በሶማሊያ የባሕር ዳርቻ ላይ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት ዘጠኝ ሰዎች መገደላቸውን ባለሥልጣናት ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በሶማሊያ የባሕር ዳርቻ ታግቶ የቆመ ነዳጅ ጫኝ መርከብን ዒላማ ያደረገ የድሮን ጥቃት ዘጠኝ ሰዎች መግደሉን የፑንትላንድ ባለሥልጣናት ተናገሩ።
የፑንትላንድ ባለሥልጣናት ጥቃቱ የተፈጸመው በሶማሊያ ኑጋል ክልል፣ ጎዶብጂራን የባሕር ዳርቻ አቅራቢያ መሆኑን ተናግረዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩት መርከቧ ኤምቪ ሉቱፍ (MV Lutuf) የምትባል ሲሆን ከቀናት በፊት በባሕር ላይ ወንበዴዎች ታግታ ወደ አካባቢው መምጣቷን ተናግረዋል።
የካሜሮንን ሰንደቅ ዓላማ የምታውለበልበው ይህች መርከብ መዳረሻዋ ቱርክ ነበር ተብሏል።
ቢቢሲ የመርከቧን መዳረሻም ሆነ ሌሎች ተያያዥ መረጃዎችን ከገለልተኛ ወገን ማጣራት አልቻለም።
መርከቧ ከዚህ ቀደም ጋርማል የሚባል አካባቢ ቆማ የነበረ ሲሆን በአካባቢው በተፈጸመ የድሮን ጥቃት አራት ሰዎች ሞተዋል።
የድሮን ድብደባውን ማን እንደፈጸመው በይፋ የተገለጸ ነገር የለም። የሶማሊያ መንግሥትም ጥቃቱን አላወገዘም።
የፑንትላንድ ባለሥልጣናት ከዚህ ቀደም የተፈጸመውን ጥቃት አውግዘው የተገደሉት የባሕር ላይ ወንበዴዎች አይደሉም ብለው ነበር።
የአካባቢው ባለሥልጣናት የድሮን ጥቃቱን የፈጸመችው ቱርክ ልትሆን ትችላለች ቢሉም የቱርክ ባለሥልጣናት ግን ለቢቢሲ ምንም መረጃው እንደሌላቸው ተናግረዋል።
አብዲፋታህ ዩሱፍ የተባለ የዐይን እማኝ ማንነታቸው የማይለይ ስምንት በጥቃቱ የተገደሉ ሰዎችን መመልከቱን ተናግሯል።
“ስምንት በጥቃቱ የተቃጠሉ አስከሬኖች አይቻለሁ።” ብሏል።
የጎዶብጂራን ከንቲባ የሆኑት ኬነን ኦማር ለመበስበስ የተቃረበ አስከሬን ቆይቶ በመገኘቱ የሟቾች ቁጥር ዘጠኝ ደርሷል ብለዋል።
የሟቾቹ አስከሬን ሰኞ ይቀበራል ተብሎ ይጠበቃል።
የፑንትላንድ የመረጃ ምክትል ሚኒስትር ቢሌ ቀቦውሳዴ ከክስተቱ ጋር የተያያዙ ሁኔታዎች በመጣራት ላይ ናቸው ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ቀደም ሲል ከባሕር ላይ ዘረፋ ጋር ግንኙነት የነበራቸው ግለሰቦች እና ቡድኖች እንደገና እንዳይንቀሳቀሱ ለማድረግ የውጭ አካላት እየሞከሩ ሊሆን እንደሚችል የመጀመሪያ ደረጃ መረጃዎች እንደሚያመለክቱም ገልጸዋል።
የፑንትላንድ ባለሥልጣናት መርከቦቻቸው በባሕር ላይ ዘራፊዎች ሊያዙ ወይም ሊታገቱ የሚችሉ የመርከብ ባለቤቶች፣ ኦፕሬተሮች፣ የዋስትና ሰጪ ድርጅቶች እና ሌሎች አካላት ከዘራፊ ቡድኖች ጋር በቀጥታ ድርድር እንዳያደርጉ ወይም የማስለቀቂያ ክፍያ እንዳይፈጽሙ አሳስበዋል። እንዲህ ዓይነት ክፍያዎች የወንጀል ቡድኖች ተግባራቸውን እንዲቀጥሉ የሚያስችላቸውን ግብዓትና ማበረታቻ ሊሰጧቸው እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል።


