የዩክሬን ምርኮኞችን የያዘች ጄት ድንበር አቅራቢያ መከስከሷን ሩሲያ ገለጠች

የፎቶው ባለመብት, RUSSIAN TELEGRAM
ኢሉሺን-76 የተባለች የሩሲያ ወታደራዊ አውሮፕላን ዩክሬንን በሚያዋስነው ደቡባዊው ቤልጎሮድ ግዛት መከስከሷ ተሰማ።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር እንዳለው አውሮፕላኗ 65 ዩክሬናውያን ምርኮኞችን አሳፍራ ለእስረኞች ልውውጥ ወደ ቤልጎሮድ እያቀናች ነበር።
አውሮፕላኗ አሳፍራቸው ነበር የተባሉት ሰዎች የዩክሬን የጦር ምርኮኞች ስለመሆናቸው ገለልተኛ ማረጋገጫ የለም።
ሪያ ኖቮስቲ የተሰኘው የዜና ወኪል በበኩሉ ስድስት የበረራ ባለሙያዎችን ጨምሮ አውሮፕላኗ 9 ሰዎችን አሳፍራ ነበር ብሏል።
ዩክሬንስካ ፕራቭዳ የተባለው የዩክሬኑ ድረ-ገጽ ደግሞ አውሮፕላኗ ለሩሲያ ኤስ-300 የአየር መቃወሚያ መሣሪያ ሚሳዔሎችን ተሸክማ ነበር ብሏል።
ድረ-ገጹ ስለጦር ምርኮኞች ምንም ያለው ነገር የለም።
ማኅበራዊ ሚድያ ላይ የተሰራጩ ቪዲዮዎች ያብሎኖቮ የተሰኘችው መንደር አቅራቢያ አንድ አውሮፕላን ከተከሰከሰች በኋላ ፍንዳታ እና እሣት እንደተከላት ያሳያል።
ከተማዋ ከቤልጎሮድ 70 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ሲሆን፣ አደጋው የደረሰው በሥፍራው ሰዓት አቆጣጠር ረፋድ 5፡00 ገደማ ነው።
የሩሲያዋ ቤልጎሮድ ግዛት አስተዳዳሪ ቪያቼስላቭ ግላድኮቭ አውሮፕላኗ መኖሪያ ሠፈር አካባቢ መውደቋንና ሁሉም ተሳፋሪዎች መሞታቸውን ገልጠዋል።
አንዳንድ የዩክሬን መገናኛ ብዙኃን መጀመሪያ አውሮፕላኗ በዩክሬን ጦር ተመትታ እንደወደቀች የዘገቡ ሲሆን፣ ነገር ግን ከቆይታ በኋላ እኒህ ዘገባዎች ተሰርዘዋል።
የዩክሬን ጦር ኃይል አባል ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከሆነ ስለአደጋው ሙሉ መረጃ የላቸውም፤ ጉዳዩን ለማጣራት ምርመራ እያካሄዱ ነው።
የሩሲያ ፓርላማ የመከላከያ ኮሚቴ ሊቀ-መንበር የሆኑት አንድሬ ካርታፖሎቭ አንድ ሌላ አውሮፕላን 80 የጦር ምርኮኞችን አሳፍራ እየተጓዘች እንደነበር አሳወቀው ነገር ግን አሁን የበረራ አቅጣጫዋን ቀይራለች ብለዋል።
“አሁን ስለእስረኞች ልውውጥ የምናወራበት ጊዜ አይደለም” ሲሉ ሊቀ-መንበር ካርታፖሎቭ ለአንድ የሩሲያ ቴሌቪዥን ጣቢያ ተናግረዋል።
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቃል-አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ በበኩላቸው ክሬምሊን ስለአደጋው እንደሚያውቅ ተናግረው፤ ነገር ግን ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ኢሉሺን-76 አውሮፕላን መከስከሷ ከተሰማ በኋላ በመላው ዩክሬን የአየር ጥቃት ማስጠንቀቂያ ተሰምቷል።
ከዩክሬን ድንበር 40 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ቤልጎሮድ የዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ በኋላ በርካታ ሰዎች በአየር እና ድሮን ጥቃት ሞተውባታል።
ባለፈው ታኅሣሥ በደረሰ የአየር ጥቃት 25 ሰዎች ተገድለው 100 የሚሆኑ ደግሞ ቆስለዋል። ነገር ግን ዩክሬን ይህን ጥቃት ያደረስኩት ወታደራዊ መሠረተ-ልማቶችን መርጬ ነው ብላለች።
ሩሲያ፤ ዩክሬን ላይ ጦርነት ያወጀችው በአውሮፓውያኑ የካቲት 2022 ሲሆን ጦርነቱ ሁለተኛ ዓመቱን ሊደፍን ቢቃረብም የመቆም አዝማሚያ አላሳየም።
ባለፈው ሳምንት ሩሲያ ከጥቅም ውጭ ከሆነችው ባኽመት አጠገብ የምትገኝ ሥፍራን መቆጣጠሯን አሳውቃለች። ክሬምሊን ተቆጣጠርኩት ያለው ሥፍራ በምሥራቅ ዩክሬን ዶኔስክ ግዛት የሚገኝ ነው።
ዩክሬን ስለዚህ ዜና እስካሁን የሰጠችው አስተያየት የለም።
በተለይ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ሩሲያ በዩክሬን የምታደርሰውን የአየር ጥቃት አጠናክራ የቀጠለች ሲሆን፣ ባለፈው ማክሰኞ በዩክሬን ከተሞች ላይ በደረሰ ጥቃት 18 ሰዎች ሲገደሉ 130 ደግሞ ቆስለዋል።
የዩክሬን መከላከያ ሚኒስትር ሩስቴም ኡሜሮቭ ጦራቸው የጦር መሣሪያ እጥረት እንዳጋጠመው ገልጠው ሩሲያ ባለፉት ወራት ብቻ 600 ሚሳዔሎችን እና ከ1000 በላይ ድሮኖችን ተጠቅማለች ብለዋል።
ዩክሬን በአብዛኛው እየተጠቀመች ያለችው የድሮን ጥቃት ነው።
ባለፈው ሳምንት በሴይንት ፒተርስበርግ ከተማ የደረሰ የድሮን ጥቃት አንድ ግዙፍ የነዳጅ ማመላሻ ጣቢያ መትቷል።
በቅርቡ በዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ አደራዳሪነት ዩክሬን 248 ምርኮኞችን አሳልፋ ስትሰጥ ሩሲያ ደግሞ 230 ምርኮኞችን ለዩክሬን አስረክባለች።
ዩክሬን እንደምትለው ሰላማዊ ዜጎችን ጨምሮ 8 ሺህ ዩክሬናውያን በሩሲያ ቁጥጥር ሥር ይገኛሉ።












