ፍቅረኛውን የገደለው እና ከኬንያ ፖሊስ ጣቢያ አምልጦ የነበረው አሜሪካዊ ታዳኝ ተያዘ

የፎቶው ባለመብት, DCI Kenya
ፍቅረኛውን በአሜሪካ ገድሎ የሸሸው እና ከኬንያ ፖሊስ ጣቢያ አምልጦ የነበረው አሜሪካዊ ታዳኝ በቁጥጥር ስር ዋለ።
የ41 ዓመቱ ኬልቪን ካንጌቴ በአሜሪካ ፍቅረኛውን ገድሎ ወደ ኬንያ የሸሸው ጥቅምት ወር ላይ ነበር።
ከሁለት ሳምንት በፊትም በመዲናዋ ናይሮቢ ከሚገኝ አንድ የምሽት ክበብ ሲወጣ በቁጥጥር ስር ቢውልም ከሳምንት በኋላ ማምለጥ ችሎ ነበር።
ግለሰቡ አሜሪካ ተላልፎ እስኪሰጥም ድረስ ለ30 ቀናት በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንዲቆይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ካስተላለፈበትም በኋላ ነው ያመለጠው።
ኬልቪን ተይዞበት ከነበረው የናይሮቢ የፖሊስ ጣቢያ ወጥቶም በህዝብ ማመላለሻ ተሽካርካሪ ተሳፍሮ መሄዱንም ፖሊስ አስታውቆ ነበር።
የናይሮቢ የፖሊስ ኃላፊ አዳምሰን ቡንጂ ተጠርጣሪው ከአምስት ቀናት ከሚቆጠር ፍለጋ በኋላ ማክሰኞ ምሽት ከናይሮቢ ወጣ ብላ በምትገኘው ጎንግ በተሰኘ ስፍራ መያዙን ገልጸዋል።
ኬልቪን ታስሮ ከነበረበት ሙትሃይጋ ፖሊስ ጣቢያ በእግሩ መውጣቱንም ፖሊስ አስታውቆ ነበር። የግለሰቡ የህግ ባለሙያዎች ቡድን በበኩሉ የደንበኛው ህይወት አደጋ ላይ ነው ሲል ተናግሮ ነበር።
“በድጋሜ በቁጥጥር ስር አውለነዋል። በአሁኑ ወቅት በእስር ላይ ነው ያለው። ለዚህም ተግባር የተባበሩንን አካላት ሁሉ እናመሰግናለን” ሲሉም የፖሊስ ኃላፊው ዘስታር ለተሰኘው የዜና ድረገጽ ገልጸዋል።
የወንጀል ምርመራ ዳይሬክቶሬት፣ ዲሲአይ ተጠርጣሪው በቁጥጥር ስር የዋለው “ደህንነቱ የተጠናከረ ዘመቻ መደረጉን ተከትሎም” እንደሆነ ገልጿል።
ግለሰቡ በቁጥጥር ስር ከዋለም በኋላም በከፍተኛ ጥበቃ ታጅቦም ፍርዱን ወደሚጠብቅበት ናይሮቢ ፖሊስ ጣቢያ ተወስዷል።
ኬልቪን በድጋሜ በቁጥጥር የዋለው በዘመዶቹ ቤት ተሸሽጎ በነበረበት ወቅት እንደሆነም ፖሊስ ገልጿል።
ግለሰቡንም አድኖ ለመያዝ በርካታ ፖሊሶች ተሰማርተውም ነበር ተብሏል።
ከፖሊስ ጣቢያ ከማምለጡም ጋር በተያያዘ አንዳንድ ዘመዶቹ እንዲሁም ጠበቃው በቁጥጥር ስር መዋላቸውም ተነግሯል።
ግለሰቡ ጥቅምት ወር ላይ የሴት ጓደኛውን ከገደለ በኋላ በቦስተን ሎጋን አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በሚገኝ ስፍራ በመኪና ውስጥ አስከሬኗን ጥሏት እንደሸሸ ባለስልጣናቱ ተናግረዋል።
ከዚያም ወደ ትውልድ አገሩ ኬንያም ሸሽቷል ተብሏል። ግለሰቡ በቀረበበት ክስ ላይ እስካሁን የሰጠው አስተያየት የለም።
የኬንያ እና የአሜሪካ ፖሊሶችም በጥምረት ለወራትም ሲፈልጉት ከቆየም በኋላ ነው የተያዘው።
የግለሰቡ ፍቅረኛ የነበረችው ማርጋሬት ምቢቱ ቤተሰቦች ለአሜሪካ ሚዲያ እንደተናገሩት ከመገደሏ በፊት ግንኙነታቸውን ለማቋረጥ እቅድ ነበራት ብለዋል።
የ30 ዓመቷ ግለሰብ ኬንያዊት አሜሪካዊት ስትሆን በማሳቹስተስ ግዛትም በነርስነት ታገለግል ነበር።
በህይወት ለመጨረሻ ጊዜ የታየችውም ከስራዋ ቦታ ስትወጣ ጥቅምት ወር ላይ ነበር።
መጥፋቷ ሪፖርት ከተደረገ በኋላ ከሁለት ቀናት በኋላ አስከሬኗ ተገኝቷል።
በህይወት ለመጨረሻ ጊዜ የታየችውም ከስራዋ ቦታ ስትወጣ ጥቅምት ወር ላይ ነበር።
መጥፋቷ ሪፖርት ከተደረገ በኋላ ከሁለት ቀናት በኋላ አስከሬኗ ተገኝቷል።
መጥፋቷ ሪፖርት በተደረገበት እና አስከሬኗ በተገኘበት ባሉት ቀናትም ግለሰቡ ጠፍቷል ብለው እንደሚያምኑም ባለስልጣናቱ ተናግረዋል። አስከሬኗ ከተገኘበት ከአውሮፕላን ማረፊያው ከሚገኘው የመኪና ማቆሚያ ስፍራን ለቆ ሲወጣም የሚያሳይ ቪዲዮ መውጣቱን ተከትሎም በግድያዋ እጁ እንዳለበት ተገልጿል።












