ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሂሩት እና ለሜቻ በሮም ዳይመንድ ሊግ ደምቀው አመሹ
ትላንት ስኔ 2/2014 ዓ.ም. ምሽት በተካሄደ የዳይመንድ ሊግ ውድድር ኢትዮጵያዊያኑ ሂሩት መሸሻ እና ለሜቻ ግርማ አሸናፊ ሆነዋል።
በተለያዩ ከተሞች በዙር የሚከናወነው የዳይመንድ ሊግ ውድድር ትናንት በጣሊያኗ ሮም ተከናውኗል።
በምሽቱ ውድድር በሴቶች 1500 ሜትር ሂሩት መሸሻ ወድድሩን በበላይነት አጠናቃለች።
ሂሩት ውድድሩን 4 ደቂቃ 03.79 በመጨረስ ቀዳሚ ሆናለች።
አክሱማዊት አምባዬ በአንድ ሰከንድ ዘግይታ ውድድሩን በሁለተኛነት አጠናቃለች።
ሂሩት የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ናት።
በዓለም አቀፍ የቤት ውስጥ ሻምፒዮና ደግሞ ነሐስ ሜዳሊያ ማጥለቅ ችላለች።
ለሜቻ ግርማ ደግሞ በወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል ውድድር ነው አሸናፊ የሆነው።
ለሜቻ ውድድሩን ለማጠናቀቅ 7 ደቂቃ 59.23 ሰከንድ ፈጅቶበታል።
ለሜቻ ባለፉት አስር ቀናት በኦስትራቫ፣ ራባት እና ሮም ያደረጋቸውን ውድድሮች በሙሉ ከስምንት ደቂቃ በታች ማጠናቀቅ ችሏል።
ኬንያዊው አብረሃም ኪብዎት ሁለተኛ ሆኖ ውድድሩን ፈጽሟል።
ጌትነት ዋለ ሦስተኛ ሆኖ የትላንት ምሽቱን ውድድር አጠናቋል።
ለሜቻ በቶኪዮ ኦሎምፒክ እና በዓለም ሻምፒዮና የብር ሜዳሊያ ማሳካት ችሏል።
በዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮናም ሁለተኛ ሆኖ ማጠናቀቅ የቻለ አትሌት ነው።
በአምስት ሺህ ሜትር የወንዶች ውድድር ኬንያዊው ኒኮላስ ኪፕኮሪር አሸናፊ ሆኗል።
የሃገሩ ልጅ ጃኮፕ ክሮፕ ደግሞ ሁለተኛ ሆኖ አጠናቋል።
ዮሚፍ ቀጄልቻ ውድድሩን ሦስተኛ ሆኖ ጨርሷል።
ሰለሞን ባረጋ አራተኛ ሲወጣ ጥላሁን ሃይሌ እና ሙክታር እንድሪስ ስድስተኛና ሰባተኛ ሆነው አጠናቀዋል።
በ800 ሜትር የተወዳደረችው ፍሬወይኒ ሃይሉ አምስተኛ ሆና ውድድሩን ጨርሳለች።
ዳይመንድ ሊግ በ2010 ተጀመረ ውድድር ነው።
ውድድሩ ጎልደን ሊግ የተሰኘውን ውድድር ተክቶ ነው መካሄድ የጀመረው።
በተለያዩ ከተሞች ለአንድ ቀን ብቻ የሚሄድ ውድድር ዓይነት ነው።
የውድድሩ አሸናፊዎች በተለያዩ ከተሞች በሚያስመዘግቡት ውጤት ዳጎስ ያለ ሽልማት ይበረከትላቸዋል።
ቀጣዩ አስተናጋጅ የኖርዌይዋ ኦስሎ ስትሆን ውድድሩ ከሳምንት በኋላ ይከናወናል።