የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ኪየቭን ሊጎበኙ ነው

የዩናይትድ ኪንግደሙ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የዩክሬን ፕሬዚዳንት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር አንዲ በርንሃም እና የዩክሬኑ መሪ ቮሎድሚር ዜሌንስኪ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር አንዲ በርንሃም ሰኞ ዕለት ኪየቭን እንደሚጎበኙ እና አገራቸው ለዩክሬን የምታደርገውን ድጋፍ እንደምትቀጥል እንደሚያረጋግጡ ተገለጸ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀደም ብሎ በዩኬ እና በፈረንሳይ በተቋቋመው "የፈቃደኞች ጥምረት" ላይ በመገኘት የመጀመሪያ ስብሰባቸውን ያደርጋሉ።

በተጨማሪም ዩናይትድ ኪንግደም ለዩክሬን ላደረገችው ድጋፍ እውቅና ለመስጠት የተዘጋጀውን ሽልማት የሚቀበሉ ሲሆን በነጻነት ቀን በዓል ዝግጅቶች ላይ ይሳተፋሉ ተብሏል።

በርንሃም ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ የተጠናከረውን የሩሲያ ጥቃት ምክንያት በማድረግ ዩናይትድ ኪንግደም ለዩክሬን የምታደርገውን ድጋፍ በድጋሚ ያረጋግጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ሩሲያ አርብ ዕለት በዩክሬን የገበያ ማዕከል ላይ በፈጸመችው መጠነ ሰፊ ጥቃት ቢያንስ 16 ሰዎችን ገድላለች።

በርንሃም ሰኞ ዕለት ከሚያደርጉት ጉብኝት አስቀድሞ "በዩክሬን 35ኛ የነጻነት በዓል ዕለት የዩክሬን ሕዝብ ምንም ጥርጣሬ እንዳይገባው። ዩኬ ዛሬም፤ ወደፊትም ከጎናችሁ ናት።" ብለዋል።

"አገራችን ለዩክሬን ባበረከተችው አስተዋጽኦ እኮራለሁ፤ የዩክሬን ሕዝብም ድጋፋችን እንደማይናወጥ በቀጥታ ከእኔ እንዲሰማ እፈልጋለሁ። ከሁሉም በላይ የዩክሬን ደኅንነት የእኛ ደኅንነት ነው።"

ዩክሬን ከዩኬ ጋር ያላት ወዳጅነት "ከሩሲያ ሕገ ወጥ ጦርነት የሚያልፍ መሆኑን" ጨምረው ተናግረዋል። "ሩሲያ በቁርጠኝነታችን ላይ ጥርጣሬ ሊኖራት አይገባም። ፍትሃዊ እና ዘላቂ ሰላም እስኪኖር ድረስ ወደኋላ አንልም።"

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ዩክሬን በቅርቡ በሩሲያ መሠረተ ልማቶች ላይ በፈጸመችው ጥቃት የብሪታንያ ድሮኖች መጠቀሟን የገለጸችው ሞስኮ፣ ይህም "መዘዞችን" እንደሚያስከትል አስጠንቅቃለች።

ኪየቭ በሞስኮ እና በሌሎች የሩሲያ ግዛቶች የረዥም ርቀት ተወንጫፊዎችን በመጠቀም ጥቃቶችን ፈጽማ የአገሪቱ ትልቁ የኦንላይን መሸጫ የሆነውን ዋይልድቤሪስን፣ የነዳጅ ማጣሪያዎችን እና መጋዘኖችን ደብድባለች።

በዩኬ የሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ ብሪታንያ "የዩክሬን ቀውስ እንዲባባስ ሆን ብላ እየሰራች ነው" ሲል ከስሷል፣ "በግጭቱ ውስጥ የምትሳተፍበት ጥልቀት በጨመረ ቁጥር . . . የምትከፍለው ዋጋ ከፍ ያለ ነው" ሲልም አስጠንቅቋል።

በርንሃም ባለፈው ሳምንት ለዚህ ዛቻ ምላሽ ሲሰጡ "እኛ የመልካም ጊዜ ወዳጆች ብቻ አይደለንም፤ ዩክሬን በምትፈልገን ሰዓት ሁሉ እንገኛለን። ይህ አይለወጥም።" ብለዋል።

ማክሰኞ ዕለት ስለሩሲያ ስጋት ሲጠየቁ፣ በርንሃም እንግሊዝ "ዩክሬን ራሷን እንድትከላከል ድጋፍ እየሰጠች ነው።" ሲሉ አብራርተዋል።

አክለውም የዩኬ አቋም በቀደሙት ጠቅላይ ሚኒስትሮች ሆነ አሁን ተመሳሳይ መሆኑን ገልጸዋል።

በርንሃም ማክሰኞ ዕለት የሩሲያን ማስፈራሪያ በተመለከተ ተጠይቀው ዩኬ "ለዩክሬን ድጋፍ እያደረገች ነው፤ ስለዚህ ራሷን እየተከላከለች ነው። በግጭቱ ውስጥ ሁሉ ይህ የዩኬ አቋም ነው፤ ከዚህ ቀደም በነበሩ ጠቅላይ ሚኒስትሮችም የነበረው ነው የሚቀጥለው።" ብለዋል።

በብሪታንያ ሁለት የተለያዩ ኩባንያዎች የተሰሩት ድሮኖች በሩሲያ ውስጥ በተፈፀመው መጠነ ሰፊ እና ስኬታማ የሆኑ ወታደራዊ እንዲሁም የነዳጅ ማጣሪያዎችን፣ መጋዘኖችን እና የኦንላየን ጅምላ አከፋፋይ የሆነውን ዋይልድቤሪስን ጨምሮ የኢንደስትሪ ዒላማዎችን ለመምታት ጥቅም ላይ ውለዋል።

ዩክሬን የሩሲያው አማዞን የሚባለውን የኦንላየን ገበያ ድርጅት በተደጋጋሚ ዒላማ ያደረገች ሲሆን በአገሪቷ ካሉ አስር ትላልቅ የድርጅቱ የሎጂስቲክስ ማዕከላት ሰባቱ ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን ገልጻለች።

በእነዚህ 35 ቢሊዮን ዶላር የኢኮኖሚ ጉዳት አድርሰዋል በተባሉ ጥቃቶች የዩኬ ድሮኖች ጥቅም ላይ መዋላቸውን ወታደራዊ ምንጮች ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ሩሲያ በዩክሬን ላይ ሙሉ ወረራ የከፈተችው ከአራት ዓመታት በፊት ሲሆን አሁን ላይ አንድ አምስተኛውን የዩክሬን ክፍል ተቆጣጥራ ትገኛለች።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ ቃል አቀባይ ማሪያ ዛክሃሮቫ፣ በሮስቶቭ ክልል የሚገኘውን የነዳጅ ማከማቻ ጨምሮ የሩሲያን ግዛት ለማጥቃት የዩኬ ሰራሽ ድሮኖች ጥቅም ላይ ውለዋል ብለዋል።

ሞስኮ ለዩኬ ማስጠንቀቂያ የሰጠችውም ዩክሬን በሩሲያ ላይ ተከታታይ ጥቃት ከፈፀመች በኋላ ነው።