ክርስቲያኖ ሮናልዶ ከፍተኛ በተባለ ክፍያ የሳዑዲ አረቢያውን አል ናስር ክለብ ተቀላቀለ

ክርስቲያኖ ሮናልዶ

የፎቶው ባለመብት, Al Nassr

ታትሟል

የፖርቹጋል ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን አምበል ክርስቲያኖ ሮናልዶ ለሦስት ዓመት ቆይታ የሳዑዲውን ክለብ አል ናስርን ተቀላቀለ።

ሮናልዶ በቅርቡ በሰጠው ቃለ ምልልስ ላይ የነበረበትን የእንግሊዙን ክለብ ማንችስተር ዩናይትድን ከተቸ በኋላ ውዝግብ ውስጥ ገብቶ ነው ከቡድኑ ጋር የተለያያው።

ሮናልዶ ለሳዑዲው ክለብ ሲፈርም በዓመት 177 ሚሊዮን ፓወንድ (210 ሚሊዮን ዶላር በላይ) እንደሚከፈለው የተስማማ ሲሆን፣ ይህም በታሪክ ለእግር ኳስ ተጫዋች የሚከፈል ከፍተኛው ደሞዝ ነው ተብሏል።

የ37 ዓመቱ ሮናልዶ ወደ ሳዑዲ የሚያደርገውን ዝውውሩን በተመለከተ “በተለየ አገር ውስጥ ከአዲስ የእግር ኳስ ቡድን ጋር ለመጫወት መጓጓቱን” ገልጿል።

ጨምሮም “በአውሮፓ እግር ኳስ ውስጥ ለማግኘት የምፈልገውን አሸናፊነት ሁሉ አሳክቻለሁ፤ አሁን ደግሞ ያለኝን ልምድ ወደ እስያ አህጉር ለማሻገር ትክክለኛው ጊዜ ነው ብዬ አስባለሁ” ብሏል።

የሳዑዲ አረቢያ እግር ኳስ ሊግ የዘጠኝ ጊዜ አሸናፊ የሆነው አልናስር ከሮናልዶ ጋር ያደረገውን ስምምነት “ታሪካዊ ነው” ሲል ገልጾታል።

ክለቡ እንዳለው ይህ ስምምነት “ሊጋችንን፣ አገራችንን እና ቀጣዩን ትውልድ፣ ወንድ እና ሴት ልጆቻችንን በእራሳቸው የላቁ ሆነው እንዲወጡ ለማድረግ መነቃቃትን ይፈጥራል” ብሏል።

ባለፈው ዓመት ሌላኛው የሳዑዲ ክለብ አል ሂላል ለሮናልዶ የ305 ሚሊዮን ፓወንድ ክፍያ ቢያቀርብለትም፣ ከዩናትድ ጋር ባለው ግንኙነት ደስተኛ መሆኑን በመግለጽ ሳይቀበለው ቀርቶ ነበር።

ክርስቲያኖ ሮናልዶ ባለፈው ኅዳር ከታዋቂው የቴሌቪዥን ትርኢት አቅራቢያ ፒርስ ሞርጋን ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ በማንችስተር ዩናይትድ “መከዳቱን” እና ለአሰልጣኙ ኤሪክ ቴን ሃግ አክብሮት እንደሌለው ከተናገረ በኋላ ከክለቡ ጋር ለመለያየት በቅቷል።

ከዩናይትድ ወደ ሪያል ማድሪድ ከዚያም ወደ ጁቬንቱስ ያቀናው ሮናልዶ ከአንድ ዓመት በፊት ወደ ቀድሞ ክለቡ የተመለሰው ሲሆን፣ ለማንችስተር ዩናይትድ በተሰለፈባቸው 346 ጨዋታዎች 145 ግቦችን አስቆጥሯል።

ሮናልዶ ከዩናይትድ ጋር ውዝግብ ውስጥ ሲገባ በሳምንት 500 ሺህ ፓወንድ ክፍያን ያገኝበት የነበረው ስምምነቱ ሊጠናቀቅ ሰባት ያህል ወራት ቀርተውት የነበረ ቢሆንም፣ በስምምነት ለመለያየት ወስኖ ነው ከቡድኑ የተለየው።

ክርስቲያኖ ሮናልዶ በቅርቡ በተጠናቀቀው የኳታሩ የዓለም ዋንጫ የአገሩን ብሔራዊ ቡድን በአምበልነት የመራ ሲሆን፣ በአምስት የተለያዩ የዓለም ዋንጫ ውድድሮች ላይ ግብ በማስቆጠር ታሪክ አስመዝግቧል።