የሳርስን ቀውስ ያጋለጡት ቻይናዊ ዶክተር አረፉ

ታትሟል

ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት በቻይና የተከሰተውን የሳርስ ወረርሽኝ ያጋለጡት ዶክተር ጂያንግ ያንዮንግ በ91 ዓመታቸው አረፉ።

የቀድሞ ወታደራዊ የቀዶ ጥገና ሐኪም የነበሩት ጂያንግ የቻይና ባለስልጣናት የሳርስ ወረርሽኝን ለመሸፋፈን ሲሞክሩም ነው ይፋ ያወጡት።

ቅዳሜ ዕለት በቤጂንግ በሳንባ ምች ህይወታቸው ማለፉን ቤተሰቦቻቸው እንዲሁም በሆንግ ኮንግ የሚገኝ የሃገሪቱ ሚዲያ ዘግቧል።

የሳርስ ወረርሽኝ በተነሳበት በመጀመሪያው ወቅት የቻይና ባለስልጣናት ስጋቱን እያጣጡሉትና ሃሰተኛ መረጃ እየሰጡ መሆኑን ደብዳቤ መጻፋቸውንም ተከትሎ ዶክተሩ ከፍተኛ ምስጋና ተችሯቸዋል።

ይህንንም ተከትሎ ዶክተሩ በቻይና የቤት እስርም ገጥሟቸው ነበር።

የሳርስ ወረርሽኝ በአውሮፓውያኑ 2003 ከ8 ሺህ በላይ ሰዎችን ሲያጠቃ ከእነዚህም ውስጥ 774ቱ መሞታቸውን የዓለም ጤና ድርጅት አኃዝ ያሳያል።

ዶክተር ጂያንግ በወቅቱ በቤጂንግ ሆስፒታል ውስጥ ነበር የሚሰሩት። የቻይና የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አዲስ የመተንፈሻ ህመም እንደተከሰተና የታመሙ ሰዎች ቁጥርም አነስተኛ ነው በማለት ማስታወቁንም ተከትሎ ነው በዶክተሩ ላይ ስጋት ያጫረባቸው።

ዶክተሩ በወታደራዊ ሆስፒታል ክፍሎች ብቻ ከ100 በላይ በሳርስ ህመም መጠቃታቸውንም ተናገሩ።

ባለስልጣናቱ ህመሙን ቸል እንዳሉትና፤ ለመደበቅም እየሞከሩ ነው በማለት ለቻይና የመንግሥት ሚዲያዎች ደብዳቤ ጻፉ።

ደብዳቤው በአንድ የውጭ ሚዲያ እጅ በመግባቱ ሙሉ ይዘቱ ይፋ ሆነ። የዶክተሩ ማጋለጥንም ተከትሎ የቻይና መንግሥት ሃሰተኛ መረጃ መስጠቱን አምኖ የዓለም የጤና ድርጅትም ወደ ተግባር እንዲገባ ጠይቋል።

ጥብቅ የቁጥጥር እርምጃዎች በአፋጣኝ የተጣሉ ሲሆን ይህም የቫይረሱ ስርጭት እንዲገታ አድርጎታል።

በዚህም በወቅቱ የቻይና የጤና ጥበቃ ሚኒስትር እና የቤጂንግ ከንቲባ እንዲባረሩም ምክንያት ሆኗል።

“ቻይናን ለማዳን ብቻ ሳይሆን አለምንም ለማዳን ምን እየተከናወነ እንደሆነ መግለጥ እንዳለብኝ ተሰማኝ” ሲሉም ዶክተር ጂያንግ ተናግረው ነበር።