ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን "የፋኖ ታጣቂዎች" ፈጸሙት በተባለ ጥቃት "11 ሰዎች" መገደላቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ
በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ አገምሳ ከተማ እና በዙሪያው ባሉ መንደሮች ውስጥ "በፋኖ ታጣቂዎች ተፈጽሟል" በተባለ ጥቃት ሁለት ንጹኃንን ጨምሮ 11 ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎችን እንዲሁም የዞኑ አስተዳዳሪ ተናገሩ።
ታጣቂዎቹ በመቶዎች የሚቆጠሩ ከብቶች እና ሌሎች ንብረቶች መዘረፋቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እንደገለጹት ጥቃቱ የተፈጸመው ማክሰኞ ሰኔ 23/2018 ዓ.ም. ከንጋት 11 ሰዓት አንስቶ ነው።
ለደኅንነታቸው በመስጋት ስማቸውን እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የአገምሳ ከተማ ነዋሪ፤ ታጣቂዎቹ የመጡት "ከምሥራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ ነው" ብለዋል።
ሌላ ነዋሪ ደግሞ "አስከፊ ሁኔታ ነው የነበረው። ከማክሰኞ ሌሊት 11 ሰዓት ሰው ከእንቅልፉ ሳይነሳ የፋኖ ታጣቂዎች ነዋሪዎችን መግደል ጀመሩ። ንብረትም ዘርፈዋል። የሞቱ ብዙ ናቸው፤ የቆሰሉም እንደዚሁ" በማለት የደረሰውን አስታውሰዋል።
ሁለት ነዋሪዎች እንደተናገሩት፤ ተጣቂዎቹ ወደ አካባቢው በገቡበት ሰዓት በስፍራው የክልልም ሆነ የፌደራል መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች አልነበሩም።
ጥቃቱ የተፈጸመው በአካባቢው የነበረው መከላከያ ሠራዊት አባላት ከአካባቢው ከወጡ ከቀናት በኋላ ነው።
ነዋሪዋ፤ "የአገር መከላከያ ነበሩ፤ እነሱ ከዚያ ወጡ። ምክንያቱን አናውቅም። ከወጡ ከሁለት ቀናት በኋላ ታጣቂዎቹ ገቡብን። ከጥቃቱ በኋላ ግን መከላከያው ወደ ካምፑ ተመልሷል።
ይህ ጥቃት የመጀመሪያ አይደለም፤ ለሦስተኛ ጊዜ ነው የተፈጸመው" ሲሉ ሁኔታውን ገልጸዋል።
ሌላ ነዋሪ በበኩላቸው "የፌደራል [ኃይሎች] የሉም። ሚሊሻማ ነበረ፤ አልነቃበትም። ያው ዝም ብሎ በድንገት ገብቶ ሕዝቡ ከእንቅልፉ ሳይነቃ ከተማ ውስጥ ያለ ከብት፣ በግ፣ ፍየል አንድ ሳይቀር የሰው ቤት ሰብረው ይዘው ወጡ" ብለዋል።
"400 ገደማ ከብቶች" መወሰዳቸውን የሚናገሩት እኚህ ነዋሪ፤ መደብሮች ጭምር መዘረፋቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ሌላኛዋ ነዋሪ ደግሞ "ከብት አልቀረም፤ ፍየልም አልቀረም። ያስቀሩት ምንም ነገር የለም። የምንሸሽበት ቦታ ሁሉ አልነበረንም። አሁን ራሱ አስጊ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው" ብለዋል።
እንደ ነዋሪዎቹ ገለጻ፤ በጥቃቱ ንጹኃን ነዋሪዎች እና የአካባቢው ሚሊሻ አባላት ተገድለዋል። አንድ ነዋሪ "11 ሰዎች" መገደላቸውን እና "17 ሰዎች" መቁሰላቸውን ተናግረዋል።
ከተገደሉት መካከል ሁለት "ሲቪል ሰዎች"፤ የተቀሩት ደግሞ "የሚሊሻ አባላት" እንደሆኑ አብራርተዋል።
ሌላ ነዋሪ በበኩላቸው "ከሟቾቹ ውስጥ የማውቃቸው ሚሊሻዎች ይገኙበታል" ሲሉ እማኝነታቸውን ሰጥተዋል።
ጥቃቱ እስከ ረፋድ አምስት ሰዓት ድረስ ቀጥሎ እንደነበር የገለጹ አንድ ነዋሪ፤ የፀጥታ ኃይሎች የደረሱት "ሚሊሻዎቹ ከሞቱ በኋላ" መሆኑን ተናግረዋል።
የሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ምሬሳ ፊጣ ጥቃቱ መፈጸሙን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
"ጥቃቱ [ማክሰኞ] ነው የተፈጸመው፤ በሰው እና በንብረት ላይም ጉዳት ደርሷል። የከተማው እና የዞኑን ኃይል አቀናጅተን ታጣቂዎቹ እንዲያፈገፍጉ አድርገናል። በዚያው ቀን ጠዋት 4:30 አካባቢ የአገር መከላከያ ደርሶልናል" ብለዋል።
"ታጣቂው ኃይል አሁንም አጎራባች ቀበሌዎች ውስጥ" መኖሩን የሚያመለክት መረጃ እንዳላቸው የጠቀሱት ዋና አስተዳዳሪው፤ "ፋኖ ከተማውን ተቆጣጥሮ ነበር" መባሉን ግን አስተባብለዋል።
"ጠላት ከተማውን ተቆጣጥሬያለሁ ሊል ይችላል፤ በተግባር ግን የለበትም። ከዚያ ከተማ ተመትቶ ወጥቷል" ሲሉ ተናግረዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እና የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ምሬሳ በአካባቢው ለተፈጸመው ጥቃት ተጠያቂ ያደረጉት "የፋኖ ኃይሎችን" ነው።
የአሙሩ ወረዳ በፌስቡክ ገጹ ባወጣው መረጃ "የፋኖ ፅንፈኛ የተባለው ኃይል በአገምሳ ከተማ ተኩስ በመክፈት በሕይወት እና በንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱ" ገልጿል።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪው አቶ ምሬሳ በበኩላቸው፤ በወረዳው በሚገኙት "ሁለት ቀበሌዎች" ውስጥ የፋኖ ኃይሎች እንደሚንቀሳቀሱ ተናግረዋል።
ቢቢሲ በፋኖ ኃይሎች ላይ የቀረበውን ክስ በተመለከተ ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም። ይሁን እንጂ ታጣቂ ኃይሉ ከዚህ ቀደም በሲቪሎች ላይ ጥቃት ፈጽሟል በሚል የቀረቡበትን ክሶች ሲያስተባብል ቆይቷል።
በሆሮ ጉድሩ ወረዳ መሠል ጥቃቶች ሲደርሱ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። በ2014 ዓ.ም. መጨረሻ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት፣ የአማራ ኢመደበኛ ታጣቂ ኃይሎች እና ግለሰቦች ባደረሷቸው ተከታታይ ጥቃቶች ከ100 በላይ ሰላማዊ ሰዎች እንደተገደሉ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አስታውቆ ነበር።