የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ዓለም ሩሲያን እንዲቀጣ ተማጸኑ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘሌንስኪ ሩሲያ ሉዓላዊ አገሬን በመውረሯ ዓለም ተገቢውን ቅጣት እንዲቀጣት ያሻል ሲሉ ተናገሩ።
ዘሌንስኪ ይህን ያሉት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ነው።
ፕሬዝዳንቱ ቀደም ብሎ በተቀዳና ለጉባኤተኛው ባስተላለፉት የቪዲዮ መልእክት ሩሲያን የሚዳኝ ልዩ የጦር ፍርድ ቤት እንዲቋቋም፣ የጦር ወንጀል የፈጸሙትም ለፍርድ እንዲቀርቡ ጠይቀዋል።
አገራት ለዩክሬን ተጨማሪ የጦር መሣሪያ እርዳታ እንዲያደርጉ፣ ወራሪዋን ሩሲያን ደግሞ አይቀጡ ቅጣት እንዲቀጡ የጠየቁ ሲሆን ወደ ሰላም ሊወስድ የሚችል ያሉትን ሐሳብም ለጉባኤው አቅርበዋል።
ዘሌንስኪ ንግግራቸውን ሲጨርሱ ከጉባኤተኛው ደማቅ ጭብጨባ ተችሯቸዋል።
የፕሬዝዳንት ዘሌንስኪ ንግግር በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የተላለፈው ቪላድሚር ፑቲን 300 ሺህ ለሚሆኑ ተጠባባቂ ወታደሮቻቸው የዝመቱ ጥሪን ባስተላለፉበት ዕለት ነው።
የቭላድሚር ፑቲን የዝመቱ ጥሪ በሩሲያ ባልተለመደ ሁኔታ የሕዝብ ተቃውሞ ገጥሞታል።
የተወሰኑ ዜጎችንም አደባባይ እስከመውጣት አድርሷቸዋል።
ፕሬዝዳንት ዘሌንስኪ ‘የፑቲን አዲሱ የክተት ጥሪ የሚነግረን ነገር ቢኖር ሰውዬው ለሰላም ምንም ቦታ እንደሌላቸው ነው’ ብለዋል።
ሩሲያ በኃይል በያዘቻቸው የዩክሬን ግዛቶች ሕዝበ ውሳኔ ለማድረግ ዕቅድ ይዛለች።
ይህም ነዋሪዎች የሩሲያ አካል እንሁን በሚለው ላይ ድምጽ እንዲሰጡ የሚያስችል ነው።
ይህን የሩሲያን ዕቅድ ፕሬዝዳንት ዘሌንስኪን ጨምሮ በርካታ የምዕራብ መንግሥታት አውግዘውታል።
በዚህ የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ዘሌንስኪ በቅርብ ጦራቸው መልሶ በያዛት የሰሜን ምሥራቅ ከተማ አዝዮም የተገኘውን የ445 ሰዎች የጅምላ መቃብርንም አንስተዋል።
በአዝዮም ከተማ ሩሲያ የጦር ወንጀል እንደፈጸመችም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።
ከተገደሉት ውስጥ የተወሰኑት የወንድ የዘር ፍሬያቸው እንዲሰለብ ተደርገው መገኘታቸውን ለጉባኤተኛው አስረድተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ፕሬዝዳንት ዘሌንስኪ ሩሲያ ከጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባልነት እንድትሰረዝም ጥያቄ አቅርበዋል።
ባሳለፍነው ቅዳሜ የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ፖሊሲ ኃላፊ ጄሴፍ ቦሬል ሩሲያ ላይ አዲስ ማዕቀብ እንደሚጣል ተናግረው ነበር።
ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ በመጨረሻ ይህን ንግግር በአካል ሳይሆን በቪዲዮ ካሉበት ለማሰራጨት ፍቃድ የሰጧቸውን የ101 ዓለም አገራት አመስግነዋል።
በአንጻሩ የሩሲያን ወረራ ያላወገዙና አንዲት ሉአላዊት አገር ስትወረር ገለልተኝነትን የመረጡ አገራትን ደግሞ አውግዘዋል።
ይህ በእንዲህ ሳለ ሩሲያና ዩክሬን እስረኞችን በመለዋወጥ ረገድ የተሳካ ሥራ መሥራታቸው ታውቋል።
በዚህ ስኬታማ በተባለው የእስረኞች ልውውጥ 215 ወታደሮች ከሩሲያ ወደ ዩክሬን የተመለሱ ሲሆን ከነዚህ መሀል 10 የሚሆኑት የሌሎች አገር ዜጎች ናቸው።
በአንጻሩ 55 የሩሲያ ወታደሮች ወደ አገራቸው ሩሲያ የተወሰዱ ሲሆን የፑቲን ወዳጅ ናቸው የሚባሉት ፖለቲከኛ ቪክቶር ሜድቬቹክም ለሩሲያ ተሰጥተዋል።
እኒህ ፖለቲከኛ በዩክሬን በአገር ክህደት ወንጀል ተከሰው እንደነበር ይታወሳል።












