ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሞተ በማስመሰል ከእስር ቤት ያመለጠው ወንጀለኛ ከዓመት በኋላ ተያዘ
በግድያ እና በአስገድዶ መድፈር ወንጀሎች ጥፋተኛ ተብሎ እስር ቤት የነበረው ደቡብ አፍሪካዊ የሞተ አስመስሎ ከእስር ቤት ካመለጠ ከአንድ ዓመት በኋላ ታንዛኒያ ውስጥ በቁጥጥር ሥር ዋለ።
ታቦ ቤስቴር የተባለው ወንጀለኛ ታስሮ በነበረበት ክፍል ውስጥ እራሱን በእሳት አቃጥሎ ሕይወቱን አጥፍቷል ተብሎ ታምኖ ነበር።
ይሁን እንጂ በእስር ቤት ክፍል ውስጥ የተገኘው አስክሬን የቤስቴር አለመሆኑን የአስክሬን ምርመራ ካረጋገጠ በኋላ ወንጀለኛውን የመያዝ ጥረት ከአንድ ወር በፊት ተጀምሮ ነበር።
ቤስቴር ከጥቂት ቀናት በፊት ከሴት ፍቅረኛው እና ከሌላ ሦስተኛ ግለሰብ ጋር በታንዛኒያ በቁጥጥር ሥር የዋለ ሲሆን ለደቡብ አፍሪካ ተላልፎ ይሰጣል ተብሏል።
ፖሊስ እንደሚለው ሦስቱ ግሰለቦች ወደ ጎረቤት አገር ኬንያ የመሸሽ እቅድ ነበራቸው።
ቤስቴር “የፌስቡክ አስገድዶ ደፋሪ” በሚለው ቅጽል ስሙ ይታወቃል። ይህን ስያሜ ያገኘው ደግሞ ጥቃት የሚያደርስባቸውን ሴቶች በፌስቡክ አማካይነት አታሎ በእጁ ስለሚያስገባቸው ነው።
ግለሰቡ እአአ 2012 ላይ ሞዴል የነበረችውን ኖፉንዶ ታይሁሉ የተባለች የሴት ጓደኛውን ደፍሮ ገድሏል በሚል ጥፋተኛ ተብሎ ነበር። እአአ 2011 ላይ ደግሞ ሌሎች ሁለት ሴቶችን አስገድዶ በመድፈር እና በመዝረፍ ጥፋተኛ ተብሎም ነበር።
ቤስቴር ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ ታስሮ በነበረበት የደቡብ አፍሪካ እስር ቤት ውስጥ እራሱን አቃጥሎ ሕይወቱን አጥፍቷል ተብሎ ነበር።
ይሁን እንጂ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ቤስቴር ሕይወቱ አልፏል መባሉን ጥያቄ ውስጥ የሚከቱ ዘገባዎችን ማውጣት ጀመሩ።
የአስክሬን ምርመራ አስክሬኑ የቤስቴር አለመሆኑን ካረጋገጠ በኋላ ፖሊስ ሌላ የግድያ ምርመራ ፋይል ከፍቷል።
በቤስቴር እስር ቤት ክፍል ውስጥ ተቃጥሎ የተገኘው ሰው ማንነት እስካሁን ባይታወቅም ግለሰቡ ግን ጭንቅላቱ ላይ ጉዳት ደርሶበት ሕይወቱ ስለማለፉ የምርመራው ውጤት አሳይቷል።
ቤስቴር ታስሮ ይገኝበት የነበረውን እስር ቤት የሚጠብቀው የእንግሊዙ ጂ4ኤስ ወንጀለኛው እንዲያመልጥ ረድቷል ተብሎ ክስ ይቅርብበታል።
ቢቢሲ ከግል ኩባንያው አስተያየት ለማግኘት ያደረገው ጥረት ባይሳካም ጂ4ኤስ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ሦስት ሠራተኞችን ከሥራ አባርሪያለሁ ብሏል።
ቤስቴር በታንዛኒያ በቁጥጥር ሥር ከመዋሉ በፊት በደቡብ አፍሪካዋ ጆሃንስበርግ የባለጸጎች መንደር ውስጥ ግዙፍ መኖሪያ ቤት ተከራይቶ እየኖረ ነው የሚሉ ሪፖርቶች ሲወጡ ነበር። ከዚህ በተጨማሪም ቤስቴር በመደብሮች ውስጥ በግልጽ ሲገበያይ አይተነዋል የሚሉ ሰዎችም ነበሩ።
በዓለም ላይ በርካታ ጾታዊ ጥቃቶች በሚፈጸሙባት ደቡብ አፍሪካ የቤስቴር ከእስር ቤት ማምለጥ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሶ ነበር።