ዩክሬን የሩስያን ኤ-50 የስለላ አውሮፕላን መትቼ ጣልኩ አለች

የሩሲያ አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

የዩክሬን ጦር በአዞቭ ባሕር ላይ የሩስያ የስለላ አውሮፕላን መትቶ መጣሉን አስታወቀ።

ይህ በሞስኮ የአየር ኃይል ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ሊያደርስ እንደሚችል ተንታኞች ተናግረዋል።

የዩክሬን የጦር ኃይል አዛዥ ጄኔራል ቫለሪይ ዛሉዥኒ እንዳሉት የአየር ኃይሉ ኤ-50 የተሰኘ በረዥም ርቀት ራዳር የሚቃኝ አውሮፕላን እና አይኤል-22 የተሰኘ የቁጥጥር ማዕከል አውሮፕላንን "አውድመዋል።"

ኤ-50 ተሰኘው ስለላ አውሮፕላን የአየር መከላከያዎችን በመለየት የሩስያ ጄቶች ዒላማዎችን እንዲያጠቁ ያመቻቻል።

ዩክሬን በደቡብ-ምስራቅ በሚገኙ የሩሲያ ኃይሎች ላይ የበላይነት ለመያዝ መቸገሯ ተገልጿል።

የዩናይትድ ኪንግደም የመከላከያ ሚኒስቴር ባለፈው ዓመት በሰጠው አጭር መግለጫ ሩሲያ “በግምት” ስድስት የሚደርሱ ኤ-50ዎች በአገልግሎት ላይ ነበራት ብሏል። አውሮፕላኖቹ ለመሥራት በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ሊፈጅ ይችላል።

ቢቢሲ ጥቃቱን ማረጋገጥ አልቻለም።

የሩስያ ባለስልጣናት ስለ ጥቃቱ ምንም መረጃ እንደሌላቸው ቢናገሩም ታዋቂ የሆኑ እና ጦርነቱን የሚደግፉ የሩሲያ ተንታኞች የኤ-50 አውሮፕላን መመታት ከፍተኛ ኪሳራ እንደሚሆን ተናግረዋል ።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ራይባር የተሰኘ ስመ ጥር ወታደራዊ ጣቢያ እንዳለው ዩክሬን ስለአውሮፕላኑ ያወጣችው መረጃ ከተረጋገጠ "ለሩሲያ አየር ኃይል ሌላ ጥቁር ቀን" ይሆናል።

ሌላ ጣቢያ ደግም አይኤል-22 የትዕዛዝ ማዕከል በሩሲያ “ጥቃት” ተመቷል፤ ጥቃቱን በድጋሚ ወደ ሩሲያ እንዲዞር ተችሏል ተብሏል።

የዩክሬን አየር ኃይል ቃል አቀባይ ዩሪ ኢህናት እንዳሉት አይኤል-22 አውሮፕላን ከጥቅም ውጭ እስኪሆን ድረስ ወድሟል።

በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የወጣና የአይኤል-22 ነው ተባለ ምስል በጅራቱ ላይ የደረሰውን ጉዳት አሳይቷል።

በሥዕሉ ላይ ብዙ ዝርዝሮች ጉዳዮች ስለማይታዩ በገለልተኛ ወገን ትንታኔ ለመስጠት አስቸጋሪ አድርጎታል።

ቢቢሲ ቬሪፋይ ፎቶውን ከአካባቢው ካሉ ነባር ፎቶዎች ጋር ለማነጻጸር ሞክሯል።

የእሳት አደጋ ሞተሩ በክራስኖዶር ክልል ከሚጠቀሙት የተሽከርካሪ አይነቶች ጋር ሊመሳሰል የሚችል ነው። ከጀርባ ያለው ሰማያዊ ህንጻ ደግሞ የጥቁር ባህር ዳርቻ ከተማዋ አናፓ አየር ማረፊያ ጋር ተመሳሳይ ነው።

ይሁን እንጂ የኤ-50 የስለላ አውሮፕላን "ዋናው ዒላማችን ነበር" ብለዋል ኢህናት።

ጀነራል ዛሉዚኒ በቴሌግራም እንደተናገሩት የዩክሬን አየር ኃይል በደቡብ ምስራቅ በሚገኘው በአዞቭ ክልል ዘመቻውን “በጥሩ ሁኔታ አቅዶ ነበር።”

ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ላይ የቤላሩስ ተቃዋሚ ቡድን የሆነው ቢዋይፒኦኤል በሚንስክ አቅራቢያ ባደረሰው የድሮን ጥቃት ኤ-50 ወታደራዊ አውሮፕላን ላይ ጉዳት ማድረሱን ተናግሮ ነበር።

ሩሲ የተባለው ተቋም ባልደረባ እና የአየር ጦርነት ስፔሻሊስት የሆኑት ጀስቲን ብሮንክ ለቢቢሲ እንደተናገሩት መረጃው ከተረጋገጠ የኤ-50 አውሮፕላን መውደም ለሩሲያ አየር ኃይል “አሳፋሪ ኪሳራ” ነው።

ኤ-50ን "ቁልፍ ትዕዛዝ የሚሰጥ፣ ቁጥጥር እና ክትትል የሚያደርግ" ከመሆን ባለፈ ለሩሲያ አውሮፕላኖች እና ለሚሳኤል ስርዓቶች "የቅድመ ማስጠንቀቂያ እና ስለ ዩክሬን አነስተኛ አውሮፕላኖች ኢላማ መረጃዎችን የሚሰጥ" ነው ብለዋል።

በሩሲያ አየር ኃይል ውስጥ የእነዚህ አውሮፕላኖች ቁጥር "ጥቂት ብቻ" ናቸው። "ጥቂት የሰለጠኑ ባለሙያዎችም ስላላቸው የአንዱን መውደም ትልቅ ጉዳት ነው" ብለዋል።

የቢቢሲ የደህንነት ጉዳዮች ዘጋቢ ፍራንክ ጋርድነር በበኩሉ "በአስፈሪ መጥፎ ዜናዎች ውስጥ የተገኘ የዩክሬን ትንሽ የምስራች" ሲል ስለጉዳዩ አስታውቋል።

አጠቃላይ ሁኔታው የጥይት እጥረት፣ የወታደሮቿ የሞራል ዝቅጠት እና ሩሲያ በመሠረተ ልማቷ ላይ የምታደርሰውን ጥቃት የሚመለከት በመሆኑ "ለዩክሬን ጥሩ አይመስልም" ብሏል።