ባሌ ውስጥ አንዱን ልጁን ገድሎ ሌላውን ከነሕይወቱ የቀበረው አባት ሞት ተፈረደበት

በኦሮምያ ባሌ ዞን መደወላቡ ወረዳ ሁለት ልጆቹን በአሰቃቂ ሁኔታ ገድሎ የቀበረው አባት ሞት ተፈረደበት።

የፎቶው ባለመብት, iStock

ታትሟል

በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን ውስጥ መደወላቡ ወረዳ ሁለት ልጆቹን በአሰቃቂ ሁኔታ ገድሎ የቀበረው አባት በሞት እንዲቀጣ ተፈረደበት።

የባሌ ዞን ዐቃቤ ሕግ የሆኑት አቶ ከድር አብዳ ለቢቢሲ አንደተናገሩት ግድያው የተፈፀመው ከሦስት ሳምንታት በፊት ታኅሣሥ 24/2015 ዓ.ም. ነው።

የአምስት ልጆች አባት የሆነው እና እድሜው በ30ዎቹ ውስጥ የተገመተው አቶ መሐመድ አብድራህማን ሁለት ልጆቹን መግደሉን አምኖ፣ እምነት ክህደት ቃሉን ለፖሊስ መስጠቱን ዐቃቤ ሕጉ ተናግረዋል።

አቶ መሐመድ የሰባት እና የስድስት ዓመት ልጆቹን በገደለበት ማለዳ ከብት ለመጠበቅ በማለዳ አብረውት ከቤት የወጡ ቢሆንም፣ ነገር ግን ምሽት ላይ ብቻውን ወደ ቤት መመለሱን ዐቃቤ ሕጉ የክስ መዝገቡን በመጥቀስ አስረድተዋል።

ዘይዲን እና አራርሶ የተባሉት ታዳጊ ልጆቹን ሳይዝ ወደ ቤቱ የተመለሰው አባት “ማታ ወደ ቤት ሲመለስ ልጆቹን ከአጠገቤ አጣኋቸው” በማለት ለሚስቱ ተናግሯል።

ከዚህ በኋላ የአካባቢው ነዋሪዎች እና ዘመዶቻቸው በጋራ በመሆን ከብት ሊያግዱ ወጥተው ወደ ቀያቸው ያልተመለሱትን ሕጸናት ፍለጋ ጀመሩ።

ይህ ፍለጋ ለሳምንት ያህል የቀጠለ ነበር።

በዚህ ሁኔታ ውስጥ የአካባቢው ሰው አባትየውን መጠርጠር ጀመረ።

ይህ ጥርጣሬ የመጣው አባት ሲያሳይ ከነበረው ባህርይ በመናሳት መሆኑን ዐቃቤ ሕጉ አቶ ከድር ያስረዳሉ።

“እየፈለጉ ባለ ጊዜ የአካባቢው ሰው ልጆቹ ወደ የተቀበሩበት ስፍራ ሲደርሱ ወደዚያ አካባቢ እንዳይሄድ ይከላከል ነበር።”

የፖሊስ የምርመራ መዝገብ እንደሚያስረዳው የልጆቹ አስከሬን የተገኘው ግድያው ከተፈፀመ ከአንድ ሳምን በኋላ፣ ጥር 02/2015 ዓ.ም. ነው።

“የአካባቢው ሰው ልጆቹን በሚፈልግበት ጊዜ መጥፎ ሽታ ያለብት ጉድጓድ አገኘ። ጉድጓዱ ሲቆፈር የልጆቹ አስከሬን ተገኘ።”

ማኅበረሰቡ በልጆቹ ግድያ አባታቸውን እንደሚጠረጥሩ በመግለጽ ለፖሊስ ጥቆማ እንደሰጠ የመደወላቡ አካባቢ ዐቃቤ ሕጉ ይናገራሉ።

የሕግ አካላትም ጥቆማውን መሠረት በማድረግ ምርመራ በሚያደርጉበት ወቅት ተጠርጣሪው ድርጊቱን መፈፀሙን ማመኑን አቶ ከድር ገልፀዋል።

“አባት የእምነት ክህደት ቃል በሚሰጥበት ጊዜ፣ ‘እኔ ነኝ የገደልኳቸው’ አለ። አገዳደሉንም አንድ ሁለት ብሎ በዝርዝር አስረዳ” ብለዋል።

አባት ልጆቹን እንዴት ሊገድል ቻለ?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አቶ መሐመድ አብድራህማን ልጆቹን በአሰቃቂ ሁኔታ መግደሉን ለፖሊስ ከሰጠው ቃል መረዳት ይቻላል ይላሉ ዐቃቤ ሕጉ።

አቶ ከድር ተጠርጣሪው ያመነውን ሲያብራሩ “የሰባት ዓመት ልጁን በመጥረቢያ ሁለት ጊዜ መትቶ ከወደቀ በኋላ አዋልድጌሳ (የዱር አውሬ) በቆፈረው ጉድጓድ ውስጥ ከተተው። በመቀጠልም ሁለተኛውን ልጅ በሕይወት እያለ ጭንቅላቱን ደፍቆ እዚያው ጉድጓድ ውስጥ መክተቱን ተናግሯል።”

በልጆቹ ግድያ ጥፋተኛ የተባለው አባት እንደተናገረው አንዱን ልጁን ገድሎ ሌላኛውን ደግሞ በሕይወት እያለ መቅበሩን ለፖሊስ ማመኑ ተገልጿል።

አባት ከዚህ በፊት የተለየ ባህሪ ያሳይ እንደሆነ ወይንም ይህንን ወንጀል አንዲፈጽም ያደረገው የተለየ ምክንያት ይኖር እንደሆን የተጠየቁት ዐቃቤ ሕግ ከድር፣ ምንም የተለየ ነገር ምክንያት እንዳልተገኘ ተናግረዋል።

በተጨማሪም የአእምሮ ጤናው ሁኔታን የተጠየቁት ዐቃቤ ሕጉ “አእምሮው ጤነኛ ነው” በማለት የመለሱ ሲሆን፣ በምርመራ ወቅትም ምንም የተለየ ነገር አንዳልተገኘ ተናግረዋል።

ይህንን ጉዳይ ሲከታተል የነበረው የጤና ባለሙያም ለግድያው ምክንያት ሊሆን ይችላል ብሎ ያለው ምንም ነገር የለም ሲሉ አክለዋል።

የአቶ መሐመድ የእምነት ክህደት ቃሉን በሚሰጥበት ወቅት እንደተናገረው ከሆነ ግድያውን በፈፀመበት ወቅት ተናድዶ ነበር።

“ከባለቤቱ ጋር ተጋጭቶ ስለነበር በዚያ ንዴት ልጆቹን መግደሉን ተናግሯል” ሲሉ ዐቃቤ ሕጉ ለቢቢሲ አስረድተዋል።

“ያንተ ጓደኞች ከአጠገብህ ቤት ሰርተው አሉ። አንተ ግን እዚህ ድህነት ውስጥ ጥለኽን ነው ያለኽው ስላለችኝ ተናድጄ ይህንን እርምጃ ልወስድ ችያለሁ” ብሎ ለፖሊስ መናገሩን አቶ ከድር ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ይህ ጉዳይ ወደ ፍትህ አካላት ከደረሰ በኋላ ለባሌ ዞን ዐቃቤ ሕግ ጉዳዩ ተልኮ በግለሰቡ ላይ፣ ከባድ የሰው ሕይወት ማጥፋት ክስ ተመስርቶበታል።

ዐቃቤ ሕግ በ1996 የወጣውን የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ አንቀጽ 539/1 በመጥቀስ በጠየቀው ቅጣት መሠረት ፍርድ ቤቱ በግለሰቡ ላይ ፍርድ መስጠቱን ገልጸዋል።

የተከፈተበትን ክስ ተከሳሽ ሙሉ በሙሉ በማመኑ ፍርድ ቤቱ ጥር 10/2015 ዓ.ም. የጥፋተኝነት ውሳኔ አስተላልፏል።

“የገዳይን ጭካኔ፣ የተበዳዮችን ሕጻናት መሆን እንዲሁም የተገደሉበትን መንገድ ግምት ውስጥ በማስገባት የሞት ፍርድ ተሰጥቷል።”

የሞት ፍርድ የተፈረደበት አባትም በፈጸመው ከባድ ወንጀል ምንም ዓይነት “የመፀፀት ስሜት” አላሳየም ይላሉ የሕግ ባለሙያው።