ሰሜን ኮሪያ ለሩሲያ መሳሪያ እያቀረበች ነው የሚለውን ክስ አስተባበለች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ሰሜን ኮሪያ ለሩሲያ መሳሪያ እየሸጠች ነው የሚለውን የአሜሪካ ሪፖርት አስተባበለች።
ሩሲያ የጦር መሳሪያ ለማከማቸት ወደ ሰሜን ኮሪያ ፊቷን አዙራለች የሚለውን የአሜሪካ ሪፖርት ተከትሎም ነው ሰሜን ኮሪያ ይህንን ምላሽ የሰጠችው።
ሰሜን ኮሪያ ለሩሲያ መሳሪያ ሸጣ እንደማታውቅ እንዲሁም ለወደፊቱም እቅድ እንደሌላት ገልጻለች።
የአሜሪካ ባለስልጣናት ሩሲያ ከሰሜን ኮሪያ ሮኬቶችን እና ከባድ መሳሪያዎችን ገዝታ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።
ከሰሜን ኮሪያ በተጨማሪ ከኢራን ጦር መሳሪያ ግዢ ፈፅማለች የተባለችው ሩሲያ የምዕራቡ ዓለም ማዕቀብ ሩሲያ በዩክሬን የምታደርገውን ጥረት እያደናቀፈ መሆኑን ያሳያል ብለዋል።
ሩሲያ የጦር መሳሪያ ግዢ ፈፅማለች የሚለውን ሪፖርት አስተባብላለች።
በሁለቱ ኃገራት መካከል የሚደረግ ማንኛውም የጦር መሳሪያ ልውውጥ የተባበሩት መንግሥታትን ማዕቀብ የሚጥስ ነው።
የሰሜን ኮሪያው የመንግሥት ሚዲያ ኬሲኤንኤ ላይ ሐሙስ እለት በቀረበው መግለጫ በሰሜን ኮሪያ መከላከያ ሚኒስቴር ስማቸው ያልተጠቀሰ አንድ ባለስልጣን “ከዚህ በፊት የጦር መሳሪያዎች ወደ ሩሲያ ልከን አናውቅም ለወደፊቱም የመላክ እቅድ የለንም” ብለዋል።
አሜሪካ እና ሌሎች “ጠላት ኃይሎች” ብለው የጠሯቸው አካላት ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ሴራ ባዘለ መልኩ አሉባልታ እያሰራጩ ነው ሲሉ ከሰዋል።
በያዝነው ወር የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እንዳሉት ሩሲያ ከሰሜን ኮሪያ የገዛችው “ሮኬቶችና ከፍተኛ የከባድ መሳሪያዎችን” እንደሆነም ጠቅሰዋል።
ሆኖም የአሜሪካ የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ቃለ አቀባይ ጆን ኪርቢ ግዥዎቹ ገና እንዳልተጠናቀቁ እና የጦር መሳሪያዎች በዩክሬን ጦርነት ውስጥ ጥቅም ላይ ስለመዋላቸው የሚያሳይ ምንም ዓይነት ማስረጃም እንደሌለም ከማሳሰቢያ ጋር ገልጸዋል።












