በርካቶች ራሳቸውን እንዲያጠፉ ለመርዳት መርዝ የሸጠው ካናዳዊ ክስ ተመሰረተበት

የፎቶው ባለመብት, Peel Regional Police
በርካቶች ራሳቸውን እንዲያጠፉ በማማከር እንዲሁም መርዝ የሸጠው ካናዳዊ ተጨማሪ 12 ክሶች ቀረቡበት።
በቶሮንቶ ተቀማጭነቱን ያደረገው የ57 ዓመቱ ኬኔት ሎው ግለሰቦች ራሳቸውን እንዲያጠፉ በማማከር እንዲሁም በማገዝ ሁለት ክሶች የተመሰረተበት ግንቦት ወር ላይ ነበር።
ግለሰቡ ገዳይ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን የያዙ 1 ሺህ 200 እሽጎችን ወደ 40 አገራት ልኳል ብሎ እንደሚያምን ፖሊስ አስታውቋል።
የብሪታንያ መርማሪዎች እንዳሉት ኬኔት መርዝ የሸጠላቸው 88 የዩናይትድ ኪንግደም ዜጎች ህይወታቸው አልፏል።
ኬኔት በቅርብ ጊዜ የቀረቡበት ክሶች በካናዳዋ ኦንታሪዮ ግዛት ውስጥ ራሳቸው ያጠፉ ሰዎችን አማክሯል እንዲሁም አግዟል የሚሉ ናቸው።
የሟቾቹ እድሜያቸው ከ16 እስከ 36 ዓመታቸው እንደሆነም ተገልጿል።
በኦንታሪዮ የሚገኙ አስራ አንድ የፖሊስ ኤጀንሲዎች በምርመራው የተሳተፉ ሲሆን የዮርክ ግዛት ፖሊስ ኢንስፔክተር ሲሞን ጄምስ “ውስብስብ” እና አሁንም ያላለቀ ምርመራ መሆኑንም አስታውቀዋል።
መርማሪዎች “መረጃዎችን በአለም አቀፍ ደረጃ ላሉ ህግ አስከባሪ አካላት እያካፈሉ ነበር” ሲሉም ኢንስፔክተሩ አክለዋል።
“በማህበረሰባችን ውስጥ ያሉ ተጋላጭ ዜጎችን ኢላማ ያደረጉ የወንጀል ድርጊቶችን አንታገስም” ሲሉም አስረድተዋል።
ኬኔት ሎው ሰዎች ህይወታቸውን እንዲያጠፉ የሚያግዙ መሳሪያዎችን እንዲሁም መርዞችን የሚያቀርቡ በርካታ ድረ ገጾችም እንደነበሩት የካናዳ መርማሪዎች ገልጸዋል።
በለንደን የሚገኘው የብሔራዊ ወንጀል ኤጀንሲ (ኤንሲኤ) ከቀናት በፊት ግለሰቡ በዩናይትድ ኪንግደም ብቻ ለ272 ሰዎች መርዝ መላኩን አስታውቋል።
ከእነዚህም መካከል 88ቱ መሞታቸውን የብሪታንያ ፖሊስ ቢያስታውቅም ለግለሰቦቹ ህይወት ማለፍ ብቸኛውና ቀጥተኛው መንስዔ መርዝ ስለመሆኑ ማረጋገጥ አልቻለም።
“በእነዚህ ሁኔታዎች የሚወዷቸውን ሰዎች ላጡ ቤተሰቦች የሚሰማን ሃዘን ጥልቅ መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን። በአሁኑ ወቅት በፖሊስ ኃይል የሰለጠኑ መኮንኖች ድጋፍ እያደረጉላቸው ይገኛሉ” ሲሉም የኤንሲኤ ምክትል ዳይሬክተር ክሬግ ተርነር አርብ ዕለት ገልጸዋል።
ኤጀንሲው አክሎም “በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ተፈጽሟል ብለው በሚጠረጥሯቸው ወንጀሎች” ላይ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን ገልጿል።












