ሰሜን ኮሪያ ለዓመቱ የመጨረሻ የተባሉ ተወንጫፊ ሚሳኤሎችን ተኮሰች  

ኪም ጆንግ ኡን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ኪም ጆንግ ኡን
ታትሟል

ሰሜን ኮሪያ እየተጠናቀቀ ላለው የፈረንጆች ዓመት የመጨረሻ ሊሆኑ ይችላሉ የተባሉ ሦስት የአጭር ርቀት ተወንጫፊ ሚሳኤሎችን ወደ ኮሪያ ባሕር መተኮሷን የደቡብ ኮሪያ ጦር ሠራዊት አስታወቀ።

እነዚህ ሚሳኤሎች የተወንጨፉት ሰሜን ኮሪያ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን (ድሮን) በደቡብ ኮሪያ የአየር ክልል ውስጥ ከአምስት ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ካሰማራች ከአምስት ቀናት በኋላ ነው።

ዛሬ በሚጠናቀቀው 2022 ዓመት ከሌሎች ዓመታት በበለጠ ሰሜን ኮሪያ በርካታ ሚሳኤሎችን አስወንጭፋለች።

በቅርቡ የተደረጉት የሰሜን ኮሪያ የሚሳኤል ሙከራዎች በአሜሪካ እና በአጋሮቿ ላይ አስቸኳይ የሆነ ስጋትን የሚደቅኑ አይደሉም ስትል አሜሪካ አጣጥላቸዋለች።

ዛሬ ተተኮሱ የተባሉት የአጭር ርቀት ተወንጫፊ ሚሳኤሎች፣ ከሰሜን ኮሪያዋ ዋና ከተማ ፒዮንግያንግ በስተደቡብ ከምትገኘው ህዋንግሂ ከተባለችው ግዛት መወንጨፋቸውን የደቡብ ኮሪያ ጦር ሠራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ተናግረዋል።

ባለሥልጣኑ አክለውም “የሰሜን ኮሪያ ተወንጫፊ ሚሳኤሎችን መተኮስ ከባድ ጠብ አጫሪነት ሲሆን፣ ይህም የኮሪያን ልሳነ ምድር እንዲሁም የዓለም አቀፉን ሕብረተሰብ ሰላምና መረጋጋት የሚያናጋ ነው” ብለዋል።

የተተኮሱት ሚሳኤሎች 350 ኪሎ ሜትር ያህል መጓዛቸውን የደቡብ ኮሪያ ጦር ሠራዊት ገልጿል።

ቀደም ሲልም አንድ ሚሳኤል ባሕር ላይ መውደቁን የጃፓን የባሕር ጠረፍ ጠባቂዎች አሳውቀዋል።

በዚህ ሳምንት በሁለቱ አገራት የጋራ ድንበር አካባቢ ሲበሩ የነበሩትን አምስት ድሮኖች መትቶ ባለመጣሉ የደቡብ ኮሪያ ጦር ሠራዊት ይቅርታ ጠይቋል።

ከድሮኖቹ መካከል አንዱ ወደ ዋና ከተማዋ ሴዑል አቅራቢያ የተጠጋ ሲሆን፣ ደቡብ ኮሪያ በድሮኖቹ ላይ ጀቶች እና ሄሊኮፕተሮችን አሰማርታ የማስጠንቀቂያ ተኩስ ከፍታ ነበር።

ሰሜን ኮሪያ እያደረገቻቸው ካሉ ከእነዚህ የሚሳኤል ሙከራዎች ጋር ግንኙነት አላቸው በተባሉ የአገሪቱ ባለሥልጣናት ላይ በታኅሣሥ ወር መጀመሪያ አሜሪካ እና የእስያ አጋሮቿ ማዕቀብ ጥለዋል።

በሰሜን እና ደቡብ ኮሪያ መካከል ያለው ግንኙነት የበለጠ እየተበላሸ የሄደው የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ዩን ሱክ-ዬኦል ወግ አጥባቂ መንግሥት ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ ሥልጣን ተረክቦ በሰሜን ኮሪያ ላይ ጠንካራ አቋም እንደሚይዝ ካሳወቀ በኋላ ነው።

በቅርብ የተካሄዱትን የጦር መሳሪያ ግንባታዎችን በበላይነት የሚመሩት ኪም ጆንግ ኡን ከቀደሙት የአገሪቱ መሪዎች በበለጠ ጠንካራ አቋም እያራመዱ መሆናቸው ይነገራል።

በቅርቡም ኪም አገራቸው ሰሜን ኮሪያ በዓለም ላይ ዋነኛዋ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ኃያል አገር እንድትሆን እንደሚፈልጉ እና ይህም “ከማይቀለበስበት” ደረጃ ላይ መድረሱን ተናግረው ነበር።