ደቡብ ኮሪያ ከሰሜን ኮሪያ ጋር በይፋ ጦርነትን የሚቋጭ ንግግር እንዲደረግ ጠየቀች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንት ሊ ጄ ሚዩንግ ከጎረቤታቸው ሰሜን ኮሪያ ጋር ለመወያየት ጥያቄ አቀረቡ።
ውይይቱ በሁለቱ አገራት መካከል በተወሰነ ደረጃ ያለውን ጦርነት በይፋ ለማቆም ያለመ መሆኑንም አስታውቀዋል።
በሁለቱ አገራት መካከል ባለው ከወታደራዊ ቀጣና ውጪ የሆነ ድንበር ላይ ግጭት እንዳይነሳ "ዘርፈ ብዙ የደኅንነት ሥርዓት" ለመዘርጋትም ሐሳብ አቅርበዋል።
በተጨማሪም የሰሜን ኮሪያን የኒውክሌር ፍላጎት ለመግታት ተግባራዊ መደረግ የሚችሉ መንገዶች ላይ መመካከር እንደሚያስፈልግም ጠቅሰዋል።
ሰሜን ኮሪያ ኒውክሌር መሸከም የሚችሉ ባለስቲክ ሚሳዔሎችን በመተኮስ በተደጋጋሚ ሙከራ አድርጋለች። ይህ እርምጃ ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን ላይ የኃይል የበላይነት ለማሳየት የተደረገ ነው።
የኮሪያ ባሕረ ገብ መሬትን በቁጥጥር ሥር ያዋሉት ሁለቱ አገራት፣ በአውሮፓውያኑ 1953 የተኩስ አቁም ስምምነት ተፈራርመዋል።
የሰላም ስምምነት ስላልተፈራረሙ ግን ጦርነቱ አሁንም ድረስ ቀጥሏል።
በሁለቱ አገራት መካከል ባለው ከወታደራዊ ቀጣና ውጪ የሆነ ድንበር ላይ ግጭቶች ተነስተዋል፤ አካባቢውም በውጥረት የተሞላ ነው።
ሁለቱ ወገኖች ግጭትን በማስነሳት አንዳቸው ሌላኛቸውን ይወቅሳሉ።
ከዚህ ቀደም የፕሮፓጋንዳ ጽሑፍ እና ቆሻሻ የያዙ ፊኛዎች ከአንደኛው ግዛት ወደ ሌላኛው በመላክ ሲካሰሱ ነበር።
የቀድሞው የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንት ዩን ሱክ ዩል ወታደራዊ ሕግ ለመደንገግ በመሞከራቸው መከሰሳቸው ይታወሳል።
አገራቸው ከሰሜን ኮሪያ እና ከቻይና ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሻከር ሞክረዋል የተባሉት የቀድሞው ፕሬዝዳንት በቁጥጥር ሥር ውለውም ነበር።
ባለፈው ዓመት የተሾሙት አዲሱ ፕሬዝዳንት የኮሪያ ባሕረ ገብ መሬት ከጃፓን ነጻ የወጣበትን ቀን አስመልክተው ባደረጉት ንግግር፣ "አንዳችን ሌላችንን ማስፈራራት እናቁም እና ረዥሙ ጦርነት ያክትም" ብለዋል።
ሁለቱ አገራት "በሰላም አብሮ ለመኖር እና በጋራ ለማደግ እንዲችሉ" ፊት ለፊት ተገናኝተው ይወያያሉ ብለው እንደሚያምኑም ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ የሰሜን ኮሪያን የኒውክሌር አቅም "በተሳካ ሁኔታ ለመግታት" ንግግሮች መደረግ አላባቸው ብለዋል።
ሰሜን ኮሪያ እስካሁን ለቀረበላት የውይይት ጥሪ ምላሽ አልሰጠችም።
በአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቭዥን ጣቢያ ኪም ጆንግ ኡን የኮሪያ ባሕረ ገብ መሬት ከጃፓን ነጻ የወጣበት ቀን ሲከበር ታይቷል።
ከዚህ ቀደም ፒዮንግያንግ የቀረበላትን የውይይት ጥያቄ ውድቅ አድርጋለች።
የውይይት ጥያቄው የአሜሪካ በደቡብ ኮሪያ የኒውክሌር ኃይል ያለው ሰርጓጅ መርከብ የማሰማራት ስምምነት አካል ነው ስትልም አጣጥላለች።
በ2024 የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ሁለቱ አገራት አንድ የሚሆኑበት ዕድል የለም ብለዋል።
ሕገ መንግሥቱ ተሻሽሎ ደቡብ ኮሪያ "ዋነኛ እና ቀንደኛ ጠላት አገር" ተብላ እንድትፈረጅም ይፈልጋሉ።
በኮሪያ ባሕረ ገብ ጦርነት ቢነሳ የሰሜን ኮሪያ ግብ ደቡብ ኮሪያን "መልሶ ጠቅልሎ መግዛት" እንደሆነም ተናግረዋል።
ሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር መሣሪያ እንዳላት በይፋ ያስታወቀችው በ2022 ነበር።
የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳነት ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ ሰሜን ኮሪያ በዓመት ከ15 እስከ 20 የሚሳዔል ተተኳሽ እያመረተች እንደሆነ ገልጸዋል።















