ኢንስታግራም ወላጆች ልጆቻቸውን ለመቆጣጠር የሚያስችላቸውን ዘዴ አስተዋወቀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኢንስታግራም ባለቤት ሜታ በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ውስጥ ባለው መድረኩ ላይ ወላጆች ቁጥጥር የሚያደርጉበት አዲስ ዘዴ አስተዋወቀ።
ይህ ዘዴ በቀን ከ15 ደቂቃ እስከ 2 ሰዓት ያለ የጊዜ ገደብ የማስቀመጥ አማራጭን የሚያካትት ሲሆን የተቀመጠው የጊዜ ገደብ ሲጠናቀቅ በመተግበሪያው ላይ ጥቁር ስክሪን እንዲታይ ያደርጋል።
ከዚህም በተጨማሪ ወላጆች ልጆቻቸው እረፍት የሚያደርጉበትን ሰዓት ማስቀመጥ፣ልጆቻቸው የሚጽፉባቸውን ገጾች እና ያንን ለምን እንዳደረጉ ማየት ይችላሉ።
ከዚህም ባሻገር ግዙፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያ በመላው ዓለም ቨርቹዋል ሪያሊቲ [እውነታን ዓይናችን ላይ በሚደረግ መሣሪያ የሚከስት] ይዘቶችን ማዳመጥ የሚያስችሉ ሄድሴት [ማዳመጫዎች] ላይ የወላጆች መከታተያ እየሠራ ነው።
በዩኬ ባስተዋወቀው አዲሱ መቆጣጠሪያው ላይ ወላጆች ልጆቻቸውን ለመቆጣጠር የሚያስችላቸውን ዘዴ እንዲሰራ እንዲያደርጉ መጋበዝ ይችላሉ። ከዚህ ቀደም ይህንን ግብዣ መላክ የሚችሉት ወጣቶቹ ብቻ ነበሩ።
የግብይት ፈቃዶችን መስጠት፣ መተግበሪያን ማገድ [ብሎክ ማድረግ] እንዲሁም የልጆቻቸውን የጓደኞች ዝርዝር ማየትም ያስችላል።
በሙከራ ላይ ያለ ሌላ የኢንስታግራም ገጽታም አለ። ይህ የልጆችን ትኩረት ለመሳብ የሚረዳ ሲሆን ታዳጊዎች በተደጋጋሚ ተመሳሳይ ነገሮችን የሚፈልጉ ከሆነ የተለያዩ አርዕስተ ጉዳዮችን እንዲመለከቱ ያስተዋውቃል።
ይህ የኢንስታግራም ዘዴ በአሜሪካ የተዋወቀው ባለፈው መጋቢት ወር ላይ ነው።
ኢንስታግራም እድሜያቸው ከ13 ዓመት በላይ ለሆኑ ወጣቶች የተዘጋጀ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረክ ነው።
ሜታ እንደሚለው ቨርቹዋል ሪያሊቲ ይዘቱም የተዘጋጀው ለታዳጊዎችና ከዚያ በእድሜ ከፍ ላሉ ሰዎች ነው። ይሁን እንጂ ሁለቱንም መድረኮች የሚጠቀሙ ከተቀመጠው የእድሜ ክልል የሚያንሱ ሕጻናት አሉ።
እአአ በ2021 ኢንስታግራም እድሜያቸው ከ13 ዓመት በታች ለሆኑ ህጻናት የኢንስታግራም ገጽ ለመክፈት የነበረውን ዕቅድ መተዉ ይታወሳል።
ኢንስታግራምን ጨምሮ ፌስቡክንና ዋትስአፕን የሚያስተዳደርው ሜታ፣ ታዳጊዎች ኢንስታግራም ጭንቀትና ድብታ ፈጥሮብናል ሲሉ መውቀሳቸውን በሰራው ጥናት ቢደርስበትም የጥናቱን ውጤት ይፋ ሳያደርግ በድብቅ ይዞታል ሲል ባለፈው ዓመት ዎል ስትሪት ጆርናል ዘግቦ ነበር።
ኢንስታግራም ግን ዘገባው በተወሰኑ የጥናት ውጤቶች ላይ ያተኮረና የድርጅቱን ገጽ ያጠለሸ ነው ሲል አጣጥሎታል።
እአአ በ2017 የ14 ዓመቷ ሞሊይ ሩስል በኢንስታግራም ገጽ ላይ ራስን ስለመጉዳትና ስለማጥፋት የሚያሳዩ ይዘቶችን ከተመለከተች በኋላ ራሷን አጥፍታለች።
እአአ በየካቲት 2021 በተደረገ ምርመራ መርማሪው፣ ሞሊይ በመጨረሻዎቹ የሕይወቷ 6 ወራቶች የኢንስታግራም ገጿን በቀን ከ120 ጊዜ በላይ እንደተጠቀመች መስማታቸውን ተናግረዋል።
ኢንስታግራም ይህንን ተከትሎ በሰጠው መግለጫ “መተግበሪያው ራስን መጉዳትን ወይም ራስን ማጥፋትን የሚያበረታታ ይዘትን አይፈቅድም። እንደዚህ ዓይነት ይዘት ያላቸውን ጽሁፎችና መረጃዎችንም ያስወግዳል” ብሏል።












