እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ያላቸው አገራት ለምን ለዓለም ዋንጫ አያልፉም?

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

ሊዮኔል ሜሲ በዘንድሮው ዓለም ዋንጫ የመጀመሪያውን ግብ ሲያስቆጥር የጨዋታው ተመልካቾች በደስታ ተሞልተዋል።

ተመልካቾቹ አርጀንቲናዊ ባይሆኑም እንኳን ደስታውን ከመጋራት አላገዳቸውም።

በባንግላዲሽ መዲና ዳካ ጨዋታውን ለመመልከት የተሰበሰቡ ሰዎች ዝነኛውን ነጭ እና ሰማያዊ ካናቴራ ለብሰው ነበር።

በሕንድ እና ኢንዶኔዥያ ከተሞችም ተመልካቾች ግጥሚያው በፍቅር ተሞልተው ተከታትለዋል።

ሜሲ እና የተቀረውን የአርጀንቲና ቡድን የሚደግፉ ተመልካቾች አገሮቻቸው ለዓለም ዋንጫ አላለፉም።

ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ካላቸው 10 አገራት መካከል ሁለቱ ብቻ ናቸው ለዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ያለፉት። እነዚህም ብራዚል እና አሜሪካ ናቸው።

ከዚህ በፊት ሩሲያ እና ናይጄሪያ በዓለም ዋንጫ ተሳትፈዋል።

ቻይና እና ኢንዶኔዥያ በዝነኛ ዓለም አቀፍ ስፖርታዊ ክንውን ላይ የተሳተፉት አንዴ ነው።

በሕዝብ ቁጥር ዓለምን የምትመራው ሕንድ፣ ባንግላዲሽ፣ ኢትዮጵያ እና ፓኪስታን ለዓለም ዋንጫ መድረስን ከመመኘት ባለፈ አልተሳካላቸውም።

በአውሮፓውያኑ 1950 በብራዚል ለተካሄደው የዓለም ዋንጫ ሕንድ አልፋ የነበረ ቢሆንም፤ ብዙም ሳትቆይ ከውድድሩ ወጥታለች።

ዝነኛዋ የባንግላዲሽ ተዋናይ፣ ፀሐፊ እና እግር ኳስ አፍቃሪ አውዲት ካሪም "በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ እግር ኳስ ወዳጆች ያሏት አገር በእግር ኳስ ወደ ኋላ መቅረቷ ተቀባይነት የለውም" ትላለች።

ለመሆኑ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ያላቸው አገራት ለምን ለዓለም ዋንጫ አያልፉም?

የአገር ስፋት አስተዋጽኦ አለው?

በሐሳብ ደረጃ ብዙ የሕዝብ ቁጥር ያለው አገር ብዙ አትሌቶች የመመልመል ዕድሉ ይሰፋል።

የዓለም ዋንጫን ካሸነፉ ስምንት አገራት ሰባቱ ሰፊ የሕዝብ ቁጥር አላቸው። እነዚህም አርጀንቲና፣ ብራዚል፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን እና ስፔን ናቸው።

በዚህ ቡድን ውስጥ የማትካተተው ኡራጓይ ናት።

እንግሊዛዊው የምጣኔ ሃብት ባለሙያ እና ምሁር ስቴፈን ስያማንስኪ እንደሚለው ከዓለም ዋንጫ ጋር በተያያዘ ከግምት የሚገባው የሕዝብ ቁጥር ብቻ አይደለም።

"እግር ኳስ ከምጣኔ ሃብት ጋር ተመሳሳይ አሠራር አለው። ሁለቱም ለማደግ ሰው ይፈልጋሉ። ካፒታል እና መሠረተ ልማትም ያስፈልጋቸዋል" ይላል።

በእግር ኳስ የሥልጠና ቦታዎች እና ችሎታ ያላቸው ተጫዋቾችን ማግኘት ቁልፍ ቦታ ይሰጣቸዋል።

ሳይመን ኩፐር ከተባለ ባለሙያ ጋር በጥምረት በሠሩት ጥናት መሠረት አንድ አገር የትኛውንም ነገር ለማሸነፍ "በአማካይ በዓመት ወደ 15 ሺህ ዶላር ገቢ ያስፈልገዋል።"

ብራዚል እና አርጀንቲና የአገር ውስጥ ጠቅላላ ገቢያቸው ከዚህ ያነሰ ቢሆንም አንድ ላይ ስምንት የዓለም ዋንጫ አሸንፈዋል።

እንግሊዛዊው የምጣኔ ሃብት ባለሙያ ገቢ ላይ ክህሎት መጨመር አለበት የሚለው ለዚህ ነው።

"ክህሎት የሚዳብረው በልምድ ነው። በዓለም ዋንጫ ያሸነፉ አገራት ቅኝ ግዛት ከማክተሙ በፊት የ100 ዓመት ልምድ ያላቸው ናቸው" ይላል።

ኡራጓይ 3.5 ሚሊዮን ሕዝብ ቢኖራትም ሁለት ጊዜ (በአውሮፓውያኑ 1930 እና 1950) የዓለም ዋንጫ ያሸነፈችውም በዚህ ምክንያት ነው።

የኡራጓይ የመጀመሪያ ዓለም አቀፍ ግጥሚያ በ1902 ከአርጀንቲና ጋር ሲሆን 6 ለባዶ አሸንፈዋል።

የብራዚል ግጥሚያ ከዚህ ከ12 ዓመታት በኋላ ነበር።

የአፍሪካ እና ደቡብ እስያ ብሔራዊ ቡድኖች ዕድሜያቸው ከዚህ ያጠረ ሲሆን፣ እግር ኳስ የተስፋፋውም ዘግይቶ ነው።

ሆኖም ግን እንደ ሞሮኮ ያሉ ቡድኖች ስኬታማ ሆነዋል።

በዓለም ዋንጫ ለግማሽ ፍጻሜ በመድረስ የመጀመሪያዋ አፍሪካዊ አገር ሆና በ2022 የኳታር የዓለም ዋንጫ ታሪክ ሠርታለች።

በአውሮፓውያኑ 2002 የዓለም ዋንጫን ከጃፓን ጋር አዘጋጅ የነበረችው ደቡብ ኮሪያ ከአንድ እስከ አራት ባለው ደረጃ በማጠናቀቅ የመጀመሪያዋ የእስያ አገር ሆናለች።

"ኢንዶኔዥያ፣ ሕንድ፣ ባንግላዲሽ እና ሌሎችም አገራት እዚህ ላይ አልደረሱም" ሲል ባለሙያው ያስረዳል።

እነዚህ አገራት ውስን ግብዓት እና ክህሎት ስላላቸው ወደ ኋላ መቅረታቸውን ይናገራል።

የኢትዮጵያ ችግር ምንድን ነው?

ኢትዮጵያ በአውሮፓውያኑ 1962 የአፍሪካ ዋንጫ ብታሸንፍም ለዓለም ዋንጫ አልፋ አታውቅም።

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገራት መካከል ለማለፍ ተቃርባ የነበረው በ2014 ቢሆንም በናይጄሪያ ተረትታለች።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ በኢንቨስትመንት እጥረት እንደሚፈተን ተንታኞች ሲናገሩ ይደመጣል።

የአገሪቱ ብሔራዊ ቡድን በደጋፊው ፊት የሚጫወትበት ደረጃውን የጠበቀ ስቴድየም አለመኖሩም ይነሳል።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሥራ አስኪያጅ ክፍሌ ሰይፈ በሰኔ ወር ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ "በዚህ ዙር በሦስት የተፈቀዱ ስቴድየሞች ብቻ 380 ግጥሚያዎች አድርገናል" ብለዋል።

ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ከሞሮኮ ጋር የተጋጠመው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ስቴድየም አጥቶ እንደነበር አይዘነጋም።

ከእግር ኳስ ውጪ ያሉ አማራጮች

አንዳንድ አገራት ከእግር ኳስ ውጭ ባሉ ስፖርቶች የበለጠ ታዋቂ መሆናቸውን ማንሳትም ያስፈልጋል።

ለምሳሌ በሕንድ የሚዘወተረው ክሪኬት ነው። የአገሪቱ የክሪኬት ሊግ በዓለም በሃብት የናጠጠው እንደሆነ ይነገርለታል።

መካከለኛ እና ከፍተኛ ገቢ ያላቸው ወላጆች ልጆቻቸው በክሪኬት እንዲጎብዙ ያበረታታሉ።

የቀድሞ የተጫዋቾ መልማይ ሻም ታፓ "ልጆች በእግር ኳስ ስኬታማ ከሆኑም ገንዘብ ሊያገኙ እንደሚችሉ ወላጆች ማወቅ አለባቸው" ይላል።

አውዲት እንደምትለው ከሆነ ግን እንደ አውስትራሊያ እና ኒው ዚላንድ ያሉ አገራት በክሪኬት ጥሩ ስም ቢኖራቸውም በእግር ኳስም ጎልተው ወጥተዋል።

"በዓለም ዋንጫ ለመሳተፍ በቂ ዝግጅት እና መዋቅራዊ አሠራር የለንም" ስትል ታስረዳለች።

የቻይናን ጉዳይ ለብቻው ማየት ይቻላል። በኦሊምፒክ ገናና ከሆኑ አገራት አንዷ እየሆነች ነው።

በወንዶች እግር ኳስ ግን ተመሳሳይ ውጤት አልተመዘገበም።

ቤይጂንግ የሚገኘው የእግር ኳስ ተንታኝ ማርክ ድራየር "ቻይና ዓለም አቀፍ እግር ኳስ ተጫዋቾች ማፍራት የማትችልበት ምክንያት የለም" ይላል።

የቻይና ዋነኛው ችግር ሁሉም ነገር በመንግሥት ቁጥጥር ሥር መሆኑ ነው ሲል ያስረዳል።

ትዕዛዞች ከላይ ወደ ታች በተዋረድ ስለሚተላለፉ እግር ኳስ ዝነኛ እንዲሆን የበላይ አካላት መገፋፋት እንዳለባቸው ይገልጻል።

ቻይና ከ2010 ጀምሮ እግር ኳስ ላይ ከፍተኛ ገንዘብ ብታፈስስም ከ2002 ወዲህ ወደ ዓለም ዋንጫ አልተመለሰችም።

ኢንዶኔዥያ በ1938 በዓለም ዋንጫ ብትወዳደርም ከዚያ በኋላ አልተመለሰችም። ዘንድሮ ጥሩ ብቃት ብታሳይም ለማለፍ አልቻለችም።

ኢንዶኔዥያዊ የዘር ሐረግ ያላቸው የአውሮፓ ተጫዋቾችን አሳትፋለች።

የቢቢሲ ኢንዶኔዥያ ባልደረባ ዤሮም ዊራዋን "ስምንት ወይም ዘጠኝ የሚሆኑት ተጫዋቾች አውሮፓ የተወለዱ የሚሆኑበት ጊዜ አለ" ይላል።

ፓኪስታን እና ባንግላዲሽ በመጀመሪያው የውድድር ዙር ነው የወጡት።

በፖለቲካ ምክንያት ፊፋ ከ2017 እስከ 2025 ባሉት ዓመታት ሦስት ጊዜ ፓኪስታንን ከውድድር አግዷል።

እግር ኳስ አፍቃሪዋ አውዲት እንደምትለው ብዙ አገራት ለዓለም ዋንጫ ባያልፉም በውድድሩ መዝናናትን እንደ ማካካሻ ይወስዳሉ።

"በእኔ ዕድሜ ባንግላዲሽን በዓለም ዋንጫ አያለሁ ብዬ አላስብም። ግን የባንግላዲሽ ዜጎች በዓለም ዋንጫ መደሰታቸውን ይቀጥላሉ።"