ጥቁር አሜሪካዊው በፖሊስ በ60 ጥይት የተገደለበት ቪዲዮ ይፋ ሆነ

ታትሟል

የአሜሪካ ፖሊስ በኦሃዮ ግዛት ውስጥ አንድ ጥቁር በፖሊሶች በ60 ጥይት ተደብድቦ የተገደለበትን ቪዲዮ ይፋ አደረገ።

ጄይላንድ ዎከር የተባለው የ25 ዓመት ወጣት ምሽት ላይ በፖሊሶች እንዲቆም ሲደረግ ቀድሞ ተኩስ መክፈቱን እና ፖሊሶችም ለደኅንነታቸው እንደሰጉ ተገልጿል።

ነገር ግን ዎከር ከመኪናው ወርዶ ከፖሊሶች በሩጫ ሲሸሽ ምንም አይነት መሳሪያ ያልያዘ ሲሆን በኋላ ላይ ግን ሽጉጡ መኪናው ውስጥ ተገኝቷል።

ይህንን ተከትሎም ክስተቱ ያጋጠመባት ከተማ አክሮን ውስጥ ተቃውሞ በመጀመሩ ከንቲባዋ ነዋሪዎች ትዕግስት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

የቪዲዮውን ይፋ መሆን ተከትሎ "ቪዲዮው ልብን የሚሰብር ነው፣ ለመቀበል በጣም ይከብዳል" ሲሉ ከንቲባ ዳኒኤል ሆሪጋን ተናግረዋል።

የኦሃዮዋ ከተማ አክሮን፣ ፖሊስ አባላቱ ሕግና ደንብ ጥሰው እንደሆነ ለማወቅ የራሱን ምርመራ እንደሚያደርግ ሲያሳውቅ፣ የግዛቲቱ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዴቭ ዮስት በክስተቱ ዙሪያ “የተሟላ፣ ፍትሃዊ የባለሙያዎች” ምርመራ እንደሚደረግ አመልክተዋል።

በግድያው ውስጥ ተሳትፈዋል ከተባሉት ስምንት ፖሊሶች መካከል ሰባቱ ነጮች፣ አንዱ ደግሞ ጥቁር ሲሆን፣ ሁሉም አስተዳዳራዊ እረፍት እንዲወጡ ተደርገዋል።

የሟች ቤተሰብ ጠበቃ እንደተናገሩት፣ የፖሊስ መኮንኖቹ ጄይላንድ ዎከር ተመትቶ ወድቆ እንኳን መተኮሳቸውን አላቆሙም ብለዋል።

የጥቁሮች መብት ብሔራዊው ማኅበር ፕሬዝዳንት የሆኑት ዴሪክ ጆንሰን፣ ክስተቱን “በቅርብ ርቀት የተፈጸመ ግልጽ ግድያ” ሲሉ ገልጸውታል።

ባለፈው ሳምንት ሰኞ የጄይላንድ ዎከር መኪና የትራፊክ መቆጣጠሪያ ላይ ቆሞ ነበር።

ከዚያም ከመኪናው ውስጥ ተኩስ የተሰማ ሲሆን የትራፊክ ካሜራም የታየውን የእሳት ፍንጣቂ ቀርጾ ማስቀረቱን አሶሼትድ ፕረስ የዜና ወኪል የአክሮን ፖሊስ አዛዥ ስቲቭ ሚይሌት ጠቅሶ ዘግቧል።  

የፖሊስ ካሜራ ቀርጾ ያስቀረው ምስል፣ አንድ ጭምብል ያጠለቀ ግለሰብ ከመኪናው ውስጥ ሲወጣና ወደ መኪናው ማቆሚያ ሥፍራ ሲሮጥ እና ፖሊሶች ተኩስ ከመክፈታቸው አስር ሰከንዶች ቀደም ብሎ ሲከታተሉት ያሳያል።

ግለሰቡን ለመያዝ መጀመሪያ ላይ አንድ ፖሊስ በኤሌክትሪክ የሚሰራ ራስን መከላከያ መሣሪያ የተጠቀመ ቢሆንም ውጤታማ አለመሆኑን ፖሊስ ተናግሯል።

የፖሊስ አዛዡ ሚይሌት “ከቪዲዮው ላይ የተገኘው አንደኛው ምስል ዎከር  ወገቡን ሲነካካ፣ ሌላኛው ደግሞ ወደ ፖሊስ መኮንኖች ሲዞር እና ሦስተኛው ምስል እጁን እያንቀሳቀሰ ወደ ፊት ሲሄድ ያሳያል” ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በመኪናው መቀመጫ ወንበር ላይ ሽጉጥ የተገኘ ሲሆን በአካባቢው የተገኘው ቀለሃ ከሽጉጡ ጋር ተመሳሳይ መሆኑን ፖሊስ ገልጿል።

ቪዲዮው ከተለቀቀ በኋላ ተቃዋሚ ሰልፈኞች በአክሮን ከተማ ፍትሕ ማዕከል ፍት ለፊት በመሰባሰብ በሰላማዊ መንገድ ተቃውሟቸውን እያሰሙ ነው።

የሟች ቤተሰብ ጠበቃ የሆኑት ቦቢ ዲሴሎ እንዳሉት ፖሊስ ዎከር መሬት ላይ ከወደቀ እና እጁ ከታሰረ በኋላ የመጀመሪያ ሕክምና እርዳታ እንኳን ሳይሰጡት ደጋግሞ ተኩሶበታል።

የዎከር ቤተሰቦች ለሲቢኤስ ኒውስ በሰጡት መግለጫ “ ቁጣ ምንም ማለት አይደለም። ይህንን መረዳት እንችላለን።ጥቃት ግን ልንቀበለው አንችልም። ፍትሕ በመጠየቅ ለጄይላንድን ሕይወት ክብር እንስጥ “ ብለዋል።