ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሚሊዮኖች የሚታደሙበት እና ለስድስት ቀናት የሚቆየው የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ የቀብር ሥነ ሥርዓት
የቀድሞው የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ ከተገደሉ ከአራት ወራት በኋላ ከቅዳሜ ጀምሮ ለቀናት የሚቆይ የቀብር እና የመታሰቢያ ሥነ ሥርዓት ይካሄዳል። የአገሪቱ ባለሥልጣናት ዝግጅቱን "የክፍለ ዘመኑ የቀብር ሥነ ሥርዓት" ሲሉ ገልጸውታል።
የኢራን ባለሥልጣናት እንዳሉት በስንብት ሥነ ሥርዓቱ ላይ ከ12 አስከ 20 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች እንደሚገኙ ይጠበቃል። በዚህም የተነሳ ለመንግሥታዊ ሥነ ሥርዓት የሚደረገው ዝግጅት ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ይሆናል ተብሏል።
በሺህዎች ለሚቆጠሩ ሃይማኖታዊ ተጓዦች ማረፊያ የሚሆኑ ካምፖች፣ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ጎብኙዎች ማረፊያ እንዲሁም በማዕከላዊ ቴህራን የሚታደመውን ሕዝብ ማስተናገድ እና ሌሎችም ውስብስብ የመስተንግዶ ኃላፊነቶች በአዘጋጆቹ ላይ ወድቀዋል።
ይህንንም ሂደት የሚመራው በዋና ከተማዋ ቴህራን የሚገኘው የኢራን አብዮታዊ ዘብ አካል የሆነው 'ሞሐመድ ራሱላህ' በተባለው ጓድ ነው ተብሏል።
በሥነ ሥርዓቱ ላይ ለመታደም ወደ ቴህራን የሚያቀኑ የፖለቲካ፣ የሃይማኖት እና የደኅንነት ባለሥልጣናት ዝርዝር በብዙዎች ከሚጠበቅ ጉዳዮች መካከል ዋነኛው ይሆናል። በሥነ ሥርዓቱ ላይ ከሚገኙት ባልተናነሰ ሁኔታ ቀብሩን የማይታደሙ አካላት ማንነት ትኩረት የሚስብ ጉዳይ መሆኑን ታዛቢዎች ይናገራሉ።
ፕሬዝዳንቶች፣ ጠቅላይ ሚኒስትሮች፣ የፓርላማ አፈ ጉባዔዎች እና ሚኒስትሮችን ጨምሮ የበርካታ አገራት ባለሥልጣናት በሥነ ሥርዓቱ ላይ ለመታደም እንደሚመጡ ተገልጿል። በተጨማሪም 800 የሚሆኑ የውጭ አገር ጋዜጠኞች ለዘገባ ወደ ኢራን እንደሚመጡ ይጠበቃል።
የኢራን ባለሥልጣናት የተጨበጠ መዳፍ ያለበት ምሥል እና "ከፍ እንላለን" የሚል መፈክር የአያቶላህ ኻሜኒ የቀብር ሥነ ሥርዓት መሪ ቃል እንዲሆን ወስነዋል።
ለስድስት ቀናት የሚቆየው የመታሰቢያ እና የቀብር ሥነ ሥርዓት ቅዳሜ ጠዋት 12 ሰዓት ላይ የሚጀመር ሲሆን፣ ጎብኚዎች አስከ እሁድ ከሰዓት በኋላ ድረስ ለአሊ ኻሜኒ ያላቸውን አክብሮት እንዲገልጹ ይደረጋል።
ሥነ ሥርዓቱን የሚቆጣጠረው ሞሐመድ ራሱላህ ጓድ አዛዥ ሐሳን ሐሳንዛዴህ እንዳሉት የአያቶላህ አሊ ኻሜኒ አስከሬንን የያዘው ሳጥን ከፍ ባለ መድረክ ላይ ለሕዝብ ዕይታ ይቀርባል። እንግዶችም ከ15 አስከ 20 ደቂቃ ባለው ጊዜ ውስጥ እንዲወጡ ይደረጋል።
ማክሰኞ ዕለት ደግሞ በሺዓ እስልምና አማኞች ዘንድ ከፍተኛ ስፍራ በሚሰጣት እና ከዋና ከተማዋ ቴህራን በስተደቡብ በምትገኘው ቆም ከተማ ይካሄዳል። በከተማዋ ዋነኛ የሃይማኖት ምልክት ከሆኑት ስፍራዎች መካከል አንዱ በሆነው ጃምካርን ውስጥ በከፍተኛ የሺዓ መንፈሳዊ መሪ የቀብር ፀሎት ይደረጋል።
ረቡዕ ደግሞ የኻሜኒ አስከሬን ወደ ጎረቤት አገር ኢራቅ ናጃፍ ከተማ ይወሰዳል። የሺዓ እስልምና የመጀመሪያው ኢማም በሆኑት ኢማም አሊ መስጂድ ውስጥ የሚካሄደው ፀሎት ተከትሎ አስከሬኑ ወደ ኢራን ከመመለሱ በፊት የስንብት ሥነ ሥርዓቱ ካርባላ በምትባል ከተማ ውስጥ ይደረጋል።
በኢራቅ የሚካሄደው ሥነ ሥርዓት እዚያ ባሉ ቡድኖች ጥያቄ መሠረት የሚደረግ እንደሆነ የኢራን ባለሥልጣናት ተናግረዋል። አንዳንድ ተንታኞች ይህ ስነ ስርዓት ኻሜኒ በዓለም ዙሪያ ባሉ የሺዓ እምነት ተከታዮች ዘንድ ያላቸውን ተጽእኖ እንዲሁም ኢራን በቀጣናው ኣላትን የሃይማኖት እና የፖለቲካ ትስስር እንደሚያሳይ ተናግረዋል።
የቀብር ሥነ ሥርዓቱን ለማስተባበር ወደ ኢራቅ ተጉዘው የነበሩት የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ቀብሩ ለኢራን "ትዕምርታዊ ጠቀሜታ" እንዳለው ተናግረዋል።
በመጨረሻም ሐሙስ ዕለት የኻሜኒ የቀብር ሥነ ሥርዓት በትውልድ ከተማቸው ማሻድ ውስጥ በሚገኘው በየዓመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በሚጎበኙት እና የኢራን ዋነኛው የሃይማኖት ስፍራ በመሆነው ኢማም ሬዛ ቅዱስ ስፍራ ይፈጸማል።
ከዚያም በኋላ የሀዘን ሥነ ሥርዓቱ ለቀጣይ 40 ቀናት በመላዋ ኢራን ውስጥ የሚካሄድ ሲሆን ቀብራቸው አንድ ዓመት አስኪሞላው የመታሰቢያ ዝግጅቶች ይከናወናሉ።
የአያቶላህ አሊ ኻሜኒ የቀብር ሥነ ሥርዓት የሚካሄደው ኢራን ከአሜሪካ እና ከእስራኤል ጋር ያደረገችውን ከባድ ጦርነት ተከትሎ ከፍተኛ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ፈተናዎች በገጠማት ጊዜ ነው።
ተንታኞች እንደሚሉት በአንድ ርዕዮተ ዓለማዊ የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ ለመሪዎች የሚደረግ የቀብር ሥነ ሥርዓት ፖለቲካዊ እና ሃይማኖታዊ ዓላማን ለማሳካት ይጠቅማል።
አንዳንዶች የኢራን መንግሥት ሥነ ሥርዓቱን አንድነቱን እና የሚያራምደውን ትርክት ለማሳየት እና ለማጠናከር እንደ አጋጣሚ ይጠቀምበታል ይላሉ። እንዲሁም ከኻሜኒ በኋላ ያለውን ሥርዓት ለማጠናከር እና ቦታቸውን ለተረከበው ለልጃቸው ሞጅታባ ድጋፍን ለማሰባሰብ እንደተምሳሌት ሊያውሉት ይችላሉ።
ነገር ግን አንዳንዶች እንዲህ ዓይነቱ ትልቅ ሥነ ሥርዓት በአገሪቱ ያለውን ሥር የሰደደ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ክፍፍልን በራሱ ሊፈታው አይችልም ይላሉ።
ለቀድሞው ጠቅላይ መሪ የቀብር ሥነ ሥርዓት መጠነ ሰፊ ዕቅድ እና ዝግጅት የተደረገ ቢሆንም፤ የመሪነት ቦታውን የተረከቡት ልጃቸው ሞጅታባ ኻሜኒ፣ እህት እና ወንድሞቻቸው በአባታቸው ቀብር ላይ ይገኙ ይሆን የሚለውን ጨምሮ በርካታ ቁልፍ ጥያቄዎች እየተነሱ ነው።
የኻሜኒ ወንድ ልጆች ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ ከተካሄደው የ12 ቀናት ጦርነት በኋላ በይፋ ታይተው አይታወቅም። የካቲት ላይ ጦርነቱ ሲጀመር በተፈጸሙ ጥቃቶች ባለቤታቸውን ጨምሮ በርካታ የቤተሰባቸው አባላት እንደተገደሉባቸው የተዘገበው የአዲሱ ጠቅላይ መሪ የጤና ሁኔታን በተመለከተ የሚታወቅ ነገር የለም።
የቀብር ሥነ ሥርዓቱ አስፈጻሚ ኮሚቴ ዋና ፀሐፊ የሆኑት አሊ አክባር ማክሰኞ ዕለት እንደተናገሩት ሞጅታባ በቀብሩ ላይ መገኘታቸውን የተመለከተ ማንኛውም መረጃ የሚገለጸው በኢራን ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ እና በጠቅላይ መሪው ጽህፈት ቤት በኩል ነው።
ሌላኛው ያልተመለሰ ጥያቄ የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ፀሎትን የሚመራው ማን ነው የሚለው ነው። በሺዓ ሃይማኖት ልማድ መሠረት የፀሎት ሥነ ሥርዓቱን የሚመራው ግለሰብ ሃይማኖታዊ እና ፖለቲካዊ ተሰሚነትን የሚይዝ ነው።
ስለዚህም አዲሱ ጠቅላይ መሪ ሞጅታባ ኻሜኒ በሥነ ሥርዓቱ ላይ በይፋ የሚገኙ ከሆነ የኢራንን የወደፊት መሪን በተመለከተ ምልክት ሊሆን እንደሚችል አንዳንድ ታዛቢዎች ይናገራሉ።