አሜሪካ በሶማሊያ ለተሰማራው የአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ የምትሰጠውን ድጋፍ ልታቋርጥ ነው

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

አሜሪካ ከቀጣዩ የአውሮፓውያን ዓመት ጀምሮ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሶማሊያ ለሚያሰማራው የአፍሪካ ኅብረት የሰላም አስከባሪ ተልዕኮ የምትሰጠውን ድጋፍ እንደምታቆም ሁለት ሰነዶች ማመልከታቸውን ሮይተርስ ዘገበ።

በአገሪቱ የተሰማሩት 12 ሺህ የሚጠጉት የአፍሪካ ኅብረት ኃይሎች ደካማውን የሶማሊያ መንግሥት ማጠናከር እንዲሁም ከአል ቃኢዳ ጋር ግንኙነት ያለውን አልሻባብ ታጣቂ ቡድንን ከዋና ከተማዋ ሞቃዲሾ እንዲርቅ ማድረግ ችለዋል።

ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት የተወጣጡ አባላትን ያሉት 'የአፍሪካ ኅብረት የሶማሊያ የድጋፍ እና የማረጋጋት ተልዕኮ'፤ አስፈላጊ የሆኑት የምግብ፣ የውሃ፣ የነዳጅ፣ የህክምና እና የትራንስፖርት አቅርቦትን በአብዛኛው የሚያገኘው በተባበሩት መንግሥታት በኩል ነው።

በፕሬዝዳንት ትራምፕ የሚመራው የአሜሪካ አስተዳደር በሞቃዲሾ በሚገኘው የሶማሊያ መንግሥት ደስተኛ አለመሆኑን ሲገልጽ ቆይቷል። ለዚህም በምክንያትነት የሚጠቅሰው የሶማሊያ መንግሥት ለዓመታት ዓለም አቀፋዊ ድጋፍ ቢሰጠውም ታጣቂዎችን ከማሸነፍ ይቅል በውስጣዊ ፖለቲካዊ ውዝግብ ተጠምዷል የሚል ግምገማን ነው።

ሮይተርስ ተመለከትኩት ያለው ዲፕሎማሲያዊ ሰነድ እንደሚለው አሜሪካ አጠቃላይ በጀቱ 500 ሚሊዮን ዶላር የሆነው ተልዕኮን ለሚደግፈው የመንግሥታቱ ድርጅት የሞቃዲሾ ጽህፈት ቤት ከዚህ ዓመት በኋላ ድጋፍ እንደማትሰጥ ለአፍሪካ ኅብረት አሳውቃለች።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ አገራቸው ከዚህ በኋላ የአፍሪካ ኅብረት ተልዕኮን የሚያግዘውን የተባበሩት መንግሥታት አካል እንደማትረዳ ለሮይተርስ አረጋግጠዋል።

"አሜሪካ ወደ 2 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ስትሰጥ ብትቆይም፤ ሶማሊያ አልሻባብን ማዳከም እና መቆጣጠር ወይም ደኅንንቷን በራሷ መቆጣጠር አልቻለችም..." በማለት ድጋፉን ለአሜሪካ ጥቅም ተጨባጭ እና ቀጥተኛ አንድምታ ወዳላቸው ጉዳዮች እንደምታዞር ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

አሜሪካ የአፍሪካ ኅብረት በሶማሊያ ውስጥ ያለውን የተልዕኮ ጊዜን ለማራዘም በመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታ ምክር ቤት የሚቀርበውን ሃሳብ እንደማትቃወም፤ የአቅርቦት እና ሌሎች ድጋፎችን ግን እንደማትደግፍ ገልጻለች።

ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት የተልዕኮው በጀት 190 ሚሊዮን ዶላር የነበረ ሲሆን፣ ከፍተኛ ዕጥረት አጋጥሞት ገንዘቡን ለማሟላት ከባድ ፈተና ውስጥ ነበረ። ይህንን ለመቋቋምም ከተልዕኮው በጀት ሦስት አራተኛው በተባበሩት መንግሥታት እንዲሸፈን የቀረበውን ሃሳብ አሜሪካ ውድቅ ማድረጓ አይዘነጋም።

ሐሙስ ዕለት የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን የአሜሪካንን ውሳኔን በተመለከተ ለሰላም እና ደኅንነት ምክር ቤት አባላቱ የሚገልጽ ደብዳቤ ለአባል አገራቱ ጽፏል። ውሳኔው የሶማሊያ ተልዕኮው አጠቃላይ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ እንደሚኖረውም አስታውቋል።

የሶማሊያ መከላከያ ሚኒስቴር፣ የአሜሪካ መከላከያ መሥሪያ ቤት፣ የመንግሥታቱ ድርጅት የሶማሊያ እና የአፍሪካ ኅብረት ስለ ውሳኔው ከሮይተርስ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ አልሰጡም።

በሶማሊያ የመከላከያ ሚኒስቴር የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር እና አሁን የሶማሊያ ፓርላማ አባል የሆኑት አህመድ ኮሺን "ውሳኔው በሶማሊያ ላይ ከባድ ተጽእኖ ይኖረዋል" ብለዋል።

በተባበሩት መንግሥታት በኩል የሚቀርበውን ድጋፍ የሚሸፍን ሌላ አካል የማይገኝ ከሆነ በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት ተልዕኮ ሥራውን ሊቀጥል እንደማይችል ጉዳዩን በቀጥታ የሚያውቁ ሁለት ዲፕሎማቶች ተናግረዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪክ ድርጅታቸው የአሜሪካን ውሳኔ እንደሚያውቅ እና በጉዳዩ ላይ "ከአፍሪካ ኅብረት፣ ከሶማሊያ ፌደራል መንግሥት እና ከሌሎች አጋሮች ጋር ውስጣዊ ውይይት" እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።