በረራ ላይ ያለን አውሮፕላን የአደጋ ጊዜ መውጫ በር ካልከፈትኩ ብሎ ግብግብ የፈጠረው ተሳፋሪ ተከሰሰ

ታትሟል

በዩናይትድ አውሮፕላን ተሳፋሪ የነበረ ግለሰብ በበረራ ጊዜ የአደጋ ጊዜ መውጫ በር ካልከፈትኩ ብሎ ግብግብ በመፍጠሩ ተከሰሰ።

ግለሰቡ የአደጋ ጊዜ መውጫ በር ለመክፈት ከመታገሉ ባሻገር አንድ የበረራ አስተናጋጅን በሰባራ ሹካ ለመውጋት ሞክሯል።

የ33 ዓመቱ ፍራንሲስኮ ስቬሮ ቶሬስ ይህን ድርጊት የፈጸመው ከሎስ አንጀለስ ወደ ቦስተን በነበረ አንድ የአገር ውስጥ በረራ ላይ ነው።

ድርጊቱ በመንገደኞች ላይ ከፍተኛ ፍርሃትን ፈጥሮ ነበር ተብሏል።

አውሮፕላኑ በቦስተን ሎጋን ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ እንዳረፈ ፍራንሲስኮ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተወስዷል።

የዩናይትድ አየር መንገድ ንብረት በሆነው አውሮፕላን ይህ ግርግር ሲከሰት አውሮፕላኑ ለማረፍ አንድ ሰዓት ገደማ ቀርቶት ነበር።

የአውሮፕላኑ የአደጋ ጊዜ መውጫ በር ለመክፈት የሚያስችለውን የመክፈቻ ዘንግ ማላላት የቻለው ይህ ግለሰብ በበረራ አስተናጋጅና በተሳፋሪዎች ጥረት ከድርጊቱ እንዲታቀብ ባይደረግ ኖሮ ከፍተኛ አደጋ ሊያደርስ ይችል ነበር ተብሏል።

ሰውየው ይህን ሲያደርግ ምን አስቦ እንደሆነ ለጊዜው የተባለ ነገር የለም።

የበረራ አስተናጋጇ ግሰለቡን ለማስቆም ስትጥር ‘ግለሰቡ በአውሮፕላኑ ውስጥ ካሜራ አለ እንዴ?” ሲል እንደጠየቃት ተዘግቧል።

የአደጋ ጊዜ መውጫ በር ሙሉ በሙሉ ከመከፈቱ በፊት በሩ እንዲላላ የሚያደርገውን ዘንግ ነው ግለሰቡ የከፈተው።

አስተናጋጇም ወደ አውሮፕላን አብራሪው ‘ችግር ስለተፈጠረ በፍጥነት አውሮፕላኑን እንዲያሳርፍ” የሚጠይቅ መልእክት ልካለት ነበር ተብሏል።

ግለሰቡ የአስተናጋጇን ሪፖርት ማድረግ ተከትሎ ማጅራቷ አካባቢ በስባሪ ሹካ ሦስት ጊዜ እንደወጋት ክሱ ያስረዳል።

ሹካው እንደ ጦር መሣሪያ እንዲያገለግለው ግለሰቡ መጸዳጃ ቤት ገብቶ እንዳበጃጀውም በሰጠው የእምነት ክህደት ቃል ተናግሯል።

በኋላ ላይ ተሳፋሪዎች ተረባርበው ግለሰቡን በቁጥጥር ሥር እንዲውል አድርገዋል።

ግለሰቡ አውሮፕላኑ ገና ለመነሳት እየተንደረደረ ሳለ አጠገቡ ያለን ተሳፋሪ “የአደጋ ጊዜ መውጫ በሩ የት ነው ያለው?” ብሎ ሲጠይቅ ነበር ተብሏል።

በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ሚዲያ እንደዘገበው ከሆነ ግለሰቡ ለምን ይህን ድርጊት እንደፈጸመ ለፖሊስ በሰጠው ቃል ‘የበረራ አስተናጋጇ ልትገድለኝ እንደነበረ ጠርጥሬ ነው፤’ ብሏል።

ግለሰቡ ከእንግዲህ በዩናይትድ አውሮፕላን ዕድሜ ዘመኑን እንዳይሳፈር ገደብ ተጥሎበታል።

የፍትሕ ሚኒስትር እንደሚለው ግለሰቡ የፈጸመው አይነት ድርጊት በሚበር አውሮፕላን ላይ መፈጸም ዕድሜ ልክ ሊያሳስር ይችላል፤ ወይም ደግሞ 5 ዓመት የእንቅስቃሴ ገደብ የሚጣልበት እስር እንዲሁም 250ሺህ ዶላር ቅጣትን ሊጣልበት ይችላል።

ግለሰቡ ይህን ድርጊት ከፈጸመ በኋላ ለያዥ ለገናዥ በማስቸገሩ ስድስት ግዙፍ ተሳፋሪዎች እጅና እግሩን ጠፍረው በመያዝ አውሮፕላኑ እስኪያርፍ ድረስ ላዩ ላይ ተከምረውበት ነው ማስታገስ የቻሉት ብሏል ሲቢኤስ።