ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአሜሪካ የዎልማርት ሱፐርማርኬት ሥራ አስኪያጅ በሠራተኞቹ ላይ በከፈተው ተኩስ ስድስት ሰዎች ተገደሉ
በአሜሪካ ቨርጂኒያ ግዛት በሚገኘው ዎልማርት ሱፐርማርኬት ለረጅም ጊዜ ያገለገለ ሥራ አስኪያጅ በሠራተኞች ላይ በከፈተው ተኩስ ስድስት ሰዎችን ሲገድል ሌሎች ስድስት አቆሰለ።
በቼሳፒክ በሚገኘው እና ሥራ ወደ ሚበዛበት የሱፐርማርኬቱ ቅርንጫፍ ፖሊስ የተጠራው ግለሰቡ በሠራተኞች ክፍል ውስጥ በባልደረቦቹ ላይ ተኩስ ከከፈተ በኋላ ነበር።
ከዚያም መሣሪያውን ወደራሱ አዙሮ በመተኮሱ ባጋጠመው ጉዳት ሕይወቱ ሊያልፍ እንደቻለ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
ሥራ አስኪያጁ ባልደረቦቹን ተኩሶ የገደለበት ምክንያት ምን እንደሆነ እስካሁን ግልጽ አይደለም። ፖሊስም ከግድያው ጋር በተያያዘ እየፈለገ ያለው አካል የለም።
ግድያውን የፈፀመው ግለሰብ የ31 ዓመት እድሜ ያለው አንድሪ ቢንግ እንደሚባል ፖሊስ ይፋ አድርጓል። ፖሊስ እንዳለው ግለሰቡ በርካታ ጥይቶች እና ሽጉጥ ታጥቆ ነበር።
ዎልማርት በበኩሉ ከአውሮፓውያኑ 2010 ጀምሮ በድርጅቱ የተቀጠረው ይህ ግለሰብ የማታ ተረኛ እንደነበር ገልጾ፣ “የተጎዱ ሠራተኞቻችን እና ቤተቦቻቸውን ለማገዝ የምንችልውን ለማድረግ ትኩረት ሰጥተን እየሠራን ነው” ብሏል።
ከሥራ አስኪያጃቸው በተከፈተባቸው ተኩስ ጉዳት ካጋጠማቸው ስድስት ሰዎች መካከል ሁለቱ በአስጊ ሁኔታ ላይ ሲሆኑ፣ አንደኛው ደግሞ በተሻለ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል።
ለፖሊስ የመጀመሪያ ጥሪ የደረሰው ማክሰኞ ምሽት 4 ሰዓት አካባቢ ሲሆን በሁለት ደቂቃ ውስጥ ነበር ወደ ሱፐርማርኬቱ የደረሰው።
ከዚያም ወደ ውስጥ በመግባት ሱፐርማርኬቱ ውስጥ የነበሩ 50 ሰዎች እና የተጎዱ ሰዎች እንዲወጡ ካደረገ ከአንድ ሰዓት በኋላ አካባቢው ሰላም መሆኑን ተናግረዋል።
የፖሊስ ኃላፊው ማርክ ሶሌስኪ ረቡዕ ዕለት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ የጥቃቱን ምክንያት ለማጥራት በርካታ ቀናት ሊወስድ እንደሚችል ገልጸው፣ ከፌደራል ፖሊስ (ኤፍቢአይ) ጋር በመሆን ምርመራ እየተካሄደ ነው ብለዋል።
የዎልማርትን የደንብ ልብስ የለበሰ አንድ የዐይን እማኝ፣ የሠራተኛው ክፍሉን ለቆ እንደወጣና ተኩስ ከመከፈቱ በፊት ሌላ የሥራ ባልደረባው እንደገባ ተናግሯል።
የዎልማርት ሠራተኛ የሆነው ብሪያና ታይለር ለኤቢሲ ጉድሞርኒንግ አሜሪካ ፕሮግራም ሲናገር “ ሥራ አስኪያጃችን በሩን ከፍቶ ከገባ በኋላ ተኩስ ከፍቷል” ብሏል።
ጄሴ ዊልዘውስኪ በበኩሏ ተኩሱ ሲከፈት ጠረጴዛ ሥር ገብታ እንደተደበቀች ተናግራለች።
አንድ ሌላ የዎልማርት ሠራተኛም ሥራ አስኪያጁ ሽጉጡን ከደገነባት በኋላ ወደ ቤቷ እንድትሄድ እንደነገራት አስረድታለች።
በርካታ ሠራተኞች ሥራ አስኪያጁ ቀደም ብሎ ሌሎች ሰዎች አይወዱኝም የሚል ጭንቀት እንደነበረበት እና ስጋታቸውንም ለመንግሥት እንዳሳወቁ ለሲኤንኤን ተናግረዋል።
ፖሊስ ረቡዕ ዕለት በሰጠው መግለጫ፣ ሟቾቹ ሎሬንዞ ጋምብል፣ ብሪያን ፔንድልተን፣ ኬሌ ፓይል፣ ራንዳል ብሌቪንስ እና ትይኔካ ጆንሰን እንደሚባሉ አሳውቋል።
ሌላ የ16 ዓመት ሕጻንም በጥቃቱ የተገደለ ሲሆን፣ ሕጻን በመሆኑ ፖሊስ ስሙን ይፋ አላደረገም።
ሪፐብሊካኑ የቨርጂኒያ ገዢ ግሌን ዮአንኪን፣ ሐዘንን ለመግለጽ ሰንደቅ ዓላማ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ አዘዋል።
“በጉዳዩ ላይ አስተያየት ለመስጠት እና ሁኔታውን ለመረዳት ጊዜ ይኖረናል። ዛሬ ግን ያላሰቡትና ያልገመቱት የደረሰባቸው የተጎጂ ቤተሰቦችን የምናጽናናበት ነው” ብለዋል።
ፕሬዝደንት ጆ ባይደን በበኩላቸው ጥቃቱን “ትርጉም የሌለው እና ዘግናኝ ጥቃት” ብለውታል።
“ወሳኝ የሆነ የጦር መሣሪያ ሕግ ማሻሻያን ፈርሜያለሁ። ግን ይህም በቂ አልሆነም” ሲሉ ጨምረው ተናግረዋል።
ይህ ግድያ የተሰማው በአሜሪካዋ ግዛት ኮሎራዶ በተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪያን የምሽት ክለብ ውስጥ አንድ የጦር መሣሪያ የታጠቀ ግለሰብ ተኩስ ከፍቶ 5 ሰዎች መገደላቸው እና 17 ሰዎች መቁሰላቸው ከተሰማ ከቀናት በኋላ ነው።
በዎልማርት ሱፐርማርኬትም ተኩስ ሲከፈት ይህ የመጀመሪያው አይደለም። እንደ አውሮፓውያኑ 2019 በቴክሳስ ኤል ፓሶ በሚገኘው ዎልማርት 23 ሰዎች ተገድለዋል። ይህን ግድያ ፈፅሟል የተባለው ግለሰብ ፍርዱን እየተጠባበቀ ነው።