'ለእርጅና መከላከያ' በሚል የእንግዴ ልጅ የሚያዘዋውር ቡድን አባላት ፓኪስታን ውስጥ ተያዙ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ፓኪስታን እርጅናን የሚከላከል መድኃኒት ለመሥራት ከሆስፒታሎች የእንግዴ ልጆችን በማዘዋወር በተጠረጠረ ቡድን ላይ ምርመራ እያካሄደች ነው።

የአገሪቷ የፌደራል ምርምራ ተቋም ቡድኑን በየወሩ ከተለያዩ ሆስፒታሎች 200 ኪሎ ግራም የሚመዝን የእንግዴ ልጆችን በመግዛት ከስሷል።

ተጠርጣሪው ቡድን የእንግዴ ልጁን ወደ ውጭ ከመላኩ በፊት እንደሚያደርቁት እና እንደሚፈጩት የምርመራ ተቋሙ ለቢቢሲ ገልጿል።

ባለፈው ሳምንት በኢስላማባድ በተደረገ ፍተሻም ባለሥልጣናት በአንድ ሕገ ወጥ ማቀነባበሪያ ውስጥ 500 ኪሎ ግራም የሚመዝን እና የሰው እንግዴ ልጅ እንደሆነ የታመነ ነገር አግኝተዋል።

ይህንን ተከትሎም አምስት ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

የምርመራ ተቋሙ ባጋራቸው ምሥሎችም ለመከዘን እና የእንግዴ ልጁን ለማቀነባበር በሚጠቀሙበት ቤት ውስጥ በደረቁ እንግዴ ልጆች የተሞሉ ትሪዎች በጋሪ ላይ ሆነው ታይተዋል።

በሌላ በኩል የምርመራ ተቋሙ ረቡዕ ዕለት በኢስላማባድ አየር ማረፊያ ወደ ቪየትናም ሊጓጓዝ የነበረ የሰው ሕብረ ሕዋስ (ቲሹ) በቁጥጥር ሥር አውሏል።

የፓኪስታን የሰው አካል ዝውውርን የሚቆጣጠረው ባለሥልጣን ባለሙያ የሆኑት ሒና ካንዋል፣ አምስቱ ተጠርጣሪዎች በኢስላማባድ እና ራዋልፒንዲ ከሚገኙ ሆስፒታሎች የእንግዴ ልጆቹን አንዱን በ2.90 ዶላር እንደገዙት ተናግረዋል።

እንደ የምርመራ ተቋሙ ከሆነም የእንግዴ ልጆቹ በመርፌ የሚሰጥ የእርጅና መከላከያ ለመሥራት ወደ ውጭ ሊላኩ የነበሩ ሲሆን፣ እያንዳንዳቸው 2530 ዶላር የሚያወጡ ናቸው።

የቡድኑ ተግባር ከመዲናዋ ኢስላማባድ ውጭም እንደ ላሆር፣ ፔሻዋር እና ራዋልፒንዲ ባሉ ሌሎች ትላልቅ ከተሞች የተስፋፋ እንደሆነም ተቋሙ ያምናል።

በመሆኑም የኢምግሬሽን መኮንኖች፣ የቆሻሻ አወጋገድ እና አስተዳዳር ድርጅቶች እና ሆስፒታሎች ላይ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን ገልጿል።

በፓኪስታን በሰው አካል ክፍል በመነገድ ጥፋተኛ ሆኖ መገኘት 10 ዓመት የሚደርስ እስር እና እስከ 1 ሚሊዮን ሩፒ ( 3600 ዶላር ) የገንዘብ ቅጣትን ያስከትላል።

የፌደራል ምርመራ ተቋሙ ለቢቢሲ እንደገለፀው ቀደም ብሎ ከሕገ ወጥ የሰው አካል ንቅለ ተከላ ጋር በተያያዘ በርካታ እርምጃዎችን ወስዷል።

ሆኖም በተደራጀ እና ዓለም አቀፍ ሰንሰለት ባለው መልኩ ከሰው እንግዴ ልጅ ጋር በተያያዘ ይህ የመጀመሪያው ጉዳይ እንደሆነ ገልጿል።

አምስቱ ተጠርጣሪዎች ቀደም ብሎ የበግ እንግዴ ልጅ እያስረከቡ እንደሆነ የገለጹ ቢሆንም በኋላ ላይ በተደረገ ምርመራ የሰው እንግዴ ልጅ መሆኑን እንዳመኑ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

በፓኪስታን የማሕፀን እና ፅንስ ሐኪም የሆኑት ሳዳፍ ታሪቅ "በከፍተኛ ሁኔታ የሚመረዝ የሕክምና ቆሻሻ" ባሉት እንግዴ ልጅ አወጋገድ ዙሪያ ጥብቅ የሆነ መመሪያ እንዳለ ተናግረዋል።

በፓኪስታንም ሆነ በዓለም ዙሪያ ባሉ በርካታ አገራት ልጅ ከተወለደ በኋላ የእንግዴ ልጅ እንደ ቆሻሻ ይጣላል።

እንዲህ ዓይነቱን ቆሻሻ እንዲያስወግዱ የሚፈቀደው ግን የመንግሥት ፈቃድ ላላቸው ድርጅቶች ብቻ ናቸው።

እንግዴ ልጅ በእርግዝና ወቅት በማሕፀን ግድግዳ ላይ የሚያድግ እና በማሕፀን ውስጥ ያለን ሕፃን በሕይወት የሚያቆይ ጊዜያዊ የሰው አካል ነው። አንዲት እናት ከወለደች በኋላም አገልግሎቱ ያበቃል።

ሆኖም አንዳንድ ሰዎች እንግዴ ልጅ በፕሮቲን፣ በአይረን እና በስብ ንጥረ ነገሮች የበለፀገ እንደሆነ እና ይህም ለአዋቂዎች ጠቃሚ እንደሆነ ያምናሉ።

አንዳንዶች የሰውነት ሕብረ ሕዋሳት (ቲሹ) እንደገና እንዲዳብሩ ያደርጋል በሚል በክኒን እና በመርፌ በሚሰጥ መልኩ ያዘጋጁታል።

በዚህ ዙሪያ በዓለም ዙሪያ ያሉ ሳይንሳዊ መረጃዎች እንዲሁም ደንቦች ግን የተለያዩ ናቸው።