ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የማሊው ወታደራዊ መሪ ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር መነጋገራቸውን ገለጹ
የማሊ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት ኮሎኔል አሲሚ ጎኢታ ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በስልክ መነጋገራቸውን ገለጹ።
በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን የያዘው ጁንታ መሪ የሆኑት ኮሎኔሉ፤ ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር በስልክ የተነጋገሩት ትናንት ረቡዕ ነሐሴ 04/2014 ዓ.ም. መሆኑን አመልክተዋል።
“ለማሊ ፖለቲካዊ ሽግግር የሩሲያ ፌዴሬሽን ድጋፍ ላይ ተነጋግረናል” ያሉት ኮሎኔል ጎኢታ፤ የማሊን ሉዓላዊነት ያከበረ እና የሕዝቡን ፍላጎት የሚረዳ የሁለቱ አገራት ወዳጅነት ጠንካራ መሆኑን ለፕሬዝዳንት ፑቲን መገለጻቸውን በትዊተር ገጻቸው አስፈረዋል።
ከትናንት በስቲያ ማክሰኞ ኮሎኔል አሲሚ ጎኢታ በተገኙበት ሥነ ሥርዓት ላይ ማሊ ከሩሲያ የተረከበቻቸውን በርካታ ተዋጊ አውሮፕላኖችን በዋና ከተማዋ ባማኮ አየር ማረፊያ ለዕይታ አቅርባ ነበር።
ሞስኮ በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን ከጨበጠው ከማሊ ጦር ሠራዊት ጋር ያላንትን የጠበቀ ወዳጅነት ለማሳየት በሶቪየት ሕብረት የተመረቱ የጦር አውሮፕላኖችን ለማሊ ሰጥታለች።
ከመፈንቅለ መንግሥቱ በኀወላ የማሊ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት ከምዕራባውያን አገራት በተለይ ደግሞ ከፈረንሳይ ጋር የነበረው ግንኙነት በእጅጉ ሻክሯል።
ፈረንሳይ የሩሲያው ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን ዋግነር በምዕራባ አፍሪካዊቷ አገር መገኘቱን ከተቃወመች በኋላ ከጊዜያዊው ወታደራዊ መንግሥት ጋር ያላት ግንኙነት ተበላሽቶ ወደታደሮቿን ከአገሪቱ አስወጥታለች።
የፈረንሳይ እና ሌሎች የአውሮፓ አገራት ጥምር ጦር ወታደሮች በማሊ ተሰማርተው ጸንፈኛ እስላማዊ ቡድኖችን ሲወጋ ቆይቷል።
ለምዕራባውያን ጀርባዋን ሰጥታ ፊቷን ወደ ሩሲያ ባዞረችው ማሊ፣ በጽንፈኛ ቡድኖች የሚፈጸሙ ጥቃቶች ተበራክተዋል።
ከጥቂት ቀናት በፊት በእስማላዊ ታጣቂ ቡድን በተፈጸመ ጥቃት የሞቱ ሰዎች ቁጥር 42 መድረሱ ተገልጿል።
ባለፈው እሁድ ነሐሴ 01/2014 ዓ.ም. ከኢስላሚክ ስቴትስ (አይኤስ) ጋር ግንኙነት አለው የተባለ ቡድን በፈጸመው ጥቃት በርካታ ወታደሮች መገደላቸው እና መቁሰላቸው ተዘግቦ ነበር።
ቡድኑ ማሊ፣ ቡርኪና ፋሶ እና ኒጀር በሚዋሰኑበት የማሊ ግዛት ውስጥ በፈጸመው ጥቃት የሟቾች ቁጥር 42 መድረሱን እና በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ደግሞ መኖሪያቸውን ጥለው መሰደዳቸውን የአካባቢው ባለሥልጣናት ገልጸዋል።