ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ውጥረት ለማርገብ ኬንያ ያቀረበችው የባሕር ጠረፍ ስምምነት ሃሳብ የለም አለች

የኬንያ እና የሶማሊያ መሪዎች

የፎቶው ባለመብት, Villa Somalia

የምስሉ መግለጫ, በዚህ ሳምንት በኬንያ ጉብኝት ያደረጉት የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ መሐሙድ ከኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ጋር
ታትሟል

ኬንያ የኢትዮጵያ እና የሶማሊያን ውጥረት ለማርገብ ቀጣናዊ የባሕር ጠረፍ አገልግሎት ስምምነት አማራጭ ለአገራቱ አቅርቤያለሁ ማለቷን ሶማሊያ ውድቅ አደረገች።

ኬንያ አቀረብኩት ያለችው አማራጭ በቀጠናው የሚገኙ የባሕር በር የሌላቸው አገራት በንግድ ስምምነት መሠረት የባሕር መተላለፊያ አገልግሎት እና ጥቅም የሚያገኙበትን ዕድል የሚፈጥር ነው ተብሎ ነበር።

የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ከኬንያ በኩል የተባለው ዓይነት የቀረበ ስምምነት የለም ብሏል።

የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲዔታ ዓሊ ኦማር ባላድ “ሶማሊያ እና ኢትዮጵያን የሚመለከቱ የባሕር ጠፈር ስምምነት ዘገባዎች ሙሉ በሙሉ መሠረተ ቢስ ናቸው” ሲሉ ሚያዝያ 4/2016 ዓ.ም በኤክስ ገጻቸው አስፍረዋል።

አክለውም “ሶማሊያ በግዛት አንድነቷ ላይ እንደማትደራደር” ጠቅሰው “በቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት ላይ ትኩረት እንዲደረግ” ጠይቀዋል።

ኬንያ ከጂቡቲ እና ከምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) ጋር በሚደረገው ምክክር የባሕር በር የሌላቸው አገራትን በንግድ ስምምነት ተጠቃሚ የሚያደርግበት ስምምነት ማቅረቧን የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዋና ፀሐፊ ለሮይተርስ ተናግረው ነበር።

“ኢጋድ የባሕር በር አገልግሎት አጠቃቀም የሚደነግግ ሕግ ማርቀቅ ይችላል” ያሉት ባለሥልጣኑ፣ ኬንያ የምታቀርበው ሃሳብ ተቀባይነትን የሚያገኝ ከሆነ ኢትዮጵያ “አስተማማኝ የባሕር በር አማራጭ ይኖራታል” ሲሉ ኮሪር ሲንጋኦኢ ተናግረዋል።

የ X ይዘትን ይለፉት
ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

ማሳሰቢያ: በሌሎች ገጾች ላይ ላሉ ይዘቶች ቢቢሲ ኃላፊነት አይወስድም።

የ X ይዘት መጨረሻ

እኒህ የኬንያ የውጭ ጉዳይ ከፍተኛ ባለሥልጣን ኬንያ ያቀረበችው አማራጭ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ የሶማሊያን ሉዓላዊ አንድነት የሚያረጋግጥ ይሆናል ብለው ነበር።

ባለፈው ታኅሣሥ መጨረሻ አካባቢ ኢትዮጵያ ራሷን በነጻ አገርነት ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር የወደብ የመግባቢያ ስምምነት መፈረሟን ተከትሎ ነው የሁለቱ አገራት ግንኙነት መቃቃር የተከሰተው።

አሳሪ ያልሆነው የመግባቢያ ስምምነት ኢትዮጵያ ለወደፊቱ የባሕር ኃይል ጣቢያ ማቋቋም የሚያስችላትን 20 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የባሕር ጠረፍ ለማግኘት የሚያስችላት ነው።

ሶማሊያ ግዛቴ ናት በምትላት ሶማሊላንድ ኢትዮጵያ የባሕር ኃይል ጣቢያ ለመገንባት ያቀደችውን ዕቅድ በፍጹም እንደማትቀበል፣ ነገር ግን በሁለትዮሽ ድርድር ለኢትዮጵያ ለንግድ አገልግሎት የወደብ መዳረሻ ፍቃድ ልትሰጥ እንደምትችልም ሚኒስትር ዲዔታው ለሮይተርስ ተናግረዋል።

ወደብን በተመለከተ ወደ ሁለትዮሽ ውይይት ከመገባቱ በፊት ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የገባችውን ስምምነት ማፍረስ አለባት ማለታቸውንም ሮይተርስ ዘግቧል።

“ሶማሊያ የባሕር ኃይል ጣቢያን በፍጹም አትቀበልም። ነገር ግን በዓለም አቀፍ የባሕር ሕግ መሠረት ለንግድ መዳረሻነት ዝግጁ ናት” ብለዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታው ሶማሊያ የአገሪቱን ጥቅም “ሉዓላዊነት፣ የፖለቲካ ነጻነት እና አንድነትን” በጠበቁ ሃሳቦች ላይ ለመወያየት ፈቃደኛ እንደሆኑም ተናግረዋል።

የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዋና ፀሐፊ ኮሪር ኬንያ ያቀረበችውን አማራጭ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ እያጤኑት መሆኑን ገልጸው፤ የቀረበውን አማራጭ ወደፊት ለመውሰድ የሁለቱ አገራት መሪዎች ፊት ለፊት ተገናኝተው እንዲነጋገሩ ጥሪ ቀርቦላቸዋል ብለው ነበር።

ኬንያ አቀረበችው ስለተባለው የባህር ጠረፍ አማራጭ ስምምነት ሶማሊያ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታዋ በኩል ስታስተባብል ከኢትዮጵያ በኩል የተሰጠ ምላሽ የለም።

ኢትዮጵያ ራሷን እንደ ነጻ አገር ካወጀችው እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ካላገኘችው ሶማሊላንድ ጋር 20 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የባሕር ጠረፍ ለማግኘት የፈረመችው የመግባቢያ ሰነድ ሶማሊያን በእጅጉ አስቆጥቶ በቀጠናው ከፍተኛ ውጥረትን ያስከተለ ሆኗል።

ኢትዮጵያ በዚህ ስፍራ የባሕር ኃይል ሰፈር እንደምታቋቁም እና በምትኩ ለሶማሊላንድ ዕውቅና ትሰጣለች መባሉን ተከትሎም እንደ ግዛቷ አካል የምታያት ሶማሊያ ጉዳዩን ወደ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች እስከ መውሰድ አድርሷታል።

ከሶማሊያ በኩል ተደጋጋሚ ክሶች እና መግለጫዎች ከመቅረባቸው በተጨማሪም ጉዳዩን ወደ መንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤትም ወስዳዋለች።

በቅርቡም ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በማቋረጥ የኢትዮጵያ አምባሳደር እና ዲፕሎማቶች ሶማሊያን ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ አስተላልፋለች። በአዲስ አበባ የሚገኙት የሶማሊያ አምባሳደርም ወደ ሞቃዲሾ እንዲመለሱ መታዘዛቸው ይታወሳል።

ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ በታኅሣሥ 22/2016 ዓ.ም. የተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ተፈፃሚነት ወደሚኖረው ስምምነት ተቀይሮ ተግባራዊ እንደሚሆን ዕለት ተገልጾ ነበር።

ይሁንና የመግባቢያ ስምምነቱ ከተፈረመ አራት ወራት ቢያልፉም እስካሁን ድረስ ተፈፃሚነቱ የደረሰበትን ደረጃ በተመለከተ በይፋ የተነገረ ነገር የለም።