ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የእስራኤል ኃይሎች ከጄኒን እየወጡ መሆኑ ተገለጸ
የእስራኤል ወታደሮች በግዳጅ በተያዘው ዌስት ባንክ ከሚገኘው ጄኒን የስደተኞች መጠለያ መውጣት መጀመራቸውን ወታደራዊ ምንጭ ጠቆመ።
ይህም ለሁለት ቀናት በጄኒን የቆየው ኦፕሬሽን ማብቂያ ነው ተብሏል።
በእነዚህ ቀናት 12 ፍልስጤማውያን እና አንድ እስራኤላዊ ወታደር ተገድለዋል።
በጄኒን የስደተኞች ማቆያ ተኩስና ፍንዳታ ሲሰማ ቆይቷል።
የእስራኤል መከላከያ እንደሚለው፣ በጋዛ ሰርጥ የሚገኙ የፍልስጤም ታጣቂዎች ወደ እስራኤል ያስወነጨፏቸው አምስት ሮኬቶች አግኝተዋል።
ለዚህ ጥቃት ወዲያው ኃላፊነቱን የወሰደ አካል አልነበረም።
የፍልስጤም የጤና ኃላፊዎች እንዳሉት አንድ ፍልስጤማዊ በእስራኤል ኃይሎች ሲገደል፣ ይህም ከሰኞ ጀምሮ የተገደለ 12ኛው ሰው ነው።
የፍልስጤም ወታደሮች በበኩላቸው ውጊያ ላይ የነበረ ወታደር በስደተኞች ማቆያው ተገድሏል።
ጋዛን የሚያስተዳድረው ሀማስ እንዳለው እስራኤል በጄኒን ላካሄደችው ኦፕሬሽን ምላሽ በእስራኤል መኪና ግጭትና የስለት ጥቃት ተፈጽሟል።
ጥቃቱን የፈጸመው ፍልስጤማዊ በአንድ እስራኤላዊ ዜጋ ነበር የተገደለው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ “ጥቃቱ ከሽብር ውጊያችን አያሰናክለንም” ብለው በጄኒን እያካሄዱ ያሉት ኦፕሬሽን “እየተገባደደ” እንደሆነ ተናግረዋል።
በሳምንቱ መግቢያ ነበር ጥቃት መሰንዘር የጀመሩት።
ሀማስን ጨምሮ የተለያዩ ታጣቂዎችን ዒላማ ያደረገ የሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ጥቃት ተፈጽሟል።
በስደተኞች ማቆያው ከሚገኙ ታጣቂ ፍልስጤማውያን ጋር የተኩስ ልውውጥም ተደርጓል።
የተባበሩት መንግሥታት ሰብአዊ ጉዳዮች ቃል አቀባይ በጄኔቫ ባደረጉት ንግግር ሁኔታው እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል።
“በአየርና በምድር ጥቃቶች ስፋት ሰግተናል። በተለይም ሰው በብዛት በሚኖርበት የስደተኞች ማቆያ የተሰነዘረው የአየር ጥቃት አሳስቦናል” ብለዋል።
የፍልስጤም ጤና ኃላፊዎችን ጠቅሰው እንደተናገሩት፣ የ16 እና 17 ዓመት ታዳጊዎችን ጨምሮ ሦስት ልጆች ከተገደሉት መካከል ናቸው።
መሠረተ ልማት ላይ ውድመት ስለደረሰም የውሃና መብራት አቅርቦት ተቋርጧል።
የዓለም ጤና ድርጅት እንዳለው የፍልስጤም አምቡላንሶች ወደ መጠለያው እንዳይገቡ ተከልክለዋል። ለተጎዱ እርዳታ እንዳይሰጡም ታግደዋል።
ጉዳት ከደረሰባቸው 140 ሰዎች መካከል 30ው በጠና እንደተጎዱም ተገልጿል።
የፍልስጤም የቀይ መስቀል ኃላፊ እንደሚሉት ሕሙማንና አረጋውያንን ጨምሮ 3,000 ፍልስጤማውያን ከድሮን ጥቃት እንዲሸሹ አንድ ምሽት ተሰጥቷቸዋል።
ከማቆያው እንዲወጡ ከተደጉ መካከል አንደኛው ለቢቢሲ እንደገለጹት፣ እስራኤላውያን ወታደሮች በአንድ ክፍል ውስጥ እንዲቆዩ ተደርገዋል።
“የእስራኤል ወታደሮች መጥተው ከበውን ነበር። አሁን ወጥተናል። ካምፑ ውስጥ ቀርተን የነበርነው እኛ ብቻ ነበርን። በጣም ከባድ ነበር” ይላሉ።
“ድሮን ሲተኩስብን ነበር። አልበላንም አልጠጣንም ነበር። ተዳክመናል” ሲሉም አክለዋል።
የእርዳታ ተቋማት እንዳሉት የእስራኤል ወታደሮች መንገድ እያፈረሱ ሲጓዙ ነበር።
ጄኒን የስደተኞች ማቆያ የወጣት ፍልስጤማውያን ታጣቂዎች ማዕከል እየሆነ ነው።
ወጣቶቹ ዌስት ባንክን በሚያስተዳድረው ያረጀ የፍልስጤም አመራርና እና በእስራኤል የግዳጅ ይዞታ የተቆጡ ናቸው።
የፍልስጤም ጠቅላይ ሚኒስትር ሞሐመድ ሻታያህ፣ እስራኤል ራሷን የመከላከል መብት አላት የሚሉ ወገኖችን አጥበው ተችተዋል።
“እስራኤል በመሬታችንና ሕዝባችን በግዴታ ይዞታ ያስፋፋች መሆኗን ዓለም ያውቃል። መጠለያ ጣቢያዎችን፣ መሠረተ ልማትን መኖሪያን በኃይል ማፍረሷ መኮነን አለበት። ንጹኃንን መግደሏ ሊወገዝ ይገባል። ፍልስጤማውያን ራሳቸውን የመከላከል መብት አላቸው። ወራሪ ኃይል መብት አለው ሊባል ግን አይችልም” ብለዋል።