ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአሜሪካ በስህተት ሎተሪ የወጣለት ግለሰብ የ340 ሚሊዮን ዶላር ክስ መሠረተ
በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ የሚኖር አንድ አሜሪካዊ በስህተት ሎተሪ ደርሶሃል ከተባለ በኋላ የ340 ሚሊዮን ዶላር ክስ የዲሲ ሎተሪ አስተዳደር እና ‘ፓወር ቦል’ የተሰኘው ሎተሪ ድርጅት ላይ አቅርቧል።
ግለሰቡ በእጁ የያዘው የሎተሪ ቁጥር ከአሸናፊው ቁጥር ጋር አንድ ዓይነት የነበረ ቢሆንም ቆይቶ ሎተሪ አስተዳዳሪው ቁጥሩ በስህትት ይፋ እንደሆነ አስታውቋል።
ጆን ቺክስ የተባለው አሜሪካዊ ለመጀመሪያ ጊዜ ባለፈው ጥር ወር የያዘው ‘የፓወርቦል’ ሎተሪ ከአሸናፊው ቁጥር ጋር ሲመሳሰል “በድንጋጤ ደርቄ ቀርሁ” ብሏል።
ሆኖም ቺክስ የሎተሪ ትኬቱን ይዞ ወደ ሎተሪ እና ቁማር ኤጀንሲው ሲያቀና አሸናፊ አይደለህም ተብሏል።
ሰውየው ስለጉዳዩ ለቢቢሲ ሲናገር “አንዱ በኤጀንሲው የተነገረኝ ነገር የያዝከው ሎተሪ ትክክል አይደለም። በቃ፣ ቆሻሻ መጣያ ውስጥ ጣለው” የሚል ነው ብሏል።
ቺክስ ግን ትኬቱን ሳይጥል የሚከራከርለት ጠበቃ አግኝቷል።
ግለሰቡ ለደረሰበት ጉዳት እና ገንዘቡ እጁ ቢገባ በየቀኑ ሊያገኝ የሚችለውን ገቢ በማስላት በአጠቃላይ የ340 ሚሊዮን ዶላር ክስ በኤጀንሲው ላይ መስርቷል።
‘ፓወርቦል’ በቴክኒካዊ ስህተት ምክንያት ያልተገባ ሰው አሸናፊ መባሉን በዲሲ የቀረቡ የፍርድ ቤቶች ሰነድ አመልክቷል።
ቀጥሎም ቺክስ ሎተሪ በገዛበት ወቅት የተቋሙን ድረ ገጽ ደኅንነት የሚያጣራው ቡድን ሙከራዎችን እያከናወነ እንደነበርም ተጠቅሷል።
በዚህም ምክንያት በዚያ ቀን ቺክስ ከያዘው ‘የፓወርቦል’ ሎተሪ ቁጥር ጋር የሚመሳሰል ቁጥር በድረ ገጹ “በድንገት” ወጥቷል ሲል ድርጀቱ መከራከሩን ሰነዶች አሳይተዋል።
ይህ ግለሰቡ አሸናፊ እንደሆነ የሚያሳየው ቁጥር በጥር ወር ውስጥ ለሦስት ተከታታይ ቀናት ድረ ገጹ ላይ ቆይቷል።
ተቋሙ አሸናፊ ነኝ የሚለው ግለሰብ የያዘው ቁጥር በትክክለኛው ሂደት የወጣ አይደለም ብሏል።
ቢቢሲ ለሎተሪ አስተዳዳሪው ስለጉዳዩ ጥያቄ ቢያቀርብም ምላሽ ማግኘት አልቻለም።
ቺክስ የሎተሪ አስተዳዳሪውን ውልን መጣስ፣ ቸልተኝነት፣ የስሜት ጉዳት ማድረስ እና ማጭበርበርን ጨምሮ 8 ክሶችን መሥርቷል።
የሰውዬው ጠበቃ ሪቻርድ ኢቫንስ በችሎት ሰነዶች ላይ ደንበኛው የያዘው ሎተሪ እና አሸናፊው ቁጥር በመመሳሰሉ ሙሉ ሽልማቱ ይገባዋል ሲል አስፍሯል።
በሌላ በኩል ጠበቃ ኢቫንስ ደንበኛው ቺክስ ድርጅቱ በቸልተኝነት የተሳሳተ ቁጥር ለጥፎ ላደረሰበት ጉዳት ሊጠየቅ ይገባልም ብሏል።
ጠበቃው ለቢቢሲ በጽሑፉ በሰጠው መልስ “ይህ ክስ የዲሲ ሎተሪ አስተዳደር እና ፓወርቦልን ጨምሮ በሎተሪ ሥራ ውስጥ ያለውን ተአማኒነት እና ተጠያቂነት ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነው” ብሏል።
“ይህ ነገር ድረ ገጽ ላይ የወጣ ቁጥር ጉዳይ ብቻ አይደለም፣ ከሂደቱ እያተረፉ ሕይወት የሚቀይር ዕድል እናመጣለን የሚሉ ተቋማትን እውነተኝነት ጥርጣሬ ውስጥ የሚከት ነው” ሲልም አክሏል።
ሎተሪ ማሸነፌ የእኔ እና የቤተሰቤን ሕይወት የሚቀይር ነው የሚለው ቺክስ “የፍትህ ሥርዓቱ ድል እንደሚያደርግ አውቃለሁ” ብሏል።
ይህንን ክስ የሚያሸነፍ ከሆነም የቤት ባለቤቶችን ታሳቢ ያደረገ ባንክ የመክፈት ሃሳብ እንዳለውም ጠቁሟል።
ይህንን ክስ የሚመለከተው ችሎት ከሦስት ቀናት በኋላ ባለው ቀጠሮ ጉዳዩን መመርመሩን ይቀጥላል።
ቺክስ በስህተት አሸናፊ ሆኖበታል የተባለውን ያህል ገንዘብ በሎተሪ የማግኘት ዕድል እጅግ በጣም የጠበበ ሲሆን፣ በዚህም ከ292 ሚሊዮን ሰዎች አንድ ሰው የዚህ ዕጣ አሸናፊ ሊሆን ይችላል።
በንጽጽር በአሜሪካ ይህንን ዕድል ከማግኘት ይልቅ በመብረቅ መመታት ይቀርባል ይባላል። በአሜሪካ በሚቀጥለው ዓመት ከ1 ሚሊዮን 200 ሺህ ሰዎች ውስጥ አንድ ሰው በመብረቅ የመመታት ዕድል እንዳለው የአገሪቱ ብሔራዊ የአየር ትንበያ አገልግሎት መረጃ ያሳያል።