በኢትዮጵያ ባለፉት 14 ወራት ነዳጅ ምን ያህል ጨመረ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በኢትዮጵያ ከቅርብ ወራት ወዲህ ከፍተኛ የሆነ የነዳጅ ጭማሪ እየታየ ይገኛል።
ለዚህ ደግሞ ዋነኛ ምክንያቱ መንግሥት ለዘረፉ ያደረግ የነበረውን ድጎማ ማንሳት መጀመሩ ነው።
ከፍተኛ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪው በአገሪቱ ያላውን የዋጋ ንረት የበለጠ ከፍ ያደርገዋል የሚል አስተያየት ቢሰማም መንግሥት የዋጋ ማስካከያ ማድረጉን ቀጥሏል።
የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በዓለም አቀፍ ደረጃ ባለው ተከታታይይ የዋጋ ጭማሪ ምክንያት ለነዳጅ ሲደረግ የነበረውን ድጎማ ማስቀጠል እንዳልቻለ በመግለጽ ደረጃ በደረጃ ድጎማውን ሲያስቀር ቆይቷል።
በዚህም ባለፉት 14 ወራት ማለትም ከሰኔ 29/2014 ዓ.ም. እስከ ነሐሴ 23/2015 ዓ.ም. ድረስ ቤንዚን፣ ነጭ ናፍጣ እና ኬሮሲን 55 በመቶ እና ከዚያ በላይ ጭማሪ ታይቶባቸዋል።

ሰኔ 29/2014 ዓ.ም. ቤንዚን በሊትር 47 ብር ከ83 ሳንቲም ይሸጥ ነበር። ነጭ ናፍጣ 49.02 ሳንቲም እንዲሁም ኬሮሲን 49.02 ሳንቲም ለተጠቃሚዎች ይቀርብ ነበር።
ከትናንት ነሐሴ 23/2015 ዓ.ም. ጀምሮ ግን ቤንዚን በሊትር 74.85 ብር፣ ነጭ ናፍጣ 76 ብር ከ34 ሳንቲም እንዲሁም ኬሮሲን 76 ብር ከ34 ሳንቲም እንዲሸጡ የችርቻሮ ዋጋ ተቆርጦላቸዋል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚንስቴር የዓለም ነዳጅ ዋጋ ከሚያዝያ ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ሰኔ ወር መጨረሻ ድረስ አንጻራዊ መረጋጋት ታይቶበት ቆይቷል ያለ ሲሆን፣ ከሐምሌ ጀምሮ ግን የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ጭማሪ እያሳየ በመምጣቱ የዋጋ ማሻሻያ ማድረግ አስፈልጓል ብሏል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚንስቴር ለነዳጅ ይደረግ የነበረውን ድጎማ የማንሳት ተግባር ዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ ያሉ ሰዎችን በማይጎዳ እና “በበቂ ጥናት ዝግጅት” እየተከናወነ መሆኑን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
በየጊዜው እየተደረገ ካለው የዋጋ ጭማሪ ጋር ቢሆንም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከሚገኙ አገራት ነዳጅ በአነስተኛ ዋጋ ከሚሸጥባቸው አገራት መካከል ተጠቃሽ ነች።
በዓለም ዙሪያ ባሉ አገራት የነዳጅ መሸጫ ዋጋን እንደሚያቀርበው 'ስታቲስታ' መረጃ ከሆነ ኢትዮጵያ ነዳጅ አምራች ከሆኑት አንጎላ፣ ናይጄሪያ እና አልጄሪያ በመቀጠል በአፍሪካ ውስጥ በአስተኛ ዋጋ የነዳጅ ምርቶች ለሕዝቧ የምታቀርብ አገር ናት።
በአሁኑ ወቅት ዓለም አቀፉ የነዳጅ ዋጋ ካለፉት ዓመታት የበለጠ ሆኗል።
ነዳጅ ከውጭ አስመጥተው የሚጠቀሙ አገራት፣ ነዳጅ አምርተው የሚልኩ አገራት ስብስብ የሆነው ኦፔክ ፕላስ (Opec+) የነዳጅ ምርትን እንዲጨምሩ ሲጠይቁ ቆይተዋል።
ሩሲያን ጨምሮ የኦፔክ ፕላስ አባል አገራት የነዳጅ ዋጋን ለመጨመር እርምጃ ሲወስዱ ቆይተዋል።
የኦፔክ አባል አገራት ዋጋን ከሚጨምሩበት መንገድ አንዱ በቀን የሚመረተውን ነዳጅ በመቀነስ ነው።
ዋነኞቹ 23 የዓለማችን የነዳጅ ዘይት አምራች አገራት በዓለም ገበያ ድፍድፍ ነዳጅ በስንት ይሸጥ የሚለውን ለመወሰን ውይይት ያካሂዳሉ።
ከኦፔክ ፕላስ በፊት በ1960ዎቹ ኦፔክ ሲመሠረት አላማው የዓለምን የነዳጅ ዘይት ገበያ ፈር ማስያዝ ነበር። ዛሬ ላይ የዓለም 30 በመቶ ነዳጅ የሚመረተው በኦፔክ አገራት ነው።
ሳዑዲ አረቢያ በቀን ከ10 ሚሊዮን በርሜል በላይ ነዳጅ በማምረት የአንበሳውን ድርሻ ትይዛለች።












