የካሜሩን ተገንጣይ ኃይሎች ግብር አንከፍልም ያሉ በርካታ ሰዎችን ገደሉ

መሳሪያ የያዘ ሰው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

በካሜሩን መገንጠልን አላማቸው አድርገው ይንቀሳቀሳሉ የተባሉ ታጣቂዎች በናይጄሪያ ድንበር አቅራቢያ በሚገኝ መንደር ላይ በፈጸሙት ጥቃት በትንሹ 20 ሰዎችን መግደላቸው ተዘገበ።

የአከባቢው ከንቲባ ኤክዋሌ ማርቲን እንደተናገሩት ባሳለፍነው እሁድ በደቡብ ምዕራብ የካሜሩን ክፍል ኦቦኒ ሁለት በተሰኘ መንደር ውስጥ በተደረገው ወረራ እና ጥቃት ከሞቱት ባሻገር ከ60 በላይ ሰዎች ቆስለዋል።

“ታጣቂዎቹ ነዋሪዎቹ በየወሩ ገንዘብ እንዲከፍሏቸው ይፈልጋሉ፤ ነዋሪዎቹ ደግሞ ፍቃደኛ አልሆኑም። ለዚህም ነው ጥቃት ያደረሱባቸው” ሲሉ ከንቲባው ለአጃንስ ፍራንስ ፕረስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

የካሜሩን መንግሥት ይህ ተገንጣ ቡድን በሚንቀሳቀስበት አካባቢ ታግተው የነበሩ የሕዝብ ተወካይ እና ሌሎች በርካታ ታጋቾችን ማስለቀቁን ማክሰኞ ዕለት ማስታወቁ ይታወሳል።

የካሜሩን ሴኔት አባል የሆኑት ኤልዛቤት ሬጂና ሙንዲ ባለፈው ወር በሰሜን ምዕራብ ክልል በእነዚሁ የተገንጣይ ኃይሎች ታግተው ነበር።

እንግሊዚኛ ቋንቋ ተናጋሪ የሆነውን የካሜሩንን ክፍል ለመገንጠል ከሚሰራው ታጣቂ ቡድን የሕዝብ ተወካይ አባሏን ለማስለቀቅ የካሜሩን ጦር ተሰማርቶም ነበር።

እ.ኤ.አ. ከ2017 ጀምሮ በታጣቂዎች እና በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች መካከል በተደረጉ ግጭቶች ከ6,000 በላይ ሰዎች መሞታቸውን እና ከ700,000 በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን አለም አቀፉ ክራይስስ ግሩፕ ገልጾ ነበር።