ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሩሲያ ሮኬቶች የኒውክሌር ጣቢያዋ ላይ ጉዳት ማድረሳቸዋን ዩክሬን አስታወቀች
የሩስያ ሮኬቶች በግዙፉና በሩሲያ ቁጥጥር ስር በሚገኘው የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ክፍል ላይ ጉዳት አድርሰዋል ሲል የዩክሬን የኒውክሌር ኤጀንሲ ገለጸ።
ሆኖም በጉዳቱ የራዲየሽን (ጨረሮች) ማፈትለክ አለመከሰቱንም ጨምሮ አክሏል።
ኤነርሃቶም በደቡባዊ ዩክሬን በሚገኘው ዛፖሪዥያ የኒውክለር ኃይል ማመንጫ የናይትሮጅን-ኦክስጅን ክፍሉ እና ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመሩ ተጎድቷል ብሏል።
በሩሲያ የተሾሙ የአካባቢው ባለስልጣናት ዩክሬንን ተቋሙን ደብድባለች ስትል ቀደም ብለው ከሰዋል። ዩክሬንም የሩስያ ኃይሎችን ከስፍራው ሆነው በሲቪል አካባቢዎች ላይ ሮኬቶችን በመተኮስ "የሽብር ስልቶችን" ተጠቅመዋል በሚል ወቅሳለች።
“በየማለዳው ከእንቅልፋችን ተነስተን ስናይ የሚመቱት የመኖሪያ አካባቢዎች ብቻ ናቸው” ሲል አንድ የአካባቢው ነጋዴ ለቢቢሲ ተናግሯል። ቢቢሲ በኒውክሌር ጣቢያው ላይ የደረሰውን ጉዳት ማረጋገጥ አልቻለም። ኤነርሃቶም አርብ ዕለት በደረሱ ሁለት ዙር የሩስያ ሮኬት ጥቃቶች ለጣቢያው ኃይል የሚሰጡ መስመሮች እንዲያቋርጡ ማድረጋቸውን ተናግሯል። ኤነርሃቶም "ሃይድሮጂን ሊሾልክ እና ራዲዮአክቲቭ ቅንጣቶችን የመበተን አደጋ አለ" ብሏል።
"የእሳት አደጋው ከፍተኛ ነው። በአሁኑ ወቅት ምንም አይነት ጉዳት አልደረሰም" ሲል አክሏል።
ሩሲያ የዛፖሪዥያ ጣቢያን በወርሃ መጋቢት የተቆጣጠረች ሲሆን የዩክሬን ሠራተኞች ሥራቸውን እንዲቀጥሉ አድርጋለች። ሩሲያ ጣቢያውን እና በዙሪያው ያሉትን አካባቢዎች ተቆጣጥራለች። በዩክሬን ከተያዘው ግዛት አቅራቢያ ላይ ይገኛል። ጣቢያው ስድስት በግፊት የሚሠሩ የውሃ ማብላያዎችን እና ሬዲዮአክቲቭ ተረፈ ምርት ማከማቻዎችን ይዟል።
የምዕራቡ ዓለም ባለሥልጣናት ሩሲያ በአካባቢው የምትጠቀመውን ስልቶች በማንሳት ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።
ጣቢያው በኤነርሆዳር ከተማ ይገኛል። ከተማዋ በዩክሬን ደቡብ-ምስራቅ በዲኒፐር ወንዝ ዳርቻ ላይ ሰፍሯል። በሩሲያ የተሾሙ የኤነርሆዳር ባለሥልጣናት የዩክሬን ኃይሎች አርብ ዕለት ጣቢያውን ሁለት ጊዜ “ከዲኒፔር ተቃራኒ አቅጣጫ” ሆነው ደበድበዋል ብለዋል ።
“ብሔርተኞቹ ለሁለተኛ ጊዜ ዒላማቸውን መምታት የቻሉ ሲሆን ይህም በጣቢያው የኢንዱስትሪ ቦታ ላይ አርፈዋል" ብለዋል።
ኢንተርፋክስ የተባለው የሩሲያ መንግስት የዜና ወኪል በሞስኮ የተሰየመውን የፋብሪካውን አስተዳደር ጠቅሶ እንደዘገበው ከፋብሪካው የኤሌክትሪክ መስመሮች ውስጥ ሁለቱ በዩክሬን ጥቃት ተመተው ቃጠሎ አድርሰዋል ብሏል።
ከጣቢያው የኤሌክትሪክ መስመሮች ምን ያህሉ እንደሚሠሩ ግልጽ አይደለም። በተቃራኒ የተሰለፉትን ኃይሎች መካሰሶችም በተናጥል አልተረጋገጡም።
ቀደም ሲል የእንግሊዝ መከላከያ ሚኒስቴር በየዕለቱ በሚያወጣው የስለላ መረጃ ሩሲያ አካባቢውን ጥቃት ለመሰንዘር እየተጠቀመችበት ነው ብሏል። የኒውክሌር ኃይል ማመንጫው እንደማይመታ ስለሚያውቁ እንደምሽግ ተጠቅመው ከዩክሬን ሃይሎች ሊደርስ የሚችለውን ጥቃት ለመቀነስ እየተጠቀመች ነው ብሏል።
ጣቢያው ሙሉ በሙሉ ከቁጥጥር ውጭ ሆኗል ሲሉ የተባበሩት መንግስታት የኒውክሌር ኤጀንሲ ኃላፊ የሆኑት ራፋኤል ግሮሲ በዚህ ሳምንት አስጠንቅቀዋል።
በኒውክለር ጣቢያው ላይ የሚከሰት ማንኛውም አደጋ አስከፊ ውጤት ሊያስከትል ይችላል።
ኒኮፖል በሚባለው እና ከወንዙ ማዶ የሚገኘው እና አሁንም በዩክሬን ቁጥጥር ስር በሚገኘው አካባቢ ያሉ ሲቪሎችም ተመሳሳይ አስተያየት ያንፀባርቃሉ።
"የእኛ ኃይሎች አይተኩሱም ምክንያቱም የጣቢያው 30 ኪ.ሜ ዙሪያ የማይነካ ነው። ወደዚያ መተኮስ አይፈልጉም። ነገር ግን ሩሲያውያኑ አሸባሪዎች ናቸው። ለእነርሱ ምንም የማይነካ ነገር የለም" ሲል ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ የአካባቢው ነጋዴ ለቢቢሲ ተናግሯል። "እኛን ለማስፈራራት ታስቦ ነው" ሲል አክሎ ከመጋቢት አጋማሽ ጀምሮ በየምሽቱ ሮኬቶች ኒኮፖልን ይመቱ እንደነበር አስረድቷል። የጣቢያው የቀድሞ ሠራተኛ አሁንም በስፍራው ካሉ ከባልደረቦቻቸው ጋር የሚገናኙ ግለሰብ ለቢቢሲ እንደገለጹት ከሆነ በፋብሪካው አካባቢ ሮኬቶችን ከመተኮሱ ባለፈ የሩሲያ ኃይሎች አንዳንድ ወታደራዊ ቁሳቁሶችን ወደ አንዱ ህንጻ አስገብተዋል ብለዋል።
ቢቢሲ ጉዳዩን ማረጋገጥ ባይችልም ኤነርሃቶም ተመሳሳይ ነገር ይፋ አድርጓል።
የተባበሩት መንግስታት የኒውክሌር ተቆጣጣሪ ቡድን በኃይል ማመንጫው ውስጥ ለሚሰሩ ሠራተኞች ሀጉኔታዎች አስቸጋሪ ናቸው ሲል በተደጋጋሚ አስጠንቅቋል።