በማህበራዊ ሚዲያዎች በመልመል ለራሱና ሌሎች ወንዶች ጥቃት እንዲያደርሱባቸው አድርጓል።

አብዛኛዎቹ ወንዶች ታዳጊዎች ዕድሜያቸው ከ14-16 መካከል ነበሩ።

አመኔታቸውን ካገኘ በኋላም በማሳጅ ቤቱ እንዲሰሩና ለወሲብ ንግድና ብዝባዛም ዳርጓቸዋል ተብሏል። በተጨማሪም ታዳጊዎቹ ለወሲብ ንግድ ለበርካታ ደንበኞቹም ተሽጠው ለብዝበዛ መዳረጋቸው ተገልጿል።

በአሁኑ ወቅት የተላለፈውን የእስር ውሳኔም ተከትሎ አከርማን ጠበቃውን አሰናብቷል።

በቀረቡበት ክሶች በሁሉም ነጻ ባይሆንም አብዛኛዎቹን ግን እንዳልፈጸመ የተናገረው አከርማን ክሱ በድጋሚ እንዲታይ ይግባኝ እንደሚጠይቅም ለጋዜጠኞች ተናግሯል።