የወንጀል ጥናት የዶክትሬት ተማሪው በአራት ተማሪዎች ግድያ ተጠርጥሮ ተያዘ

የፎቶው ባለመብት, CBS/ MONROE COUNTY CORRECTION FACILITY
በወንጀል ሕግ እና ድርጊቶች ዘርፍ የዶክትሬት ዲግሪ አጥኚ የሆነው ግለሰብ በአሜሪካ አይዳሆ ዩኒቨርስቲ ውስጥ በተፈጸመ አነጋጋሪ እና እንቆቅልሽ ነው በተባለ የአራት ተማሪዎች ግድያ ተጠርጥሮ ተያዘ።
ብሪያን ክሪስቶፈር የተባለው የ28 ዓመት ወጣት የተያዘው ግድያው ከተፈጸመበት ስፍራ ከ4 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ ርቆ ፔንሲልቬኒያ ግዛት ውስጥ ነው።
አራቱ የአይዳሆ ዩንቨርስቲ ተማሪዎች ከትምህርት ቤታቸው አቅራቢያ በተከራዩት ቤት ውስጥ በተኙበት ነበር ከአንድ ወር በፊት ተገድለው የተገኙት።
ፖሊስ እንዳለው ተጠርጣሪው ግድያው ከተፈጸመበት ከተማ አቅራቢያ ይኖር ነበር።
ሁሉም በ20ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ የሚገኙት ዣና ኬርኖድል፣ ኤታን ቻፒን፣ ካይሊ ጎንኬቭ እና ማዲሰን ሞጋን በሰሜናዊ አይዳሆ ውስጥ በምትገኘው ትንሽ ከተማ ሞስኮ ውስጥ በተፈጸመባቸው የስለት ጥቃት ነበር ሞተው የተገኙት።
ሲፈለግ የቆየው የግድያው ተጠርጣሪ ስክራንተን በተባለችው የፔንሲልቬኒያ ግዛት ከተማ አቅራቢያ በወላጆቹ ቤት ውስጥ በቁጥጥር ስር መዋሉን ፖሊስ ገልጾ፣ አራት የመጀመሪያ ደረጃ ነፍስ ማጥፋት እና ቤት ሰብሮ የመግባት ክስ እንደተመሠረተበት ዐቃቤ ሕግ አስታውቋል።
ባለሥልጣናት እንዳረጋገጡት ተጠርጣሪው ብሪያን ክሪስቶፈር በዋሽንግተን ዩኒቨርስቲ በወንጀል ፍትህ እና በወንጀል ጥናት የዶክትሬት ተማሪ መሆኑ ተገልጿል።
ወንጀሉ የተፈጸመበት ከተማ የፖሊስ አዛዥ ጄምስ ፍሬይ ስሜታዊ ሆነው ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት“ግድያው የአካባቢውን ኅብረተሰብ ክፉኛ ያስደነገጠ ነው” በማለት ወንጀሉ ሰፊ እና ውስብስብ መሆኑን አመልክተዋል።
ፖሊስ ከኅብረተሰቡ ከ19 ሺህ በላይ ከወንጀሉ ጋር የተያያዙ ጥቆማዎችን ማግኘቱን ጠቅሶ፣ ተጠርጣሪው ከሟቾቹ ጋር ትውውቅ እንዳለው ለማወቅ ምርመራ እያደረገ መሆኑን በመግለጽ ለግድያው ምክንያቱ ምን እንደሆነ ከመግለጽ ተቆጥቧል።
ስማቸው ያልተገለጸ የሕግ አስፈጻሚ ባለሥልጣናት ለአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን እንዳረጋገጡት የተገኙ የዘረመል ማስረጃዎች ከተጠርጣሪው ጋር የሚገናኙ ሆነዋል።
ተጠርጣሪው የወንጀል ጉዳዮች የዶክትሬት ተማሪ ከመሆኑ በተጨማሪ በዋሽንግተን ስቴት ዩኒቨርስቲ ሦስት የቅድመ ምረቃ ትምህርቶችን በረዳትነት እንዲሰጥ ተመርጦ ነበር።












