ስለጥቁር አሜሪካውያን የሚያወሳው የታሪክ ትምህርት በፍሎሪዳ እንዳይሰጥ ታገደ

የፍሎሪዳ አገረ ገዢ ሮን ዴሳንቶስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የፍሎሪዳ አገረ ገዢ ሮን ዴሳንቶስ
ታትሟል

የአሜሪካዋ ፍሎሪዳ ግዛት ባለሥልጣናት ለሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ስለ ጥቁር አሜሪካውያን ታሪክ የሚያስረዳው ትምህርት እንዳጀመር አገዱ።

የሮን ዴሳንቶስ አስተዳደር እንዳለው፣ ለሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች እንዲሰጥ ሐሳብ የቀረበበት ትምህርት “የዕውቀት ዋጋ የሌለውና ከፍሎሪዳ ሕግ ጋር የሚጻረር” ነው።

ትምህርቱ በሙከራ ደረጃ በመላው አሜሪካ በ60 የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እየተሰጠ ነው።

የፍሎሪዳ የትምህርት ክፍል ለአሜሪካ ኮሌጅ ቦርድ በጻፈው ደብዳቤ ትምህርቱን እንደማይሰጥ አስታውቋል።

“የኮሌጅ ቦርዱ ሕጋዊ እና ትክክለኛ የታሪክ ይዘት ያለው ይዞ ከመጣ ጉዳዩን ዳግመኛ ለመልከት ፈቃደኛ ነን” ይላል ደብዳቤው።

የአፍሪካ አሜሪካውያን ታሪክ የያዘው ትምህርት በቦርዱ የተጀመረ ነው።

ትምህርቱ ሥነ ጽሑፍ፣ የፖለቲካ ሳይንስ እና ጂኦግራፊን ጨምሮ የ400 ዓመታት አፍሪካ አሜሪካውያን ታሪክን የያዘ እንደሆነ ተገልጿል።

ይህ ትምህርት ተማሪዎች ሁለተኛ ደረጃ ከማጠናቀቃቸው በፊት በኮሌጅ ደረጃ ያለ ዕውቀት እንዲጨብጡ ያለመ ነው።

የሪፐብሊካኑ የፍሎሪዳ አገረ ገዢ ሮን ዴሳንቶስ ቢሮ ባወጣው መግለጫ ትምህርቱ “በሌሎች ትንታኔዎች ሊሞሉ የሚችሉ አሻሚ ክፍተቶች አሉት። ይህን ደግሞ አንፈቅድም። የኮሌጅ ቦርዱ ትምህርቱን ካሻሻለ እና ሙሉውን ሥርዓተ ትምህርት ካመጣ ፈቃድ ሊሰጠው ይችላል” ብለዋል።

የኮሌጅ ቦርዱ በምላሹ “ከመምህራን፣ ተማሪዎች እና ፖሊሲ አውጭዎች በሚሰጥ አስተያየት መሠረት ትምህርቱ በየዓመቱ ማሻሻያ ይደረግበታል። የአፍሪካ አሜሪካውያን የዳበረ እና አነቃቂ ታሪክ ከሁሉም ባህል ለመጡ ተማሪዎች እንዲሰጥ እንፈልጋለን” ብሏል።

ብሔራዊ የተማሪዎች ወላጆች ማኅበር ትምህርቱ እንዲታገድ መወሰኑ “ለሁሉም አሜሪካዊ ቤተሰብ አስጊ አካሄድ ነው” ብሏል።

ዴሞክራቱ የፍሎሪዳ ሴናተር ሸቭሪን ጆንስ የአውሮፓ ታሪክ፣ ሌሎች ቋንቋዎች እና ባህሎች ትምህርት እየተሰጠ መሆኑን ጠቅሰው ውሳኔውን ተቃውመዋል።

ባለፈው ዓመት አገረ ገዢው ያሳለፉት ውሳኔ ስለ ዘር እና ሥነ ጾታ ትምህርት የሚሰጥበትን መንገድ የሚገድብ ነው።

የአፍሪካ አሜሪካ ታሪክ ትምህርትን ካረቀቁት አንዱ ለታይም መጽሔት እንደተናገሩት ትምህርቱ “በተገቢው ሥርዓት የተቀረጸና ምሁራዊ” ነው።