የሲቲ ተጫዋቾችና ደጋፊዎች ዶፍ ዝናብ ሳይገድባቸው ሶስት ዋንጫ እያሳዩ ደስታቸውን ሲገልጡ አመሹ

የሲቲ ተጫዎቾችና ደጋፊዎች ስታቸውን ሲገልጡ

የፎቶው ባለመብት, PA Media

ታትሟል

በሺዎች የሚቆጠሩ የማንቸስተር ሲቲ ደጋፊዎች የቡድናቸውን ታሪካዊ የሶስትዮሽ ዋንጫ መንገድ ላይ ሲያከብሩ ውለዋል።

የሲቲ ተጫዋቾች አናቱ ክፍት በሆነ ተሽከርካሪ ለደጋፊዎቻቸው እጃቸውን ሲያውለበልቡ ታይተዋል።

ከባድ ዝናብ ቢረግጥም አብዛኛዎቹ ተጫዋቾች ካናቴራቸውን አውልቀው እንደ ሕፃን ሲቦርቁ ነበር።

ዝናብ ያልበገራቸው ደጋፊዎች ደግሞ ሰማያዊ ጭስ የሚያበቅል ርችትና የሙዝ ቅርፅ ያለው ፕላስቲክ ሲወዘወዙ አምሽተዋል።

አሠልጣኝ ፔፕ ጉዋርዲዮላ የቴሌቪዥን ‘ሪሞት’ የሚያህል የኩባ ሲጋር ሰክተው ደስታቸውን አጣጥመዋል።

የማንቸስተር ሲቲ ተጫዋቾች መንገድ ላይ ወጥተው ከደጋፊዎቻቸው ጋር ደስታቸውን ለመግለጥ በጊዜ ቢወጡም ዶፍ ዝናብ ጥሎ አስረፍዷቸዋል።

ሲቲ፤ ባለፈው ቅዳሜ ኢንተር ሚላንን በቻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ አንድ ለምንም በመርታት ታሪካዊ ድል ተጎናፅፏል።

ቡድኑ ከዚህ ጨዋታ ቀደም ፕሪሚዬር ሊግና ኤፍ ኤ ዋንጫን አንስቶ ነበር።

የሲቲ ተጫዎቾችና ደጋፊዎች ስታቸውን ሲገልጡ

የፎቶው ባለመብት, PA Media

ሮድሪ በ68ኛ ደቂቃ ባስቆጠራት ጎል የተገባደደው የቻምፒዮንስ ሊግ ድል “ሰማይ ላይ የተፃፈ” ነበር ይላሉ ፔፕ ጉዋርዲዮላ።

በዝናብ የበሰበሱት ጉዋርዲዮላ ሶስት ዋንጫ ከተሸከሙት ደጋፊዎቻቸው ጋር ሲዘሉ ነበር።

ተከላካዩ ሩበን ዲያዝና አጥቂው ኧርሊንግ ሃላንድ ዝናብ ሲያበሰብሳቸው ካናቴራቸውን ካወለቁ ተጫዋቾች መካከል ናቸው።

በሃገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር ምሽት 2፡00 ገደማ የሲቲ ተጫዋቾች ወደተዘጋጀላቸው መድረክ ሲያመሩ ሃላንድ ‘አቧራው ጨሰ’ እያለ የቡድን አጋሮቹን ሲያስጨፍር ታይቷል።

ጉዋርዲዮላ ደጋፊዎች ዝናብና ነፋስ ተቋቁመው መምጣታቸውን አወድሰዋል።

እንግሊዛዊው አማካይ ጃክ ግሪሊሽ “ባለፉት 24 ሰዓታት ያሳለፍኩት ደስታ መቸም የማይረሳ ነው” ብሏል።

“እውነት እላችኋለሁ እስካሁን እንቅልፍ አልወሰደኝም።”

ደስታው በዶፍ ዝናብ ምክንያት ቢዘገይም ደጋፊዎች ግን ዶፉ እስኪያባራ ጥግ ይዘው ጠብቀዋል እንጂ ወደ ቤታቸው እልገቡም።

ማንቸስተር ሲቲ ከጎረቤቱ ማንቸስተር ዩናይትድ ቀጥሎ የፕሪሚዬር ሊጉን፣ ኤፍ ኤ ዋንጫና ቻምፒዮንስ ሊግ ድል በአንድ ውድድር ዘመን ያጣጣመ ብቸኛው ክለብ ነው።

የሲቲ ተቀናቃኝ ዩናይትድ በጌታ አሌክስ ፈርጉሰን ዘመን ይህን ድል ያጣጣሙት በፈረንጆቹ 1999 ነበር።

የሲቲ ተጫዎቾችና ደጋፊዎች ስታቸውን ሲገልጡ

የፎቶው ባለመብት, Reuters