ከሁለት ዓመታት መቋረጥ በኋላ የሚካሄደው ጣና ፎረም ምንድን ነው?

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ጣና ፎረም ለሰላም እና የደኅንነት ችግሮች አፍሪካ መር መፍትሔ ለመስጠት ጥሪ ያቀረበውን የትሪፖሊ ቃል ኪዳንን ተከትሎ የተጀመረ ጉባኤ ነው።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ስር በሚገኘው የሰላም እና ደኅንነት ጥናት ተቋም እንዲሁም በፍሪካ ታዋቂ መሪዎች አነሳሽነት የተመሠረተው ፎረሙ፤ ዓላማው በአህጉሪቱ የፀጥታ ጉዳዮች ላይ መሪዎች፣ ውሳኔ ሰጪዎች እና ባለሙያዎች እንዲመካከሩ፣ ሀሳብ እንዲለዋወጡ ልዩ መድረክ መፍጠር ነው።

በ2004 ዓ.ም. (እአአ በ2012) በባሕር ዳር ከተማ የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንትኦሊሴጉን ኦባሳንጆ የጣና ፎረም ጉባኤ የመጀመሪያ ሊቀ መንበርነት ሆነው ነበር ጉባኤው የተጀመረው።

ከሁለት ዓመት መቋረጥ በኋላ 11ኛው የፎረሙ ጉባኤ አርብ ጥቅምት 14/2018 ዓ.ም. ከዓመታት በኋላ በባሕር ዳር ከተማ ተጀምሯል።

ከፍተኛ የደኅንነት ጉባኤ የሆነው ጣና ፎረም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሰላም እና ደኅንነት ጥናት ተቋም የሚዘጋጅ ነው።

ጉባኤው ዓመታዊ ሲሆን ገለልተኛ በሆነ መድረክ የአፍሪካ መሪዎችን ከተለያዩ ባለድርሻዎች ጋር የአህጉሪቱን የሰላም እና የደኅንነት ችግሮች በተመለከተ እንዲወያዩ እና ሃሳብ እንዲለዋወጡ መድረክ ይሆናል።

መደበኛ ያልሆነ የንግግር መድረክ ለመሆን የሚያልመው ይህ ፎረም የፖለቲካ መሪዎች፣ የሲቪል ማኅበረሰብ አባላት፣ ምሁራንን እና ሌሎችንም በማካተት በቁልፍ ጉዳዮች ላይ ንግግርን የሚያበረታታ ነው።

የፎረሙ ጽህፈት ቤት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሰላም እና ደኅንነት ጥናት ተቋም ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፤ እንቅስቃሴው እና አጀንዳው የሚወሰነው ደግሞ የአፍሪካ መሪዎችን በያዘው ቦርድ ነው።

በአሁኑ ወቅት የቦርዱ ሊቀ መንበር የቀድሞው የጋና ፕሬዝዳንት ጆን ድራማኒ ማሃማ ናቸው።

በቅርቡ ሕይወታቸው ያለፈው ፕሮፌሰር አንድሪያስ እሸቴ ምክትል ሊቀ መንበር የነበሩ ሲሆን፤ ከቀድሞ የቦርድ መሪዎቹ መካከል ኃይለ ማሪያም ደሳለኝ፣ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም፣ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ፣ ታቦ ምቤኪ፣ ፒየር ቦዮያ እና ሌሎችም ስመ ጥር የሆኑ የአፍሪካ ቀደምት መሪዎች ይገኙበታል።

ለፎረሙ ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ የግል ዘርፎች 70 በመቶ ፋይናንስ የሚያቀርቡ ሲሆን፤ ቀሪውን 30 በመቶ ገንዘብ የተለያዩ የልማት አጋሮች ያቀርባሉ።

ጣና ፎረም ስሙን ጉባኤውን በምታስተናግደው ባሕር ዳር ከተማ ውስጥ ከሚገኙው በኢትዮጵያ ትልቁ ከሆነው ሐይቅ የወሰደ ሲሆን፣ የመጀመሪያው ጉባኤ በወርሃ ሚያዝያ 2004 ዓ.ም. ነበር የተስተናገደው።

በዚህ ጉባኤ አራት የአገራት መሪዎች እና ርዕሰ ብሔሮች፣ ሰባት ሚኒስትሮች፣ ስድስት የአገራት ወኪሎች፣ 10 የዓለም አቀፍ ደኅንነት ባለድርሻዎች፣ 30 ባለሙያዎች፣ ስድስት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች እና 13 አጋራት የተሳተፉበት እንደነበር የፎረሙ ድረ ገፅ ያመለክታል።

በዚህ የመጀመሪያው ጉባኤ የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፤ በንግግራቸው የጣና ፎረም ዓላማ ነባር ተቋማትን ለመተካት አሊያም ሥራ ለማብዛት ሳይሆን አጋዥ ለመሆን እንደሆነ ገልፀዋል።

ፎረሙ ባለፉት ዓመታት ከብዝኃነት አስተዳደር ጀምሮ የተደራጁ ወንጀሎች በአፍሪካ፣ ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ አክራሪነት እና ፖለቲካዊ እምነት እንዲሁም የተፈጥሮ ኃብት ጉዳዮችን አጀንዳ አድርጎ መክሯል።

ጉባኤው ለስምንት ዓመታት በተከታታይ በባሕር ዳር ሲካሄድ ከቆየ በኋላ ዘጠነኛው ጉባኤው በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት ከጣና ርቆ በአዲስ አበባ ከጥቅምት 9 እስከ 14/2013 ዓ.ም. ተካሂዷል።

ባለፉት አስር ዓመታት ፎረሙ በርካታ ምክረ ሃሳቦችን ያቀረበ ሲሆን፤ ምክረ ሃሳቦቹ አስገዳጅ አለመሆናቸው፣ በአፍሪካ እየጨመረ ያለው የውጭ ተፅዕኖ እና የአገራት ሰላም እና ፀጥታ መሰናክል እንደሆኑበት ይታመናል።

ስለ ሰላም እና ደኅንነት የሚመክረው ጉባኤው በአስተናጋጇ አገር ኢትዮጵያ የፀጥታ ችግር ምክንያት ላለፉት ሁለት ዓመታት አልተካሄደም።

ጉባኤው ከዚህ ቀደም 2014 ዓ.ም. በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ምክንያት ቀን ከተቆረጠለት በኋላ ተራዝሞ ነበር።

ፎረሙ ከሦስት ዓመታት በፊት በ2015 ዓ.ም. በባሕር ዳር ሲካሄድ አሁን ከተቃናቃኛቸው ጋር ጦርነት ውስጥ የገቡት የሱዳን መሪ አብዱልፈታህ አልቡርሃንን ጨምሮ በርካታ መሪዎች ተገኝተውበታል።

በ2016 ዓ.ም. 11ኛውን ጉባኤ ለማካሄድን ቀን ከተቆረጠ በኋላ በዋናነት በአማራ ክልል እየተካሄደ ባለው ግጭት ምክንያት በተደጋጋሚ ተራዝሟል።

በ2016 ዓ.ም. ፎረሙ "ባልተጠበቁ ሁኔታዎች ምክንያት" መራዘሙን አዘጋጆቹ አስታውቀው የነበረ ሲሆን፤ ዘንድሮ የተራዘመው ጉባኤ ግጭቱ ሳይረግብ እየተካሄደ።

የዘንድሮው 11ኛው የጣና ፎረም "አፍሪካ በተለዋዋጭው የዓለም ሥርዓት ውስጥ" በሚል መሪ መልዕክት ለሦስት ቀናት እንደሚቆይ አዘጋጆቹ አስታውቀዋል።