ሾልኮ በወጣ የስልክ ንግግር የጦር አዛዣቸውን የተቹት የታይላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ከስልጣን ተነሱ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የታይላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ፓኤቶንግታርን ሺናዋትራ ከካምቦዲያው የቀድሞ መሪ ጋር ያደረጉት የስልክ ንግግር ሾልኮ መውጣቱን ተከትሎ በተፈጠረ ጫና በአገሪቱ ህገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ከስልጣን ተነሱ።

በዚህ የስልክ ንግግር ላይ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር "አጎቴ" ሲሉ ለጠሩት የካምቦዲያ መሪ ሁን ሴን የአገራቸውን የጦር አዛዥ ሲተቹ ይሰማል።

ጠቅላይ ሚኒስትሯ አገራቸው ከካምቦዲያ ያላት የድንበር ውጥረት እየተባባሰ ባለበት ወቅት ሾልኮ የወጣው ይህ የስልክ ጥሪ "ስነ ምግባርን የጣሰ ነው" በሚል ነው ከኃላፊነት እንዲነሱ የተደረጉት።

በካምቦዲያው የቀድሞ መሪ ሁን ሴን ሾልኮ የወጣው ይህ የስልክ ንግግር የጠቅላይ ሚኒስትሯ ስም ያጎደፈ ሆኗል።

ተቺዎቻቸው የሃገሪቱን ጦር አንቋሸዋል ሲሉ እንዲከሷቸው ምክንያት ሆኗል።

ከዚህ ቀደም ከስልጣን እንዲወገዱ የተደረጉት ታክሲን ሺናዋትራ ልጅ የሆኑት ፓኤቶንግታር ከአውሮፓውያኑ 2008 ወዲህ በፍርድ ቤት ከስልጣናቸው የተባረሩ አምስተኛዋ ጠቅላይ ሚኒስትር ናቸው።

ዘጠኝ ዳኞች ያሉት የአገሪቱ ህገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት አርብ ዕለት በዋለው ችሎት የጠቅላይ ሚኒስትሯ ድርጊት ስነ ምግባርን የጣሰ ነው በሚል ሰባት ለሶስት በሆነ ድምጽ ከስልጣናቸው እንዲነሱ ውሳኔ ላይ ደርሷል።

ፍርድ ቤቱ የስልክ ጥሪው "በግል ግንኙነት ላይ ተመስርቶ፤ ካምቦዲያን ያስቀደመ ስለመሆኑ ማሳያ ነው" ሲል ጠቅላይ ሚኒስትሯ በበኩላቸው "ሰላምን ለማምጣት የተደረገ ድርድር" ነው ብለው ቢከራከሩም አልተቀበላቸውም።

የጠቅላይ ሚኒስትሯ ድርጊት "ከአገራቸው ጥቅም ይልቅ ካምቦዲያን አስቀድመዋል" የሚል ጥርጣሬ በህዝቡ ላይ አስፍነዋል ተብሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትሯ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ቢቀበሉም ግጭትን በመቀልበስ ህይወት ለመታደግ ያደረጉት ሙከራ እንደሆነ በሰጡት አጭር ጋዜጣዊ መግለጫ አስረድተዋል።

በታይላንድ እና በካምቦዲያ መካከል ያለው የድንበር ውጥረት ወደ አምስት ቀናት ግጭት አምርቶ በርካታ ሰዎች ተገድለው እንዲሁም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ቀያቸውን ጥለው መሰደዳቸውን ተከትሎ ነው የስልክ ንግግሩ ሾልኮ የወጣው።

በታይላንድ ለሁለት አስርት ዓመታት ፖለቲካውን በበላይነት የተቆጣጠሩት ሺናዋትራ ጎሳ አባል የሆኑት ፓኤቶንግታር፣ የስልጣን ዘመናቸው ሳይጠናቀቅ ከኃላፊነት እንዲነሱ የተደረጉ ሶስተኛዋ ፖለቲከኛ ይሆናሉ።

ከሳቸው በፊት የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ስሬታ ታቪሲን በእስር ላይ የነበሩትን የቀድሞ ጠበቃ በካቢኔያቸው በመሾማቸው ከስልጣን እንዲነሱ ተደርገዋል።

የ39 ዓመቷ ጠቅላይ ሚኒስትር በአገሪቷ ታሪክ ስልጣን የተቆናጠጡ በዕድሜ ትንሽዋ እንዲሁም ከአክስታቸው ይንግሉክ ሺናዋትራ በኋላ ሁለተኛዋ ሴት ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትሯ በአውሮፓውያኑ 2021 ሲሆን ፔው ታይ የተባለውን ፖርቲ የተቀላቀሉት ከሁለት ዓመት በኋላም መሪ ሆነዋል።

የሳቸው ተተምኪም በፓርላማ የሚመረጥ ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትሯ የሚመሩት ጥምር መንግሥት ቁልፍ የወግ አጥባቂ ፓርቲ ከጥቂት ሳምንታት በፊት መውጣቱን ተከትሎ በጥቂት አብላጫ ለመምራት እየተንገታገተ ይገኛል።

የአገሪቱን መንግሥት ከጀርባ ሆነው ያሽከረክሩታል የሚባሉት አባታቸው በፖለቲካው ውስጥ የገቡትን እሰጣገባ ጋር እየታገሉ ባሉበት ወቅት ነው የፍርድ ቤቱ ውሳኔ የተላለፈው።

አባትየው ከዘጠኝ ዓመታት በፊት ለደቡብ ኮሪያ ጋዜጣ በሰጡት ቃለ መጠይቅ የታይላንድን ንጉሳዊ ስርዓት ተሳድበዋል በሚል ክስ ተመስርቶባቸዋል።

ከ15 ዓመታት ግዞት በኋላ በአውሮፓውያኑ 2023 ወደ ታይላንድ የተመለሱት አወዛጋቢው የፖለቲካ መሪ በአገሪቱ አፋኝ በሚባለው 'ሌሴ ማጀስቲ' ህግ ክስ ከተመሰረተባቸው ታዋቂ ሰዎች መካከል ዋነኛው ናቸው።