ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከጥቁሮች ተወርሶ የነበረ የመዝናኛ ስፍራ ከ100 ዓመታት በኋላ ለቤተሰቦቻቸው ተመለሰ
የሎስ አንጀለስ ባለስልጣናት ከ100 አመት በፊት ከጥቁር ባለቤቶቹ የተነጠቀ የባህርዳርቻ የመናፈሻ ቦታ ለወራሾቻቸው መልሰዋል።
የዘር መድልዎ በደቡብ ካሊፎርኒያ በተንሰራፋበት ወቅት ለጥቁሮች የባህርዳርቻ የመዝናኛ ስፍራ እንዲሆን ለመፍጠር የብሩስ ባህር ዳርቻ እአአ በ1912 ተገዛ።
የዓይን ማረፊያ በሆነው የማንሃተን ቢች ከተማ የሚገኝ ሲሆን በ1924 በአከባቢው ምክር ቤት ተወርሷል።
ማክሰኞ ዕለት የሎስ አንጀለስ ባለስልጣናት መሬቱን ለቤተሰቡ ለመመለስ ድምጻቸውን ሰጥተዋል።
ዊላ እና ቻርለስ ብሩስ ሁለቱን መሬት በ1ሺህ 225 ዶላር ነበር እአአ በ1912 የገዙት። የባህርዳርቻው አሁን 20 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ዋጋ አለው።
ዊላ በወቅቱ ለአንድ ጋዜጠኛ "ለባህር ዳርቻ ሪዞርት የሚሆን ቦታ ለመግዛት ስንሞክር ሁሌም ውድቅ ይደረግብናል። ይህ መሬት የእኔ ነውና ይዤው እቆያለሁ" ብሎ ነበር።
በሚቀጥሉት አስርት ዓመታት የብሩስ የባህር ዳርቻ "ከመላው ደቡብ ካሊፎርኒያ ለመዝናናት ወደዚያ ለሚያቀኑ አፍሪካውያን አሜሪካውያን መዳረሻ ሆኗል" ሲሉ የቤተሰብ ቃል አቀባይ ቺፍ ዱአን “የሎው ፊዘር" ሺፓርድ ባለፈውዓመት ለቢቢሲተናግረዋል።
የአከባቢው ፖሊስ ግን መኪና ከ10 ደቂቃ በላይ ማቆም የሚገድቡ ምልክቶችንአስቀምጧል። ሌላ የቦታው ባለርስትም መተላለፍ እንደማይቻል ምልክቶችን በማስቀመጣቸው ሰዎች ውሃው ጋር ለመድረስ አንድ ኪሎ ሜትር ገደማ እንዲራመዱ አስገድዷቸዋል ብለዋል ።
እርምጃዎቹ ጎብኝዎችን ማስቆም ባለመቻላቸው የአካባቢው ባለስልጣናት መሬቱ የነበረውን ህግ ተጠቅመው ወርሰውታል። ህጉ መንግሥት ለመንገድ እና ለሌሎች ለህዝብ መገልገያዎች ያሰበውን መሬት በግዳጅ እንዲገዛ ለማድረግ ታስቦ የወጣ ነበር።
ባለሥልጣናቱ ፓርክ ለመገንባት ማቀዳቸውን ተናግረዋል። አካባቢው ምንም ሳይሠራበት ለዐመታት ቆይቶ ነው ግንባታው የተከናወነው።
“ይህ እርምጃ ስኬታማ የጥቁር ቢዝነስን እና ሸሪኮቹን ለማባረር በዘር ላይ ያነጣጠረ ሙከራ እንደነበር በሚገባ ተረጋግጧል” ሲል ማክሰኞ መሬቱ በተመለሰበት ወቅት ተገልጿል።
መሬቱን ለመመለስ የረዥም ጊዜ ዘመቻ እና አስቸጋሪ ሂደት ውስጥ ታልፏል። የባህር ዳርቻው ለዊላ እና ቻርልስ የመታሰቢያ ሐውልት ለዓመታት ቆሞበት ቆይቷል። የግዛቱ ህግ አውጪ ለዚህ ሲባል ንብረቱ እንዲመለስ የሚያስችል ህግ ማውጣት ነበረበት።
አሁን የከተማዋ አስተዳደር መሬቱን ከቤተሰቡ በዓመታ 413,000 ዶላር በሊዝ ተከራይቶ ይጠቀምበታል። በሊዝ ውሉ መሰረት ለወደፊት መሬቱን 20 ሚሊዮን ዶላር እና ተጨማሪ ወጪዎችን ጨምሮ መግዛት የሚያስችለው አንቀጽም ተካቶበታል።
የዊላ እና የቻርልስ የልጅ ልጅ ልጅ የሆነው አንቶኒ ብሩስ "ይህ ቀን እንደሚመጣ እርግጠኛ አልነበርንም" ብሏል።
"በፋይናንስ ረገድ አዳክሟቸዋል። የስኬት ህልማቸው ላይ ውሃ የቸለሰበት ነው። ዛሬ የሆነውን ነገር ቢያዩ ብዬ እመኛለሁ" ብሏል።
"ይህ ባልተነገረለት የአሜሪካ ታሪክ ዙሪያ የሰዎችን ዓይን እንደሚከፍት ተስፋ እናደርጋለን። ያለፈውን ስህተት ለማስተካከል የሚሞክር እርምጃ ነው ብለን እናስባለን።"
የመሬቱ መወረስ ተፅዕኖ ዛሬም ድረስ ስሜቱ አለ ማለት ይቻላል ሲል ሺፓርድ ቀደም ሲል ተናግሮ ነበር።
"ከዚያ ማህበረሰብ ተባረርን…በአሁኑ ወቅት በማንሃታን የባህር ዳርቻ የአፍሪካ አሜሪካውያን ውክልና አንድ በመቶ ብቻነው" ሲል በከተማው የተረጋገጠውን መረጃ ዋቢ አድርጎ አቅርቧል።