ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኡጋንዳ በኢቦላ ምክንያት ሕይወታቸው ያለፈ የጤና ባለሙያዎች ቁጥር ጨመረ
የኡጋንዳ የጤና ሚንስቴር ተጨማሪ የጤና ባለሙያ ሕይወት በኢቦላ ምክንያት ማለፉን አስታወቀ።
የ58 ዓመቷ ማርጋሬት ናቢሱቢ የማደንዘዣ ባለሙያ ስትሆን በኢቦላ ምክንያት ሕይወቷ ያለፈ አራተኛ የህክምና ባለሙያ መሆኗን የጤና ሚንስትሩ ዶ/ር ጄን ሩት አሴንግ ተናግረዋል።
የህክምና ባለሙያዎች በኢቦላ መያዙ የተረጋገጠ የመጀመሪያውን የኢቦላ ታማሚ ሲያክሙ ነበር ለቫይረሱ ተጋላጭ የሆኑት። ይህ ታካሚው ቀዶ ሕክምና አስፈልጎት ነበርም ተብሏል። ከግለሰቡ ጋር ንክኪ የነበራቸው የጤና ባለሙያዎች በፎርት ፖርታል ሆስፒታል ህክምና እየተከታተሉ ነው።
የጤና ባለሙያዎቹ ቡድኑ አባል የነበረው ታንዛኒያዊ የህክምና ተማሪ ከቀናት በፊት ሕይወቱ አልፏል።
ከዚህ ጋር ግንኙነት የሌለው የህክምና ባለሙያ በካጋዲ ግዛት ህይወቱ አልፏል።
በሙቤንዴ ግዛትም አንዲት አዋላጅ ነርስ ሕይወቷ ያለፈ ሲሆን ህይወቷ ያለፈው በኢቦላ ሊሆን ይችላል የሚል ጥርጣሬ። ሕይወቷ ያለፈው ከምርመራ በፊት ነው።
ቫይረሱ በተከሰተባቸው የመጀመሪያ ቀናት የህክምና ባለሙያዎች የመከላከያ ለብስ እጥረት እንደነበረባቸው ተገልጿል።
በኦፊሴላዊ መንገድ እንደተገለጸው ከሆነ ቫይረሱ መከሰቱ ከተነገረ ባለፉት ሁለት ሳምንታት 43 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ 10 የሚያህሉት ሕይወታቸው አልፏል።
ቫይረሱ ካለባቸው ሰዎች ጋር ንክኪ ነበረባቸው የተባሉ 800 ያህል ሰዎች መለየታቸውም ተገልጿል።