ትራምፕ አላሳይም ብለው ሲሟገቱላቸው የነበሩት የግብር ሰነዶቻቸው ይፋ ሆኑ

ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ዶናልድ ትራምፕ
ታትሟል

በሥልጣን ላይ ከነበሩበት ጊዜ ጀምሮ ለስድስት ዓመታት ሲያወዛግብ የቆየው የቀድሞው ፕሬዝዳንት የዶናልድ ትራምፕ የግብር ሰነዶች ይፋ ሆኑ።

ለፕሬዝዳንትነት በተወዳደሩበት ጊዜ በንግድ ሥራቸው ያስመዘገቡት ስኬት ተመራጭ እንደሚያደርጋቸው መቀስቀስ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ተቺዎቻቸው የትራምፕን የሀብት ምንጭ እና የገቢያቸውን ዝርዝር ለማወቅ ሲጥሩ ነበር።

ነገር ግን ዶናልድ ትራምፕ የግል መረጃቸውን ለማንም ይፋ ለማድረግ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ለዓመታት ቆይተዋል።

እነዚህ አሁን ይፋ እንዲሆኑ የተደረጉት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የግብር ሰነዶች በንግድ ተቋማቶቻቸው ላይ ያጋጠሙ ኪሳራዎችን፣ ውስብስብ የግብር ሥርዓታቸውን እና በሥልጣን ዘመናቸው የከፈሉትን የግብር መጠን ገሃድ አውጥተውታል።

ይፋ የተደረጉት ሰነዶች ዶናልድ ትራምፕ በአውሮፓውያኑ 2020 ለፌደራል መንግሥቱ ምንም ግብር እንዳልከፈሉ፣ እንዲሁም በ2016 እና በ2017 ዓመታት 750 ዶላር ብቻ መክፈላቸውን አጋልጠዋል።

ነገር ግን ተከትሎ በነበረው 2018 የአውሮፓውያን ዓመት ወደ 1 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ መክፈላቸው ታይቷል።

ነገር ግን ትራምፕ ይህ የግብር ሰነዶች ጉዳይ የተነሳው በቀጣይ በድጋሚ ለፕሬዝዳንትነት ዕጩ ለመሆን የሚያደርጉትን ጥረት ለማደናቀፍ ነው በማለት ሲከራከሩ ቢቆዩም፣ በፖለቲካ ሕይወታቸው ላይ ግን የጎላ ተጽእኖ ይኖረዋል ብለው እንደማያስቡ ባለሙያዎች ተናግረዋል።

በመቶዎች የሚቆጠሩ ገጾች ያሏቸውን የትራምፕ የግል እና የንግድ የታክስ ሰነዶች ይፋ መደረጋቸው በአሜሪካ የፖለቲካ መድረክ ላይ ያለውን ክፍፍል ያባብሰዋል ሲሉ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ደጋፊዎች አስጠንቅቀዋል።

ከሪፐብሊካኖች የወጣው መግለጫ “ዲሞክራቶች ፈጽሞ ማድረግ አልነበረባቸውም፤ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱም ሰነዶቹ ይፋ እንዲሆኑ መፍቀድ አልነበረበትም። ይህ በብዙ ሰዎች ላይ አስቀያሚ መዘዝን ይዞ ይመጣል” ብሏል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የአሜሪካንን የተወካዮች ምክር ቤት የሚቆጣጠሩት እና የሰነዶቹን ይፋ መሆን ሲከታተሉ የቆዩት ዲሞክራቶች ውሳኔው ፖለቲከኞችን የመቆጣጠር አስፈላጊ እርምጃ ነው ብለዋል።

ይፋ የተደረጉት የታክስ ሰነዶች ትራምፕ ለፕሬዝዳንትነት ከቀረቡበት ከፈረንጆቹ 2015 በዋይት ሐውስ አስከ ቆዩበት 2020 ድረስ የሚዘልቁ ናቸው። በዚህም ትራምፕ ታክስ ሊከፍሉባቸው የሚገቡ የተለያዩ ድርጅቶች የሥራ እንቅስቃሴን እና የግል ገቢያቸውን ይፋ ያደርጋል።

ጉዳዩን ሲከታተል የነበረው ኮሚቴ እንዳለው የአሜሪካ የግብር መሥሪያ ቤት፣ ትራምፕ በፕሬዝዳንትነት በቆዩባቸው የመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመታት ገቢያቸውን ኦዲት አለማድረጉን ደርሶበታል።

ለበርካታ ዘመናት ለግልጽነት እና ለተጠያቂነት ሲባል የአሜሪካ ዕጩ ፕሬዝዳንቶች እና ባለሥልጣናት ግብር የሚያስከፍሉ ገቢዎቻቸውን ለሕዝብ ይፋ ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ይህም የአገሪቱ ፕሬዝዳንት የጥቅም ግጭቶች እንዳይኖሩበት ለማድረግ እና ግብር ደግሞ የእያንዳንዱን ግለሰብ የገቢ ሁኔታ እንዲሁም ምንጭን ስለሚያሳይ ትኩረት ይሰጠዋል።

ነገር ግን ዶናልድ ትራምፕ ለፕሬዝዳንትነት በዕጩነት ከቀረቡበት ጊዜ አንስቶ የተለመደውን አሰራር በመቃወም የታክስ ሰነዶቻቸውን ይፋ ለማድረግ አሻፈረኝ ሲሉ ቆይተዋል።

ይህ እምቢተኝነታቸው ደግሞ በተችዎቻቸው ዘንድ የሚደብቁት ነገር ይኖራል የሚል ጥርጣሬን በመፍጠር ጥያቄ አስከትሏል። በተለይም ትራምፕ ከሚጠበቅባቸው በታች ግብር ሲከፍሉ ቆይተዋል የሚል ጥርጣሬ እና በሀብታቸው መጠንም የሚወራለትን ያህል እንዳልሆነ የሚያመለክቱ ጥያቄዎች ተነስተዋል።

ደጋፊዎቻቸው ግን ጥያቄ የቀረበበት ጉዳይ የግል ምስጢራቸው ከመሆኑም በላይ፣ የታክስ ወጪያቸውን ይፋ እንዲያደርጉ የሚያስገድድ የሕግ መሠረት የለም በሚል ተከራክረውላቸው ነበር።

ይህንንም ተከትሎ ኒው ዮርክ ታይምስ የሁለት አስርት ዓመታት መረጃዎችን መሠረት አድርጎ ከሁለት ዓመት በፊት በትራምፕ የታክስ ሰነዶች ላይ የምርመራ ዘገባ ካቀረበ በኋላ ጉዳዩ የበለጠ መነጋገሪያ ሆኗል።

በዚህም ዘገባው ትራምፕ በጣም ትንሽ ወይም ምንም ግብር ለመንግሥት እንዳልከፈሉ በመግለጽ፣ ሲሉ እንደነበረው ተቋሞቻቸው ትርፋማ ሳይሆኑ ከፍተኛ ኪሳራ እንደገጠማቸው አመልክቷል።

በተጨማሪም ትራምፕ ቢሊየነር ቢሆኑም በ2017 (እአአ) የከፈሉት ታክስ 750 ዶላር ብቻ ነው ብሏል።

ከዚህም በኋላ ዲሞክራቶች በ2019 (እአአ) የአገሪቱን የተወካዮች ምክር ቤት በበላይነት ሲቆጣጠሩ በፕሬዝዳንቱ የግብር ጉዳይ ላይ ክትትል ማድረግ ጀምረዋል። ጉዳዩም ጠቅላይ ፍርድ ቤት ድረስ ሄዶ ሰነዶቹ ይፋ እንዲሆኑ ከተፈቀደ በኋላ መርማሪ ኮሚቴው የመጨረሻውን ውሳኔ ሰጥቷል።

ሪፐብሊካኖች የሰነዶቹን ይፋ መሆን አጥብቀው የተቃወሙ ሲሆን፣ አርብ የትራምፕ የግብር ሰነዶች ይፋ እንዲሆኑ የተደረገው ሪፐብሊካኖች የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ተቆጣጥረው ሥራ ከመጀመራቸው በፊት ነው። ይህም ፓርቲው ጉዳዩን ለማዳፈን የነበረውን ዕድል አደናቅፎበታል።