የሱቶን ግምቶች፡ በዚህ ሳምንትስ አርሰናል እና ዩናይትድ እንዴት ይሆናሉ?

ታትሟል

የቢቢሲው እግር ኳስ ተንታኝ ክሪስ ሱቶን ዛሬን ጨምሮ ቅዳሜ እና እሁድ የሚደረጉ የፕሪሚየር ሊግ እና የኤፍኤ ዋንጫ ጨዋታ ግምቶቹን እንደሚከተለው አስቀምጧል።

ዛሬ ምሽት አርሰናል በሜዳው ከሳውዝሃምፕተን የሚያደርገው ጨዋታ ይጠበቃል። ኒውካስል እና ቶተነሃም የሚያደርጉትም የብዙዎችን ቀልብ ይዟል። ዩናይትድ በኤፍኤ ዋንጫ ከብራይተን ይጨወታል።

አርሰናል ከሳውዝሃምተን

ዓርብ ምሽት 4 ሲል መድፈኞቹ በሜዳቻው ሳውዝሃምፕተንን ያስተናግዳሉ።

አርሰናል በሁለት ተከታታይ ጨዋታ በሁለት ግብ ልዩነት እየመራ ሁለቱንም ጨዋታ አቻ መለያየቱ በተጫዋቾቹ እና በአሰልጣኙ ላይ ጫና የሚያበረታ ነው።

መድፈኞቹ ረቡዕ ወደ ኢትሃድ ስለሚሄዱ የዛሬውን ጨዋታ የግድ ማሸነፍ አለባቸው። በሊጉ በመጨረሻ ደረጃ ላይ ከሚገኝ ክለብ ጋር በሜዳቸው ተጫውተው ነጥብ ይጥላሉ ማለት በጭራሽ የሚጠበቅ አይደለም።

ግምት፡ አርሰናል 2 - 0 ሳውዝሃምፕተን

ቅዳሜ

ፉልሃም ከ ሊድስ

ባለፈው ሳምንት ፉልሃም ኤቨርተንን ማሸነፉ በጣም ነው ያስደነቀኝ። በተከታታይ አራት ጨዋታዎች የተሸነፈ ቡድን እንዴት ሆኖ ከሜዳው ውጪ ኤቨርተንን ማሸነፍ ቻለ?

በእርግጥ ማሸነፍ ይገባቸው ነበር። አሁን በራስ መተማመናቸው የተመለሰ ይመስላል። በሌላ በኩል ሊድሶች ወጥ የሆነ አቋም ላይ አይገኙም። ከሊቨርፑል ጋር አቻ ይለያያሉ ብዬ ገምቼ የነበረ ቢሆንም 6 ገብቶባቸው ተሸንፈዋል።

ከፉልሃም ጋር በሚኖራቸው ጨዋታ ብዙ ባይገባባቸውም መሸነፋቸው የሚቀር አይመስልም።

ግምት፡ ፉልሃም 2 - 1 ሊድስ

ብሬንትፎርድ ከ አስተን ቪላ

ባለፉት ሳምንታት ለአስቶን ቪላ አነስተኛ ግምት የሰጠሁት እኔ ብቻ አይመስለኝም። ቪላ ኒውካስልን 3 ለ 0 ያሸነፈው በፍጹም የበላይነት ነው። የኡናይ ኤምሪ ቡድን አሁን ላይ ከፍ ብሎ እየበረረ ነው።

በኡናይ ኤምሪ አስተዳደር ስር ዋትኪንስ ብቻ አይደለም ድንቅ የሆነው፤ ኢሚያኖ ቦንዲያም እንዲሁ አስደናቂ አቋም እያሳየ ነው።

በአንጻሩ ብሬንት ፎርድ ባለፉት ሳምንታት ደካማ አቋም እያሳየ ነው። ንቦቹ በሜዳቸው ብዙም ባይሸነፉም ከዚህ ጨዋታ ምንም ነጥብ ማግኘት እንደማይችሉ እገምታለሁ።

ግምት፡ ብሬንትፎርድ 1 - 2 አስተን ቪላ

ክርስታል ፓላስ ከ ኤቨርተን

ኤቨርተኖች በሜዳቸው ፉልሃምን አለማስቆማቸው ትልቅ የማስጠንቀቂያ ደውል ነው። በሾን ዳይሽ ስር ጥሩ ጨዋታ ቢያሳዩም ከሊጉ ላለመውረድ ነጥቦችን መሰብሰብ ግድ ይላቸዋል።

በተቃራኒው ፓላሶች የመውረድ ስጋት ያለባቸው አይመስለኝም። ሮይ ሆድሰን ወደ ፓላስ ከተመሰሉ በኋላ ከሦስት ዓመታት በኋላ አራት ተከታታይ ጨዋታዎችን ማሸነፍ ችለዋል።

ይህ ጨዋታ አቻ እንደሚጠናቀቀ ገምታለሁ።

ግምት፡ ክርስታል ፓላስ 1 - 1 ኤቨርተን

ሌስተር ከ ዎልቭስ

ከመውረድ ስጋት ርቀው የሚገኙት ዎልቭስ ናቸው። ሌስተር ደግሞ 19ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ቀበሮዎቹ ከሊጉ መሰናበት ካልፈለጉ ይህን ጨዋታ ማሸነፍ ግዴታቸው ነው። ግን በደካማ የተከላካይ መስመራቸውን ይህን ማድረግ ይችላሉ ወይ የሚለው መመለስ አለበት።

ግምት፡ ሌስተር 1 - 1 ዎልቭስ

ሊቨርፑል ከ ኖቲንግሃም ፎረስት

ከዚህ ሳምንት የጨዋታ ግምቶቼ ማን ሊያሸንፍ እንደሚችል በእርግጠኝነት መናገር የምችለው ስለዚህ ጨዋታ ነው።

ፎረስት ብዙ ቢደክሙም በቂ ውጤት እየስመዘገቡ አይደለም። 10 ተከታታይ ጨዋታዎችን ያላሸነፉት ፎረስቶች በአንፊልድ ሌላ ሽንፈት እንደሚገጥማቸው እርግጥ ነው።

ግምት፡ ሊቨርፑል 3 - 0 ፎረስት

ቦርንመዝ ከ ዌስት ሃም

ዌስት ሃሞች ከአርሰናል ጋር በነበራቸው የመጨረሻዎቹ 60 ደቂቃዎች ባለፉት ሁለት የውድድር ዘመኖች የምናቀውን ዌስት ሃምን ነው ያስታወሱኝ። አስደንቀውኝ ነበር።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ቦርንመዞች ባለፈው ሳምንት ቶተነሃምን ያሸነፉበት ሁኔታ አስደናቂ ነበር። ከሊጉ እንደማይወርዱ ይሰማኛል።

ግምት፡ ቦርንመዝ 0 - 0 ዌስት ሃም

ኒውካስል ከ ቶተንሃም

ቶተንሃም እንደ ኬን እና ሶን ያሉ ምርጥ ተጫዋቾች ቢኖራቸውም ያሸንፋሉ ብዬ ድጋፌን አልሰጣቸውም። ሰፐርስ የቻምፒየንስ ሊግ ቦታን ያገኛሉ ብዬ አልጠብቅም። አይገባቸውም።

አሁን ያለው የቶተንሃም ደጋፊ ምኞት አርሰናል ዋንጫ እንዳያነሳ እና ሰፐርስ ቻምፒየንስ ሊግ እንዲገባ ይመስለኛል።

ይህ ጨዋታ እስከ አራተኛ ሆኖ ለመጨረስ ለሚደረገው ትግል ወሳኝ ነው። በኒውካስል እና ቶተንሃም መካከል ያለው የነጥብ ልዩነት 3 ብቻ ነው። ኒውካስል ይህን ጨዋታ አሸንፎ አንድ ቀሪ ጨዋታ እያለው ልዩነቱን ወደ 6 ያሳድጋል ብዬ ገምታለሁ።

ግምት፡ ኒውካስል 3 - 1 ቶተነሃም

ኤፍኤ ዋንጫ

ማንቸስተር ሲቲ ከ ሼፊልድ ዩናይትድ

ሼፊልድ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ለመመለስ ከጫፍ ደርሷል። በቻምፒንሺፑ ጥሩ አቋም ላይ ነው ያለው። በዌምብሌ የሚኖራቸው ታሪክ ግን ሌላ ነው የሚሆነው።

በኤፍኤ ዋንጫ ጥሩ ተጉዘዋል። እሁድ ግን የጉዟቸው ማብቂያ ይሆናል። ሲቲ ጨዋታውን በሰፊ የጎል ልዩነት ያሸንፋል።

ግምት፡ ሲቲ 5 - 0 ሼፊልድ

ብራይተን ከ ማንቸስተር ዩናይትድ

ዩናይትድ በመጨረሻ የሉጉ ጨዋታ ፎረስትን አሳማኝ በሆነ መንገድ አሸንፏል። በዩሮፓ ሊግ ደግሞ በተቃራኒው በራሱ ተጫዋቾች ስህተት ተሰናብቷል።

ቁልፍ የተከላካይ መስመር ተጫዋቾቹን በጉዳት ያጣው ዩናይትድ በዌምብሌ ፈተና እንደሚገጥመው እሰጋለሁ።

ቼልሲን በአሳማኝ ሁኔታ ያሸነፈው ብራይተን ዩናይንድን እንደሚያሸንፍ እጠብቃለሁ።

ግምት፡ ብራይተን 3 - 2 ዩናይትድ