ማንቸስተር ሲቲ የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግን በማንሳት የሶስትዮሽ ዋንጫ ሕልሙን አሳካ

ሲቲ የሶስትዮሽ ዋንጫን ያሳካ ሁለተኛው ክለብ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

የማንቸስተር ሲቲ የረዥም ጊዜ የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ የማንሳት ሕልም እውን ሆኗል።

የጉዋርዲዮላ ልጆች ኢንተር ሚላንን በመርታታ አውሮፓን ከመቆጣጠራቸው በላይ የሶስትዮሽ ዋንጫ ድልን መቀዳጀት ችለዋል።

የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግና ኤፍ ኤ ዋንጫን ቀድሞ ያነሳው ሲቲ፤ ማንቸስተር ዩናይትድ ከዚህ ቀደም በፈረንጆቹ 1999 ያሳካውን ድል መድገም ችሏል።

ሁለቱ የማንቸስተር ከተማ ክለቦች በአንድ የውድድር ዓመት ሦስት ዋንጫ ያነሱ ብቸኛ የእንግሊዝ ክለቦች ናቸው።

የሲቲው ሮድሪ በ68 ደቂቃ አክርሮና ቆልምሞ ወደ መረብ የሰደዳት ኳስ የጨዋታው ብቸኛና አስፈላጊ ጎል ሆናለች።

የጉዋርዲዮላ ልጆች ለወትሮው እንደሚታወቁበት ዓይነት ጨዋታ ማሳየት ባይችሉም ዕድልና ድል ከነሱ ጋር ነበረች።

የኢንተርን ጠንካራ የተከላካይ መስመር መስበር ተስኗቸው የነበሩት ሲቲዎች በመጀመሪያው አጋማሽ ኬቪን ደ ብረይንን በጉዳት ማጣታቸው ስጋት ፈጥሮ ነበር።

ማንቸስተር ሲቲ ሶስት አበይት ዋንጫዎች ማንሳቱ አሠልጣኝ ፔፕ ጉዋርዲዮላን ከታላላቅ የአውሮፓ አሠልጣኞች መሃል ያስቀመጠ ነው።

ሃላንድ በሁሉም ውድድሮች 52 ጎሎች በማስቆጠር የመጀመሪያውን ዓመት ከሲቲ ጋር አጠናቋል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በሁሉም ውድድሮች 52 ጎሎች ያስቆጠረው ሃላንድ በመጀመሪያው ከሲቲ ጋር ታሪክ መሥራት ችሏል

ጉዋርዲዮላ ከዚህ ቀደም ከባርሴሎና ጋር ሁለት ጊዜ የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግን ማንሳት ችሏል።

የኢንተሩ ፌዴሪኮ ዲማርኮ በግንባር የገጫት ኳስ የመረቡን አግዳሚ ነክታ ስትመለስ፤ የሲቲው በረኛ ኤደርሰን የሉካኩን የግንባር ኳስ ማምከን ችሏል።

ነገር ግን ሲቲዎች የ90 ደቂቃ ውጤት እንጂ የአጨዋወት ስልት ያሳሰባቸው አይመስልም፤ ይህንንም አስመስክረዋል።

የሲቲ ተጫዋቾች አሁን ስማቸውን በታሪክ መዝገብ ላይ ማስፈር ችለዋል።

ማንቸስተር ሲቲና ጉዋርዲዮላ የቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ለማግኘት ብዙ ጥረዋል።

ከሁለት ዓመት በፊት በፍፃሜው ከቼልሲ የተገናኙት ሲቲዎች ዋንጫውን በበሐዘን እንባ ቢሰናበቱትም ቅዳሜ ምሽት በኢስታንቡል የደስታ እንባ ረጭተዋል።

ጉዋርዲዮላ ከዚህ ቀደም ተሰካም አልተሳካም የሲቲ ቆይታው ስኬት የሚወሰነው በቻምፒዮንስ ሊግ ድል መሆኑን ተናግሮ ነበር።

በ2009 እና 2011 ከባርሴሎና ጋር የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ባለድል የሆነው ካታላኑ በማንቸስተር ሲቲ ቤትም ስሙን በወርቅ አስፅፏል።

የአቡ ዳቢ ልጥጥ ባለሃብቶች ንብረት የሆኑት ሲቲዎች ምንም እንኳ 115 ሕግጋትን ጥሷል የሚል ክስ ቢቀርብባቸውም አሁን ደስታ እንጂ ሌላ አይታያቸውም።

በ2008 ሲቲን ከገዙት በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ የክለባቸውን ጨዋታ የታደሙት ሼክ መንሱር ክለባቸው ታላቁ የክለብ ዋንጫ ሲያነሳ መመልከት ችለዋል።