የተመድ ባለሥልጣን በኢትዮጵያ ላይ ያወጡትን መግለጫ እንዲያስተባብሉ መንግሥት ጠየቀ

የፎቶው ባለመብት, MoFA of Ethiopia
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ልዩ አማካሪ በአገሪቱ ያለውን ሁኔታ አስመልክተው ያወጡት መግለጫ ኃላፊነት የጎደለው ነው በማለት እንዲያስተባብሉ የኢትዮጵያ መንግሥት ጠየቀ።
የኢትዮጵያ መንግሥት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ ባለው ቋሚ መልዕክተኛ በኩል ባወጣው መግለጫ ልዩ አማካሪዋ አሊስ ዋይሪሙ ባወጡት መግለጫ በአገሪቱ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ በትክክል የማያሳይ መሆኑን በመግለጽ ማስተባበያ እንዲሰጡ ጠይቋል።
የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ፀሐፊ የዘር ማጥፋት ወንጀል መከላከል ልዩ አማካሪ የሆኑት አሊስ ዋይሪሙ ማክሰኞ ዕለት ባወጡት መግለጫ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በመንግሥት ወታደሮች እና በአካባቢ ታጣቂዎች መካከል በቀጠለው ውጊያ ምክንያት የዘር ማጥፋት ወንጀል እንዲፈጸም የሚያስችሉ ሁኔታዎች አሉ በማለት አስጠንቅቀዋል።
በትግራይ፣ በአማራ፣ በአፋር እና በኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ “ከፍተኛ የዘር ማጥፋት እና ተያያዥ ወንጀሎች የመከሰት አደጋ አለ” ያሉት ልዩ አማካሪዋ፣ በኢትዮጵያ እየተከሰቱ ያሉ ያሏቸውን ችግሮች በተመለከተ የሚወጡ ሪፖርቶች “በጣሙን የሚረብሹ እና እርምጃ እንዲወሰድ ጥሪ ማቅረብ የሚያስፈልጋቸው ናቸው” ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የመንግሥታቱ ድርጅት ቋሚ መልዕክተኛው በኩል ሐሙስ ጥቅምት 01/2016 ዓ.ም. ለዚሁ መግለጫ በሰጠው ምላሽ፣ ልዩ አማካሪዋ መግለጫውን ለማውጣት በተገቢው ሁኔታ ምርመራ ሳይደረግ ተዘጋጅቷል ያለውን በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች የባለሙያዎች ቡድን ያወጣውን ሪፖርት መጠቀማቸውን በመግለጽ ወቅሷል።
በዚህም የሰብአዊ መብቶች መርማሪ ኮሚሽኑ በተገቢ በማስረጃ ያልተደገፈ እና በኢትዮጵያ መንግሥት ተቀባይነት የሌለውን ሪፖርት መሠረት በማድረግ አማካሪዋ “አባባሽ፣ ኃላፊነት የጎደለው እና ግድየለሽ” ያለውን መግለጫ በማውጣታቸው የኢትዮጵያ መንግሥት ማዘኑን መግለጫው አስፍሯል።
ጨምሮም አሊስ ዋይሪሙ ለሁለት ዓመት የተካሄደውን ጦርነት አስመልክቶ በመግለጫቸው ላይ የሰጡትን አስተያየት አጥብቆ ተችቶታል።
አማካሪዋ በመግለጫቸው ግጭትን ለማስቆም ከአንድ ዓመት በፊት የተደረሰው ስምምነት ውጤት እንዳላስገኘ ጠቅሰው፤ ደም አፋሳሽ ግጭቶች በቀጠሉበት ሁኔታ እየጨመሩ የሚሄዱ የጭፍጨፋ ክሶች፣ የጦር ወንጀሎች እና በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች በአገሪቱ ውስጥ እየተፈጸሙ ነው ብለዋል።
በመንግሥታቱ ድርጅት የኢትዮጵያ መልዕክተኛ ይህንን አስተያየት በመተመለከተ በሰጠው ምላሽ፣ ስምምነቱ በሰሜን ኢትዮጵያ የጦር ማሳሪያ ድምጽ እንዳይሰማ ማድረጉን በመግለጽ፣ መንግሥት የፕሪቶሪያው ስምምነት ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ እንዲሆን ቁርጠኛ መሆኑን ገልጿል።
ለዚህም ኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ሥርዓትን በመዘርጋት ተጠያቂነት እና ፍትሕ እንዲሰፍን ለማድረግ የሚያስችለውን ሥራ በማከናወን በመጨረሻው ደረጃ ላይ ትገኛለች ያለ ሲሆን፣ አክሎም በአገሪቱ ያሉ ቅሬታዎች በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት አገር አቀፍ የምክክር ጥረት ተጀምሯል ብሏል።
የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ፀሐፊ ልዩ አማካሪ በመግለጫቸው ላይ የፕሪቶሪያው ስምምነት ስኬታማ አልሆነም ማለታቸው ያስቆጣው የኢትዮጵያ መንግሥት አስተያየቱ “ሐሰት” መሆኑን በመግለጽ “አገሪቱ ሰላምን ለማጠናከር ከምታደርገው ጥረት በተቃራኒ የቆመ በመሆኑ ልዩ አማካሪዋ ይህንን የተሳሳተ መግለጫ” ማስተባበል አለባቸው ብሏል።
የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ፀሐፊ የዘር ማጥፋት ወንጀል መከላከል ልዩ አማካሪ የሆኑት አሊስ ዋይሪሙ ባወጡት መግለጫ ላይ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ውስጥ ግድያ፣ የመብት ጥሰት፣ መድፈር እና ጾታዊ ጥቃቶች እንደሚፈጸሙ አመልክተው፣ የሚደርሷቸው ሪፖርቶች እንዳሰሰባቸው ገልጸዋል።
ትግራይ ውስጥ ለሁለት ዓመታት ሲካሄድ የቆየው የእርስ በርስ ጦርነት በድርድር ከማብቃቱ በፊት ሁሉም የጦርነቱ ተሳታፊ ወገኖች ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መካሄዳቸው በተለያዩ ሪፖርቶች የቀረበ ሲሆን፣ የመንግሥታቱ ድርጅትም በአገሪቱ የተከሰቱ የመብት ጥሰቶችን የሚመረምር የባለሙያዎች ኮሚሽን አቋቁሞ እንደነበር ይታወሳል።















