ለመታደም እስከ 100 ሺህ ብር የሚከፈልባቸው የፍልሚያ ውድድሮች እንዴት ትኩረት መሳብ ቻሉ?

የማርሻል አርት ተወዳዳሪዎች በሪንግ ውስጥ ሆነው

የፎቶው ባለመብት, johnnydoesjiujitsu

የምስሉ መግለጫ, ዮሐንስ (ጆኒ ጂዩ-ጂትሱ) ከሦስት ዓመት በፊት ብራዚሊያን ጂዩ-ጂትሱን መሠልጠን ሲጀመር እንደዚህ ዓይነት ውድድር ወደፊት እንደሚያዘጋጅ እርግጠኛ እንደነበር ይናገራል
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 6 ደቂቃ

በኢትዮጵያ የማርሻል አርት ውድድሮች አዲስ አይደሉም። በተወዳዳሪዎች፣ በአሠልጣኞች እና በስፖርቱ ቤተሰቦች ዘንድ ለዓመታት ይታወቃሉ።

ነገር ግን ላለፉት 27 ዓመታት ሲዘወተሩ ከስፖርቱ ወዳጆች አልፈው ወደ ሕዝብ መግባት የሚችሉበት ዕድል እምብዛም አልነበራቸውም።

እንደ ቦክስ፣ ሬስሊንግ (ነጻ ትግል)፣ ሙአይ ታይ እና ብራዚሊያን ጂዩ-ጂትሱ ዓይነት የፍልሚያ ስፖርቶችን አንድ ላይ አጣምሮ ተወዳዳሪዎችን የሚያፋልመው ድብልቅ ማርሻል አርት (Mixed Martial Art) ግን በቅርቡ በብዙዎች ዘንድ የተለየ ትኩረት መሳብ ጀምሯል።

በተለይም እንደ ቲክቶክ ያሉ የማኅበራዊ ሚዲያዎች መስፋፋት፣ ተጋጣሚዎችን እና ውድድሮችን ከተለመደው የስፖርቱ ተመልካች ውጪ ላለው ሕዝብ ለማድረስ አዲስ መድረክ ፈጥሯል።

ታዋቂ ሰዎች እና ተጽዕኖ ፈጣሪዎችም ስፖርቱን በማስተዋወቅ ግጥሚያው የሚሰጠው ትኩረት እንዲጨምር አድርገዋል።

በዚህም ምክንያት በሺዎች የታደሙበት ትልቅ የድብልቅ ማርሻል አርት ውድድር ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ላይ በአድዋ ሙዚየም ተካሄዷል።

በቅርቡም ኢትዮጵያን ፋይት ሻምፒዮንሺፕ እና ኢትዮ ፋይት ናይት በሚል የተሰየሙ ሁለት ውድድሮች በተለያዩ ጊዜያት ለመካሄድ ቀን ተቆርጦላቸዋል።

ስለድብልቅ ማርሻል አርት በጥቂቱ

ድብልቅ ማርሻል አርት (Mixed Martial Arts) አንድ ዓይነት የፍልሚያ ስፖርት ሳይሆን፣ የተለያዩ የፍልሚያ ስፖርቶችን እና የፍልሚያ ቴክኒኮችን የሚያጣምር ስፖርት ነው።

ሙአይ ታይ እና ኪክ ቦክሲንግ ቡጢ እና የእግር ምትን የሚጠቀሙ የፍልሚያ ስፖርቶች ሲሆኑ፣ ሙአይ ታይ በተጨማሪ ክርን እና ጉልበትንም ይጠቀማል።

በሌላ በኩል፣ ነጻ ትግል እና ጂዩ-ጂትሱ ተጋጣሚን በመያዝ፣ መሬት ላይ በመጣል እና በመሬት ላይ በመቆጣጠር ላይ የሚመሠረቱ የፍልሚያ ስፖርቶች ናቸው። በተለይም በጂዩ-ጂትሱ፣ ተጋጣሚን በቴክኒክ በመቆጣጠር እጅ እንዲሰጥ ማድረግ የፍልሚያው ዋና ዘዴ ነው።

የዘመኑ መገበያያ የሆነው "ትኩረት"

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የውድድሩ አዘጋጆች ኢትዮጵያን ፋይት ሻምፒዮንሺፕ እና ኢትዮ ፋይት ናይት ስፖርቱ በስፋት እንዲታወቅ እና ትኩረት እንዲያገኝ ማኅበራዊ ሚዲያ ትልቅ መነቃቃት እየፈጠረ እንደሚገኝ ይገልጻሉ።

ውድድሩ በስፋት እንዲታወቅ ካደረጉት መካከል ዮሐንስ ስለሺ ወይም ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ 'ጆኒ ጂዩ-ጂትሱ' በሚል ስሙ የሚታወቀው ወጣትም "ትኩረት የዘመኑ መገበያያ ነው" ይላል።

ዮሐንስ ከሦስት ዓመት በፊት ብራዚሊያን ጂዩ-ጂትሱን መሠልጠን ሲጀመር፣ እንደዚህ ዓይነት ውድድር ወደፊት እንደሚያዘጋጅ እርግጠኛ እንደነበር ይናገራል።

"ፍልሚያ ሁሉም ሰው ይወዳል። በተደራጀ እና ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ማሳየት አለብን" ሲል ውድድሩ ቢዘጋጅ ተቀባይነት እንደሚያገኝ ተስፋ ማድረጉን ያስረዳል።

ዮሐንስ ስፖርቱን ከመጀመሩ በፊት እርሱ 100 ኪሎ በሚመዝንበት ወቅት ሁለት፣ ሀምሳ ኪሎ የሚመዝኑ በጂዩ-ጂትሱ የሰለጠኑ እህትማማቾችን ገጥሞ እንደተረታ ያስታውሳል።

በዚህ ምክንያት ስፖርቱ ውጤታማ እንደሆነ ወዲያውኑ በመረዳቱ፣ "ለሦስት ዓመታት ያህል በቀን ለስምንት ሰዓታት ያህል ያለማቋረጥ መሠልጠን ጀምሬያለሁ" ይላል።

ልምምዱን ሲጀምር ብራዚሊያን ጂዩ-ጂትሱ የሚያውቁ ጥቂት ሰው ብቻ እንደነበሩ የሚናገረው ዮሐንስ፣ የሚለማመዱ ሰዎችም በጣት የሚቆጠሩ ነበሩ።

ስፖርቱ በአጭር ጊዜ እንዲተዋወቅ እና ተቀባይነት እንዲያገኝም በማሰብ የማስተዋወቂያ እና የማርኬቲንግ ሥራ ከሚያውቃቸው ሰዎች ጋር በመሆን አቅዶ መሥራት ጀመረ።

ቀጥሎም በቲክቶክ ላይ እሱን ገጥመው ማሸነፍ ለሚችሉ በተለያየ የማርሻል አርት ልምድ ላላቸው ሰዎች 10 ሺህ ብር እሰጣለሁ በማለት "ቻሌንጅ" ጀምሯል።

10 ሺህ ብር በማስያዝ ወደ አራት ጊዜ ተጋጥሞ ካሸነፈ በኋላ ሽልማቱን ወደ 50 ሺህ ብር ከፍ አደረገው።

በመቀጠልም ወደ 100 ሺህ ብር አሳደገው። ነገር ግን የሚገጥሙት ሰዎች እሱን ቢያሸንፉት ምንም ገንዘብ መስጠት አይጠበቅባቸውም።

አንዳንድ ጊዜም ክብደት የሚያነሱ ስፖርተኞች ወደ ሚገኙበት ዐውደ ርዕዮች በመሄድ ከበርካታ ሰዎች ጋር በአንድ ቀን በየተራ በመግጠም ይወዳደር እንደነበር ዮሐንስ ያስረዳል።

ከዚያ በኋላም ግጥሚያዎቹ ተቀርጸው እና ተስተካክለው በማኅበራዊ ሚዲያ ይለቀቃሉ።

በታይላንድ የተሳተፉ የቡድን አበላት ካገኙት ሜዳሊያ እና ምስክር ወረቀት ጋር

የፎቶው ባለመብት, Ethio fight night

የምስሉ መግለጫ, በአውሮፓውያኑ 2019 በታይላንድ የተሳተፈው ቡድን፣ ሁለት ወርቅ እና አንድ የብር እና የነሐስ ሜዳሊያዎች አግኝቷል

ዮሐንስ ለረጅም ጊዜ እራሱ እያስተካከለ እና ለመዝናኛ የሚሆን ይዘት እየፈጠረ እንደሚለቅ ይናገራል። ይህም በአጭር ጊዜ ውስጥ በማኅበራዊ ሚዲያ ተወዳጅነት እንዲያገኝ አስቻለው።

ሰዎችም "ከተሸነፈ100 ሺህ ብር የሚከፍለው ምን ያህል በራሱ ቢተማመን ነው?" በማለት የሚሠራቸውን ቪድዮዎች ይቀባበሉ ጀመር።

ሰዎች ማን ያሸንፋል ከማለት በተጨማሪ፣ ይህን ያህል ገንዘብ ለምን ያወጣል? ማን ይመጣና ይሞክራል? የሚሉ ጥያቄዎችን ማንሳት በቀጠሉ ቁጥር የእርሱ ዝና እና ተቀባይነት ልክ አያደገ ሄደ።

በዚህ ሂደት ከኢትዮጵያ ፋይት ቻምፒዮንሺፕ ዋና ሥራ ስፈጻሚ ጌታቸው መለሰ ጋር መገናኘታቸው ውድድሩ ወደ ሌላ ደረጃ እንዲያድግ ጥሩ አጋጣሚ ፈጠረ።

የውጭ አገር የድብልቅ ማርሻል አርት (Mixed Martial Art) ልምድ እና ውድድሮችን የሚያውቀው ጌታቸው ዮሐንስን ካገኘው በኋላ፣ አሸናፊ አንድ ሚሊዮን ብር የሚሸለምበትን ትልቅ ውድድር እንዲያዘጋጁ ዕድል ፈጥሯል።

ይህ ውድድር በማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ከመፍጠሩ ባለፈ፣ ፒያሳ የሚገኘው አድዋ ሙዚየም ውድድሩን ለመመልከት በመጡ ሰዎች እንዲጥለቀለቅ ያደረገ ነው። ይህ ውድድር የነበረው ተቀባይነት ከፍ ያለ በመሆኑ ቀጣይ የሚዘጋጁ ውድድሮች አጓጊ ሆነው እንዲጠበቁ ዕድል ፈጥሯል።

ለመታደም እስከ መቶ ሺህ ብር የሚከፈልበት ቀጣዩ ፍልሚያ

የኢትዮጵያ ፋይት ቻምፒዮንሺፕ ነሐሴ 21/2018 ዓ.ም. ሦስት ሙአይ ታይ፣ አራት የቦክስ እና አራት የድብልቅ ማርሻል አርት በአጠቃላይ 11 ውድድሮችን የሚያዘጋጅ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ሴቶች የሚጋጠሙበት እንደሚሆን ተገልጿል።

ሌላኛው በመስከረም 9/2019 ዓ.ም. ኢትዮ ፋይት ናይት ከሌሎች አጋር በመሆን በእነዚህ አራት ውድድሮች ከውጭ እና ከአገር ውስጥ ስፖርተኞችን አሳትፎ ውድድር እንደሚያካሂድ አስታውቋል።

ውድድሮቹ በተለይም ስፖርቱ ትኩረት እንዲሰጠው እና በማይመች ሁኔታ ውስጥ ሆነው ልምምድ የሚያደርጉ ወጣቶችን ለማበረታታት አቅደው መዘጋጀታቸውን አዘጋጆቹ ይናገራሉ።

የኢትዮጵያ ፋይት ቻምፒዮንሺፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጌታቸው መለሰ በበኩሉ፣ የማርሻል አርት ውድድሮች በኢትዮጵያ ቀደም ሲል ከነበራቸው የሕዝብ ትኩረት አንጻር በስፋት እንዲታወቁ ማድረግ እና ለተወዳዳሪዎች የሚከፈል ገንዘብን ማሳደግ የቀጣዩ ውድድር ዝግጅት ዋና ትኩረቶች መሆናቸውን ይናገራል።

ይሁንና እንደዚህ ዓይነት ውድድርን ለማዘጋጀት የሚያስፈልጉ መሠረተ ልማቶችና ባለሙያዎች አሁንም በቂ አለመሆናቸውን ጌታቸው ይረዳል።

በዳኝነት በኩልም በኢትዮጵያ በተለይ ለድብልቅ ማርሻል አርት በቂ ዳኞች አለመኖራቸው ትልቅ ችግር መሆኑን የሚያነሳው ጌታቸው፣ ለአሁኑ ውድድር ዳኞችን ከአሜሪካ እንዲመጡ በማድረግ፣ በአንድ በኩል ኢትዮጵያ ውስጥ ላሉ ዳኞች ሥልጠና እንዲሰጡ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በውድድሩ ቀን የዳኝነት ሥራውን እንዲመሩ እያደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል።

የቀጣዩ ውድድር አጠቃላይ ወጪ እስከ 17 ሚሊዮን ብር እንደሚደርስ የገለጸው ጌታቸው፣ ከዚህ ውስጥ ወደ 11 ሚሊዮን ብር የሚሆነው ለተወዳዳሪዎች የሚከፈል ነው ብሏል።

የውድድሩ የገንዘብ ሽልማትም ከ300 ሺህ ብር እስከ 5 ሚሊዮን ብር የሚደርስ መሆኑን ጌታቸው ያስረዳል።

ከፍተኛ የደጋፊ ትኩረት ያገኘው እና በዮሐንስ ስለሺ (ጆኒ) እና ካሚል ነጋሽ (ሴዶ) መካከል ለሚካሄደው ግጥሚያ 5 ሚሊዮን ብር የሚወጣበት ሲሆን፣ አሸናፊው 4 ሚሊዮን ብር፣ ተሸናፊው ደግሞ 1 ሚሊዮን ብር ያገኛል ተብሏል።

የክፍያው ልዩነት የተፈጠረው ከውድድሩ ዓይነት ጋር የተያያዘ መሆኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚው አንስቷል። በውድድሩ ዓለም "ዋና ፍልሚያ" የሚባል ውድድር እንዳለ እና ተመልካቾች በተለይ ማየት የሚፈልጉት ይህንን በመሆኑ ክፍያው ከፍ መድረጉን ይገልጻል።

ውድድሩን በቦታው ለመታደም ከ4 ሺህ ብር ጀምሮ እስከ 100 ሺህ ብር የሚደርስ የመግቢያ ቲኬት ዋጋ እንደቀረበ ጌታቸው ተናግሯል። ሁለት ሺህ ሰዎች ውድድሩን ለመመልከት የሚገኙ ሲሆን፣ ይህም ካለፈው ውድድር አንጻር ከፍተኛ ቁጥር ይሆናል።

ከውድድሩ ሊገኝ ስለሚችለው ገቢ ግን አሁን በትክክል መገመት እንደማይቻል የገለጸው ዋና ሥራ አስፈጻሚው "ይሄን ያህል እናተርፋለን ብለን የሠራነው ነገር የለም፣ ብቻ መክሰር ነው የማንፈልገው" ብሏል።

ዮሐንስ

የፎቶው ባለመብት, johnnydoesjiujitsu

የምስሉ መግለጫ, ዩሐንስ ሚያዚያ ወር ላይ ከንቃተ ሕሊና ጋር በአድዋ ሙዚየም ተጋጥሞ አሸናፊ በመሆን የአንድ ሚሊዮን ብር አሸናፊ ለመሆን በቅቷል

በውጭ አገራት በስፖርቱ ዓለም ዝና ያላቸውን የውጭ አገር ተወዳዳሪዎች እና ኢትዮጵያን ወክለው ደግሞ ቢኒያም ሽብሬ፣ ክብሮም ንጉሤ እና አገረሰላም አርባን ጨምሮ በርካታ ስፖርተኞች አሳትፎ በ'ኢትዮ ፋይት ናይት' አማካኝነት የሚያዘጋጀው ውድድርም ትኩረት ስቧል።

በቅርብ ዓመታት የማርሻል አርት ስፖርቶች በማኅበራዊ ሚዲያ፣ በተለይም በቲክቶክ፣ የበለጠ እንዲታወቁ መደረጉ ለስፖርቱ አዲስ መነቃቃት እንደፈጠረ ማስተር ዳግማዊ ወርቅነህ ይገልጻል።

"ስፖርት ማደግ የሚችለው ታዋቂ ሰዎች፣ ባለሀብቶች፣ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ለስፖርቱ ያላቸውን ዕውቀት እያሰፉ ሲመጡ፣ ወደ ሕዝቡ እየተዳረሰ ሲመጣ የስፖርቱም ደረጃ በዚያው ልክ ያድጋል" ይላል።

በዚህ መነቃቃት ተጠቃሚ ሆኖ 'ኢትዮ ፋይት ናይት' ከውጭ ልምድ ያላቸውን ተወዳዳሪዎች በማምጣት የኢትዮጵያ ተወዳዳሪዎች የስፖርቱን ዓለም አቀፍ ደረጃ በተግባር እንዲያዩና ልምድ እንዲካፈሉ ለማድረግ እየሞከረ መሆኑን ማስተር ዳግማዊ ይናገራል።

24 በሞያው ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ዳኞችን ለማምጣት ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን የሚናገረው ማስተር ዳግማዊ፣ የሕክምናና የደኅንነት ዝግጅቶችም በውድድሩ ውስጥ ትኩረት ማግኘታቸውን ጠቁሟል።

የድብልቅ ማርሻል አርት ወይም ኤምኤምኤ ውድድር የአካል ንክኪ ያለበት ስፖርት በመሆኑ፣ የተወዳዳሪዎች ጤናና ደኅንነት በውድድሩ ዝግጅት ውስጥ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው።

ተወዳዳሪዎች ወደ መወዳደሪያ መድረክ ወይም 'ኬጅ' ሲገቡ ውድድሩን የሚመራ ዳኛ ይኖራል። አዘጋጆቹ እንደሚሉት፣ ውድድሩ ያለ ሕግ የሚደረግ "ገላጋይ የሌለው ዓይነት" ድብድብ ሳይሆን በሕጎች እና መስፈርቶች የሚመራ ነው።

በመወዳደሪያውም የሚፈቀዱ እና የማይፈቀዱ ቦታዎች እንዳሉ ገልጸዋል። አንድ ተወዳዳሪ ጥቃት እንዳይሰነዝር የተከለከለ የሰውነት አካል ላይ ጉዳት ቢያደርስ ከውድድር ውጪ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

ከዚህ ባሻገር የውድድሩ አዘጋጆች ለእያንዳንዱ ውድድሮች የሚሆኑ አስፈላጊ ትጥቆች መሟላታቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም በፍልሚያው ወቅት ጉዳት ቢደርስ እንኳ ድጋፍ ለማድረግ የሕክምና ዝግጅት እንደሚደረግ ተናግረዋል። ከፍተኛ ጉዳት ቢገጥም በሚል እያንዳንዳቸው ተወዳዳሪዎች ኢንሹራንስ እንዲኖራቸው መደረጉን አዘጋጆቹ ያስረዳሉ።

ውድድሩ በአዲስ አበባ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ሥር የሚመራ በመሆኑ፣ አስፈላጊው የደኅንነት ጉዳይ መሟላቱን እና አዘጋጆቹም በስፖርቱ የሚፈለገውን መስፈርት አሟልተው መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽእኖ

ተጠሪነቱ ለአዲስ አበባ ስፖርትና ወጣቶች ቢሮ የሆነው የአዲስ አበባ ኪክ ቦክሲንግ ማኅበር ፕሬዚዳንት ዳንኤል መኮንን፣ ቢሮው ማንኛውንም ድጋፍና ክትትል በማድረግ፣ ዳኛ በመመደብ እና በማሠልጠን፣ ስፖርተኞች ተገቢውን ጥቅም እንዲያገኙ፣ ጤናቸው እንዲጠበቅ በማድረግ ውድድሩን እንደሚደግፍ ገልጸዋል።

በተለይም የማርሻል አርት ውድድር ሲዘጋጅ ሂደቶችን የማቀላጠፍ፣ የመወዳደሪያ መድረክ ወይም ኬጅ የመመደብ ሥራዎችን ጨምሮ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን ማቅረብ ቢሮው እንደሚሠራም ያስረዳሉ።

በተጨማሪም እነዚህ ውድድሮች በሚዘጋጁበት ወቅት የውድድር ቦታው ከፀጥታ ችግር ነጻ እንዲሆን ከፀጥታ ቢሮ ጋር በመነጋገር ሁኔታዎችን እንደሚያስተካክሉ ተናግረዋል።

የንክኪ ስፖርት ውድድሮች በኢትዮጵያ 27 ዓመታት በፊት ጀምሮ ሲተገበሩ እንደነበር የሚገልጹት ፕሬዝዳንቱ ቀደም ሲል ውድድሮቹ ለሰፊው ሕዝብ በቀላሉ የማይደርሱት በተለይም ማኅበራዊ ሚዲያ ባለመኖሩ እንደነበር ይናገራሉ።

የኢትዮጵያ ፋይት ሻንፒዮንሺፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጌታቸው መለሰ፤ ውድድሩ ከተካሄደ በኋላ የፍልሚያ ስፖርት (combat sport) ሥልጠና መውሰድ የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር በመጨመራቸው ምዝገባ እስከማቆም መድረሳቸውን ያነሳል።

በሚያዝያ ወር የተደረገው ውድድር በተመልካቾች ዘንድ ከፍተኛ ተጽእኖ በመፍጠሩ ምክንያት ተመሳሳይ ውድድሮችን በዓመት አራት ጊዜ ለማካሄድ መታቀዱን ተናግሯል።