ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የእስራኤል ሰፋሪዎች በፈጸሙት ጥቃት ፍልስጥዔማዊ ሲገደል በርካቶች ቆሰሉ
እስራኤላዉያን ሰፋሪዎች በከፈቱት ጥቃት አንድ ፍልስጥዔማዊ ሲገደል በርካቶች ቆሰሉ።
ጥቃቱ የተከፈተው እስራኤል በኃይል በያዘችው ዌስት ባንክ ሲሆን የተገደለው ግለሰብም በጥይት እንደሆነም ተገልጿል።
በመቶዎች የሚቆጠሩ የታጠቁ ሰፋሪዎች በዌስት ባንክ ግዛት በምትገኘው ቱርሙሳያ ከተማ ቤቶችን እና መኪናዎችን አቃጥለዋል።
በከተማዋ የሚኖሩ ፍልስጥዔማውያንም ለህይወታቸው ሰግተው በፍርሃት ላይ እንዳሉ ተናግረዋል።
ጥቃቱ በተፈጸመበት ወቅት የእስራኤል ጦር ለ45 ደቂቃ ያህል ያለ እርዳታ እንደተዋቸው አንድ ግለሰብ ተናግረዋል።
“ሰፋሪዎቹ ይህንን ጥቃት እንዲፈጽሙ እድል ሰጥተዋቸዋል” ብለዋል።
ማክሰኞ በታጠቁ ፍልስጥዔማውያን ከተገደሉ አራት እስራኤላውያን ሰፋሪዎች መካከል የ17 ዓመቱ ታዳጊ የቀብር ስነ ስርዓት ከተፈጸመ ከሰዓታት በኋላ የተፈጸመው ይህ ጥቃት የበቀል ምላሽ ነው ተብሏል።
የእስራኤል ጦር የሰፋሪዎቹን ጥቃት ቢያወግዝም ምላሽ ለመስጠት ሆን ብሎ ዘግይቷል ለሚለው ክስ ምላሽ አልሰጠም።
ሰኞ እለት የእስራኤል ወታደራዊ ኃይል በጄኒን ከተማ በፈጸመው ጥቃት ሰባት ፍልስጥዔማውያን ተገድለዋል። እሱንም ተከትሎ በዌስት ባንክ እየደረሱ ያሉ ጥቃቶች እየከፉ ሊመጡ ይችላል የሚልም ስጋት ጭሯል።
በእስራኤል በኃይል ከተያዙ ግዛቶች አንዷ የሆነችው ዌስት ባንክ ለዓመታት በርካታ ጥቃቶችን አስተናግዳለች።
በቅርቡም በመኪና የተጫኑ የእስራኤል ወታደሮችን በፈንጂ ያጠቁ የፍልስጥዔም ታጣቂዎችን ኢላማ ያደረገ ነው በሚል ከሰሞኑ የእስራኤል የአየር ኃይል ሄሊኮፕተሮችን በመጠቀም ሚሳኤሎችን ተኩሷል።
እስራኤል በፈንጂ ጥቃቱ ሰባት የእስራኤል ወታደሮች ቆስለውብኛል ብላለች።
በእስራኤል የሚሳኤል ተኩስ ምላሽም ከተገደሉት ፍልስጥኤማውያን መካከል ሁለት የ15 ዓመት ታዳጊዎችና ሁለት ታጣቂዎች ይገኙበታል ተብሏል። በማግስቱም በአንድ ቤንዚን ማደያ ላይ የሃማስ ታጣቂዎች ለፈጸሙት ጥቃትም መነሻ ነው ተብሏል።
ይህንንም ተከትሎ የእስራኤላውያንን ሰፈራ የሚደግፉ ጽንፈኛው የሃይማኖትና ብሄርተኝነት ጥምረትም ሚኒስትሮችም በዌስት ባንክ አጠቃላይ ወታደራዊ ዘመቻ እንዲካሄድ ጥሪ አቅርበዋል።
ሚኒስትሮቹ የፍልስጥኤም ህንጻዎችን ለማውደም የአየር ጥቃት ማድረግን ጨምሮ አንድ የፓርላማ አባል በተራ ፍልስጥኤማውያን ላይ ያነጣጠረ “የጅምላ ጥቃት” እንዲፈጸም ጠይቀዋል።
አሁን በሰፋሪዎች ጥቃት በተፈጸመባት ቱርሙሳያ ከተማ መኪናዎች ሲነዱ የሚያሳይ ጥቁር ጭስ፣ እንዲሁም የእጅ ቦምቦችና ተቀጣጣዮች ሲፈነዱ የሚሰማበት ቪዲዮም ወጥቷል።
የከተማዋ ከንቲባ ላፊ አደብ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ወደ 400 የሚጠጉ እስራኤላውያን ሰፋሪዎች በከተማዋ ውስጥ የሚገኙ ቤትና መኪኖች ያቃጠሉ ሲሆን አምስት ነዋሪዎች ደግሞ በጥይት ተመትተዋል።