በሩሲያ የኤስቶኒያ አምባሳደር ከአገሪቱ እንዲወጡ ታዘዙ

የኤስቶኒያ አምባሳደር ማርገስ ላይድሬ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, በሩሲያ የኤስቶኒያ አምባሳደር ማርገስ ላይድሬ
ታትሟል

በሩሲያ የኤስቶኒያ አምባሳደር ማርገስ ላይድሬ ‘ሩሲያ ጠል’ ናቸው ብሎ የከሰሰው ክሬምሊን አምባሳደሩ በቀናት ውስጥ እንዲወጡ አዘዘ።

የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባወጣው መግለጫ ኤስቶኒያ ከሞስኮ ጋር ያላትን ግንኙነት “ሆነ ብላ አጠልሽታለች” ሲል ከሷል።

ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች ወዲህ ከአገሯ አምባሳደር ስታባርር የመጀመሪያው ነው።

ኤስቶኒያም በምላሹ የሩሲያን አምባሳደር እንዲወጡ አዛለች።

ሩሲያ ውሳኔውን ያሳለፈችው ኤስቶኒያ ታሊን በተባለው የሩሲያ ግዛት ያለው ኤምባሲ ሠራተኞች መጠን ከ17 ወደ ስምንት ካደረገች በኋላ ነው።

በኤስቶኒያ ወታደራዊ መቀመጫ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን (ኔቶ) የ11 አገራት ወኪሎች ባለፈው ሳምንት መገናኘታቸውን ተከትሎ የአገራቱ ግንኙነት ሻክሯል።

ውይይቱ ዩክሬን በሩሲያ የተወሰዱባትን ግዛቶች ማስመለስን የተመለከተ ነበር።

የላቲቪያ የውጭ ጉዳይም የሩሲያ ወታደር በቀጣዩ ወር እንዲወጡ አዟል። ከሩሲያ ጋር ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በመገደብ ኤስቶኒያን እንደሚደግፍም ገልጿል።

በሩሲያ የኤስቶኒያ አምባሳደር ማርገስ ላይድሬ የተሾሙት እአአ በ2018 ሲሆን፣ ከዚያ በፊት በዩናይትድ ኪንግደም እና ፊንላንድ ሠርተዋል።

በአምባሳደር ምትክ በሚሠራ የዲፕሎማሲ አታሼ የሚተኩ ይሆናል።

ሩሲያ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ባወጣችው መግለጫ “በቅርብ ዓመታት የኤስቶኒያ አመራር ከሩሲያ ጋር ያለውን ግንኙነት እየበጣጠሰ ነው። ሩሲያ ጠል ናቸው። ለአገራችን ያላቸው ጥላቻ ጨምሯል” ብላለች።

የኤምባሲ ሠራተኞች ቁጥር መቀነሰን “ወዳጅነትን የሚያጠለሽ” እርምጃ ብሎ በሁለቱ አገራት ያለውን ግንኙነት እስከነጭራሹ የሚቋረጥበት ደረጃ መቃረቡን ጠቁመዋል።

ሩሲያ በኤስቶኒያ ያሏትን ዲፕሎማቶች ወደ ወኪል አታሼዎች ዝቅ አድርጋለች።